ኢትዮጵያና ኮሪያ ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2005(ዋኢማ)- ኢትዮጵያና የኮሪያ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት የሚያስችል ስምምነት በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ተፈረራረሙ።

ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ሺዴና በኢትዮጵያ የኮሪያ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ኪም ሀዮክ ቾል ናቸው።

ስምምነቱ የተፈረመው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የረጅም ዓመታት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣ የንግድ ልውውጥ፣ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳደግ ነው።

ስምምነቱ የአንዱ አገር ሰው ወይም ድርጅት በሚያገኘው አንድ አይነት ገቢ ላይ በሁለቱ አገራት ተመሳሳይ ግብር መክፈሉ ለካፒታል ፍሰት፣ ለዕቃዎችና በአገልግሎቶች ልውውጥ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ያስቀራል።

ስምምነቱ ተፈፃሚ የሚሆነው በገቢ ላይ በተጣሉ የግብር ዓይነቶች ላይ ብቻ ሲሆን፣ ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶችን የሚያካትት አይደለም።

የስምምነቱ አንቀፆች በየትኛውም የመንግሥት አስተዳደር እርከን ላይ በተጣሉና በሚጣሉ ተመሳሳይ ታክሶች ላይ ተፈፃሚነት እንዲኖረው ተደርጓል።

በሁለቱ አገራት መካከል ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት የተፈረመው ስምምነት ተግባራዊ የሚሆነው በሁለቱ አገራት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ሲጸድቅ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።