የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በወለጋ ዩኒቨርስቲ በድምቀት ተከበረ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2005 (ዋኢማ) - የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በወለጋ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከበረ።

በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሰራተኞች በአሉን ያከበሩት በፓናል ውይይት፣ የተለያዩ አካባቢዎች ባህላዊ ጭፈራ፣ ድራማ፣ ግጥሞችና ሌሎች ዝግጅቶችን በማቅረብ ነው።

የወለጋ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኤባ ሚጄና በፓናል ውይይት ላይ እንደተናገሩት፤ ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔሮች ብሔረሰቦች ቀን የታላቁ መሪ የአቶ መለስ ዜናዊ ራእይን ለማሳካት ቃል በመግባት ነው።

ህዳር 29/1987 የጸደቀዉ ህገ-መንግስት ለብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ካስገኛቸው ዘርፈ ብዙ ድሎች መካከል በቋንቋቸው እንዲማሩና እንዲዳኙ የከፍተኛ ትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደረግት ዋና ዋናዎቹ በመሆናቸው እለቱ ልዩ ግምት ይሰጠዋል ብለዋል።

የብሔሮች ብሔረሰቦች ቀን በህዝቦች መካከል የመቻቻል፣ የመፈቃቀርና የመከባበር ባህልን በማዳበር አንድ የማህበረ-ኢኮኖሚ ስርአት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አስታውቀዋል።

በበአሉ አከባበር ወቅት ብዙም አንድም ሆነን በመለስ ራዕይ በህገ-መንግስታችን በህዳሴያችን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሀገራችን፣ በአህጉራችንና በአለም አቀፍ መድረኮች ገንቢና ታሪካዊ ሚና የተጫወቱ የዘመኑ ታላቅ መሪ የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን በማስተጋባት ለእርሳቸው ያላቸውን አክብሮትና አድናቆት ገልፀዋል።

በዩኒቨርሲቲው የብሔሮች ብሔረሰቦች ማንነት የሚገልፅ የፎቶግራፍ ትርኢት፣ የብሔረሰቦች የባህል ምግቦችና መጠጦችና አልባሳት በኤግዝቢሽን መልክ ቀርበዋል።

በዩንቨርስቲው በህገ-መንግስት በሳይንስና ቴክኖሎጂ የጥያቄና መልስ ውደድር ብልጫ ላመጡ ተማሪዎች ሽልማት መሰጠቱን ኢዜአ ዘገባ ያስረዳል።