አህጉር አቀፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የእርስ በርስ የግብርና ንግድን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2005 (ዋኢማ) ¬ በአፍሪካ በግብርናው ዘርፍ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣትና አህጉር አቀፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የእርስ በርስ የግብርና ንግድን ማጠናከር እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ፡፡

የግብርናና የንግድ ሚኒስትሮች የጋራ ጉባኤ በአፍሪካ ህብረት እየተካሄደ ነው፡፡ ያለፉት የአፍሪካ ህብረት ሁለት ጉባዔዎች ዋነኛ አጀንዳቸውን ያደረጉት የአህጉሪቱን የእርስ በእርስ ንግድ ማስተሳሰርን ነበር፡፡

የአፍሪካ ሀገራት የሚያደርጉት የእርስ በርስ ንግድ ልውውጥ 10 በመቶ ነው፡፡ የአውሮፓ 77 በመቶ ሲሆን የእሲያ ደግሞ ከ59 በመቶ በላይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የአፍሪካውያኑ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

የአህጉሪቱ የመሠረተ ልማት ትስስር ደካማ መሆን በሀገራት መካከል ያለ የምርት ስብጥር አለመመጣጠንና ቀረጥ ደግሞ ለእርስ በርስ ንግዱ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ህብረቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 ነፃ የገበያ ቀጠናን ለመመስረት ላስቀመጠው እቅድ ስኬታማነት ትልቅ ፈተና ሆነዋል፡፡

ከ80 በመቶ በላይ ኢኮኖሚዋ በግብርና ላይ በተመሰረተው አፍሪካ እንደ ኢትዮጵያ ፈጣን የግብርና እድገት እያስመዘገቡ ያሉ ሀገራት የምግብ ዋስትናቸውን በማረጋገጥ የእርስ በርስ ንግዱን የማጠናከር ቀዳሚ ተስፋ ያላቸው ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የግብርናና የንግድ ሚኒስትሮች የጋራ ጉባዔም የአህጉሪቱን የንግድ ትስስር በማጠናከር የግብርና ምርት እድገትን በማጠናከር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥን አላማ ያደረገ ነው፡፡

የህብረቱ ምክትል ኮሚሽነር ኢራስተስ ምዌንቻ እንደተናገሩት የአፍሪካን ድህነት ለመቅረፍ በሶስት ጉዳዮች ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡ “መጀመሪያ የአህጉሪቱ ሀገራት መቀራረብ አለባቸው፤ ይህም ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ከዚያም በጋራ መስራት ከተቻለ በርግጥም ለውጥ ይመጣል፡፡” ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሩ፡፡

የኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ወንድራድ ማንደፍሮ በበኩላቸው ባለአነስተኛ ማሣውን አርሶ አደር ምርታማነት ማሳደግና የግብይት ስርዓት መዘርጋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መንግስት የሚያከናውናቸው ቁልፍ ተግባራት ናቸው በለዋል፡፡ በተለይ በገበያ ተኮር ምርቶች ላይ አርሶ አደሩ ትኩረት እያደረገ መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡ “የኢትዮጵያ መንግስት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር የሆኑ ምርቶች እንዲያመርት ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡ ለዚህም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች እያቀረበ ነው፡፡”

እንደ ኢሬቴድ ዘገባ የአፍሪካን የገበያ ክፍተት ለመሙላት ሀገራት የምግብ ሸቀጦችን ከውጪ ከማስገባት ይልቅ በሀገር ውስጥ ምርታማነትን በማሳደግ ላይ ትኩረት እንዲደርጉ ማስቻል በአፍሪካ ህብረት የተካሄደው ጉባዔ ዋነኛ ማጠንጠኛ ነው፡፡