ኢትዮጵያና ጃፓን የ310 ሚሊዮን ብር የድጋፍ ስምምነቶችን ተፈራረሙ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2005(ዋኢማ) - ኢትዮጵያና ጃፓን የ310 ሚሊዮን ብር ሁለት የድጋፍ ስምምነቶችን ተፈራረሙ፡፡

የዕርዳታ ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ሺዴና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሂሮዩኪ ኪሺኖ ናቸው።

ከተፈረሙት ስምምነቶች የመጀመሪያው የ294 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የሚውለው በደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ለሚገነቡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነው።

ሁለተኛው የ16 ሚሊዮን ብር የድጋፍ ስምምነት ደግሞ ከሉማሜ እስከ ደብረማርቆስ ያለውን መንገድ የመልሶ ግንባታ ዲዛይን ለመሥራት ይውላል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ሺዴ እንዳሉት፥  ጃፓን የውጭ ኢንቨስትመንትን በማበረታታትና በትንሽ ወለድ የረጅም ጊዜ ብድር በመስጠት ኢትዮጵያ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናት።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጃፓን የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥልም ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሂሮዩኪ ኪሺኖ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የነደፈችውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ ጃፓን በተለያዩ ክልሎች የምታካሂደውን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ አጠናክራ እንደምትቀጥልና በአገሪቱ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሰማራት ድጋፍ እንደምታደርግ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።