ሰባተኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በማስመልከት በባህርዳር ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው

  • PDF

ባህርዳር፤ ህዳር 28/2005 (ዋኢማ) - በኢትዮጵያ ህዝቦች ተጋድሎ እውን የሆነው ሕገ መንግስት ሀገሪቱን በጽኑ የኢኮኖሚ ልማት ላይ የተመሰረተ ነፃነት እንዲኖራት ማድረጉን መንግስት ኮሙኒኬሽን አስታወቀ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስኦሞን 7ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በዓል ምክንያት በማድረግ በባህርዳር በመካሄድ ላይ ባለው አውደ ጥናት ላይ እንደገለጹት፤ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ልማት መሰረት በመገንባት ረገድ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ብዙ ርቀት ተጉዛለች፡፡

አቶ በረከት አያይዘውም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ሚሌኒየም በዓል ላይ የሀገሪቱን ታሪካዊ ዳራ በፅናት የቀጠለ ነፃነት፣ ከትልቅ ስልጣኔ ወደ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የተሸጋገረና ብዝሃነትን ማስተናገድ የተሳነው በሚሉ ሶስት ጉዳዮች ከፋፍለው አቅርበው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
አገሪቱ በማስመዝገብ ላይ ያለችው ተከታታይ የኢኮኖሚ  ዕድገት አንዱ ማሳያ አድርገው የጠቀሱ ሲሆን፤ ብዝሃነትን በአግባቡ ከማስተናገድ አኳያም ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ብዙ ርቀት ተጉዘናል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ለዘመናት የቆዩ የማንነትና የእኩልነት ጥያቄዎች በህገ መንግስቱ ምላሽ አግኝተዋል ያሉት አቶ በረከት ይሁንና አሁንም በገጠርና በከተማ የወጣቶችና የሴቶች ተጠቃሚነትን ሙሉ በሙሉ ከማረጋገጥ እንዲሁም ከአርብቶ አደር አካባቢ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስራዎች ረገድ ብዙ መስራት ያለብን ጉዳዮች አሉን ብለዋል፡፡

አዲስቷን ኢትዮጵያ  ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ርብርብ ዳር ለማድረስ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ  አቶ በረከት አሳስበዋል፡፡

የውይይቱ መድረክ ህገ-መንግስቱ ከፀደቀ በኋላ የተገኙ የልማትና የዴሞክራሲ ውጤቶችን፣ ፋይዳቸውንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመለየት ያስችላል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ምክር ቤት አዲሱ አዳራሽ እየተካሄደ ባለው አገር አቀፍ ሲምፖዚየም  “ሕገ መንግስት፣ ዴሞክራሲና ልማት በኢትዮጵያ” የሚል ጥናታዊ ጽሁፍ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ቀርቧል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሰጠና አበረታች የልማትና የዴሞክራሲ ውጤቶችን ያስመዘገበ መሆኑን ዶክተሩ አብራርተዋል፡፡

አገሪቱ ባለፉት 15 አመታት ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎችን መጠን በ15 ነጥብ 9 በመቶ መቀነስ መቻሉን የጠቀሱት ዶክተር አብርሃም ይህም ኢትዮጵያ ድህነትን በግማሽ ለመቀነስ የያዘችውን የምዕተ አመቱን የልማት ግብ እንደምታሳካ አመላካች ነው ብለዋል፡፡
የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋዜጠኛ ያነጋገራቸው አንዳንድ የሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ለአገሪቱ ልማትና ዴሞክራሲ መሰረት የሆነውን ሕገ መንግስት ህብረተሰቡ በሚገባ እንዲያውቀው አውደ ጥናቱ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ በሕገ-መንግስቱ የተገኙ ውጤቶችን ቀጣይ ለማድረግ  በየጊዜው የሚስተዋሉ የአፈፃፀም ችግሮችን ለመፍታት ርብርብ መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡