ኢትዮጵያ ብዝሃነትን ማስተናገዷ ለእድገቷ መፋጠን ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

  • PDF

ባህርዳር፤ ህዳር 28/2005 (ዋኢማ) ¬- ¬በኢትዮጵያ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት በህገ-መንግስቱ መካተቱ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት መፋጠን የጎላ ድርሻ እንዳለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ገለፁ።

አፈ-ጉባዔው አቶ ካሳ ተክለብርሃን ለሰባተኛ ጊዜ በባህርዳር የሚከበረውን የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን አስመልክቶ በሕገ መንግስቱና ባስገኘው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቶች ዙሪያ በመካሄድ ላይ ባለው ሲምፖዚየም እንደገለፁት፤ በአገሪቱ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ በመፍጠር ዘላቂ የኢኮኖሚና ዴሞክራሲያዊ እድገት ማረጋገጥ ይገባል።

ባለፉት መንግስታት የነበረውን የብሄር ጭቆናና አድሏዊ ስርዓት በማስወገድ በመፈቃቀርና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት አበረታች ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
አቶ ካሳ አያይዘውም መንግስቱና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በሀገሪቱ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማቱ በየዓመቱ ከ11 በመቶ በላይ እድገት ማሰመዝገብ የተቻለ ሲሆን፤ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ስር እየሰደደ መምጣቱን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ህዝቡ መሆኑ በህገ-መንግስቱ በመደንገጉ የመንግስት ስርዓት በህዝብ ይሁንታ ብቻ የሚወሰን በመሆኑ ከጊዜ ወደጊዜ ተቀባይነቱ እያደገ መምጣቱን የተናገሩት አቶ ካሳ የውስጥና የአካባቢ ሰላምን በማስጠበቅ እመርታዊ ለውጥ መመዝገቡንም ገልጸዋል።

የተከፈተው ሲምፖዚየም በህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ የተመዘገቡ አበረታች ለውጦችን በማስታወስ አዲሱ ትውልድ ህገ-መንግስቱ ያስገኛቸው ፋይዳዎችን ለመረዳትና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግ እንደሚያስችል አቶ ካሳ ተክለብርሃን ተናግረዋል።