ለኢኮኖሚው ፈጣን እድገት የንግዱ ማሕበረሰብ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

  • PDF

ባህር ዳር፤ ህዳር 27/2005 (ዋኢማ) - ለፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የንግዱ ማሕበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የአማራ ክልል መስተዳድር አስታወቀ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የእንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ሃለፊ አቶ አህመድ አብተው 7ኛው የብሔሮች፣ ብሐረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ምክንያት በማድረግ በባህርዳር በ ትናትናው ዕለት በተከፈተው የንግድ ትርኢት እንደገለጹት በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል የንግዱ ማሕበረሰብ  ተሳትፎ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው።

የንግድ ትርኢትና ባዛር በከተማዋ ነጋዴዎችና በሌሎች ተሳታፊዎች መካከል የገበያ ትስስርና ትውውቅ እንደሚፈጥር የገለጹት አቶ አህመድ ውድድርን በማጠናከር ጤናማ የገበያ ስርዓት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘውም በአምራችነት የተሰማሩ ባለሃቶች፣ በጥቃቅንና አነስተኛ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችና ሌሎች ድርጅቶች ከነጋዴውና በቀጥታ ከተጠቃሚው ማህበረሰብ ጋር ትስስር መፍጠር የእድገቱን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ያግዛል ብለዋል።

መንግስት ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ህጋዊ የንግድ ስርዓት ለማስፈን እየሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ልማታዊ ባለሃብቱን በማበራከት፣ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በንግድ ትርኢቱና ባዛሩ ከሁሊም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የጥቃቅንና አነስተኻ ተቋማት፣ በልዩ ልዩ የስራ መስክ የተሰማሩ መካከለኛ ከፍተኛ የንግድ ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን በሕዝቦች መካከል አንድነትንና መተሳሰብ እንደሚያጠናክርም በወቅቱ ተገልጿል።

በንግድ ትርኢትና ባዛሩ 102 የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት፣ ከ150 በላይ ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የመጡ የመካከለኛና ከፍተኛ የንግድ ድርጅቶች ከቤት መገልገያ ቁሳቁስ ጀምሮ እስከ መኪና ድረስ በባዛሩ አቅርበዋል።

የንግድ ትርኢትና ባዛሩ በአማራ ክልል ንግድና ትራንስፖርት ቢሮ የተዘጋጀ ሲሆኑ እስከ ታህሳስ 1/2005 ክፍት ሆኖ ይቆያል።