የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የሽልማት አሸናፊ ሆኑ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2005(ዋኢማ) - በእንግሊዝ የሚገኘው ብራይት ኢንተርቴይንመንት ኔትወርክ የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ በአፍሪካውያን ከሚሰጠው "ዘ ኦርደር ኦፍ ኪሊማንጃሮ" የተሰኘውን ከፍተኛ ሽልማት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰጠ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው ሽልማቱን የተረከቡት በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ከበደ ናቸው፡፡

አምባሳደር ብርሃኑ በሽልማት አሰጣጡ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቆራጥ ታጋይና ለሕዝባቸው በጽናት የቆሙ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡

በእሳቸው አመራር የተነደፉ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች ተግባራዊ በተደረጉባቸው ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የሠላምና የልማት ድሎች ከመገኘታቸው ባሻገር በድህነት ላይ የተከፈተውን ጦርነት ከግብ ለማድረስ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተነድፎ እየተተገበረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሽልማት አሰጣጡ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት በእንግሊዝ የሊበራል ዴሞክራት ፓርቲ ምክትል መሪና የፓርላማ አባል ሚስተር ሲሞን ሑግስ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አገራቸውን በዲፕሎማሲው መስክና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጎልታ እንድትወጣ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአፍሪካ ላይ የነበረውን አመለካከት መቀየራቸውን ጠቅሰው፤ ለሁሉም ሕዝቦች ስለሚያስፈልገው የተጠና ለውጥና ይህንንም በሚመለከት ሊኖር ስለሚገባው ዓለም ዓቀፍ ኃላፊነት ግንዛቤ እንዲኖር ተከራክረዋል ብለዋል፡፡

እርሳቸውን የመሳሰሉ በርካታ መሪዎች እንደሚያስፈለግ የተገለፀ ሲሆን፤ ሽልማቱን ለአምባሳደር ብርሃኑ ያስረከቡት የዕለቱ የክብር እንግዳና የቡሩንዲ የገንዘብ ሚኒስትር ታቡ አብደላህ ናቸው፡፡

ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በህይወት ዘመናቸው ለኢትዮጵያና ለመላው አፍሪካ ልማትና ዕድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተበረከተ ነው፡፡

የሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ በህሊና ጸሎት፣ በኢትዮጵያ ውዝዋዜና በተለያዩ ዝግጅቶች የታጀበ እንደነበር ኢዜአ ዘግቧል።