መጪው ምርጫና የፖለቲካ ምህዳሩ

  • PDF

ይሄይስ ፍፁም
በያዝነው 2005 ዓ.ም ሚያዚያ ወር የሚከናወነውን የአካባቢና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ ከወዲሁ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከቅድመ ዝግጅቶች መካከል የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች እየሰጠ የሚገኘው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተጠቃሽ ነው፡፡

ስልጠናው ፓርቲዎቹ ያላቸውን ተሳትፎ ከግምት ያስገባ ሲሆን፤ አዳዲሰ ፓርቲዎች ያላቸውን የተሞክሮ እጥረት መቅረፍ በሚያስችላቸው መልኩ ለማስቻል እንዲሁም ነባሮቹ ደግሞ ወቅታዊ እና ነባራዊ ሁኔታውን አውቀው እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል፡፡ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ ብሎም ተዓማኒ እንዲሆን መራጩ ህዝብ እና በምርጫው ተሳታፊ የሚሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እኩል ኃላፊነት እንዳለባቸው እሙን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ዛሬ የመረጥነው ነገ የተሻለ ለውጥ ያመጣልኛል ብለው ያመኑበትን ፓርቲ መምረጥ መቻላቸው ማንም የሰጠታቸው መብት ሳይሆን ህገ - መንግስቱ ያጎናጸፋቸው መሆኑ ሁሉም ይስማማበታል፡፡  የሀገራችን ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነታቸውን ተነጥቀው ያለ ዴሞክራሲ መቆየታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

እነዚህ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  በአንድ አሃዳዊ አገዛዝ ታፍነው በቋንቋቸው እንዳይጠቀሙ እንዲሁም ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን  እንዳያውቁ ተደርገዋል፡፡ ግና ይህ አስከፊ የታሪክ ምዕራፍ ዛሬ ላይ የለም፡፡ ይልቁንም ህዝቦች በታሪካቸው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም በምርጫ ተሳታፊ ሆነው የስልጣን ባለቤት መሆን ከጀመሩ 21 ዓመታትን ተሻግረዋል፡፡ እናም የስልጣን ባለቤት ያደረጋቸው እና ለዚሁ ምዕራፍ ያበቋዋቸው ውድ የህዝብ ልጆች ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፍቃዳቸው ባጸደቁት ህገ - መንግስት መሰረት አራት ሀገራዊ ምርጫዎች፣ ሶስት የአካባቢ እና በርካታ የማሟያ ምርጫዎች መከናወናቸው ይታወሳል፡፡ በእነዚህ ምርጫዎች መራጩ ህዝብና የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች የተጫወቱት ሚና በሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት መጎልበት እና አሁን ለደረሰበት ደረጃ መብቃት የነበራቸው ድርሻ የላቀ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡

ቀደም ሲል የተከናወኑት እነዚህ ምርጫዎች ጠቅለል ባለ መልኩ የራሳቸውን ታሪካዊ አሻራዎች ጥለው ማለፋቸው ግልጽ ነው፡፡ ዘንድሮ በሚያዚያ ወር የሚከናወነው የአካባቢ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫም ህዝቡ ይበጀኛል ያላቸውን በመምረጥ ቀጣዩን የሀገራችንን የህዳሴ ጉዞ በማረጋገጡ ሂደት የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት መዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡

በምርጫ 2005 መራጩ የህዝብ ያለው ወሳኝ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ገዢው ፓርቲ  እና ተቃዋሚ ኃይሎችም ምርጫውን ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና ነጻ በማድረግ በኩል ሊጫወቱት የሚገባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ የሀገራችን ፖለቲካ ምክንያታዊ ካልሆነ እና ከጭፍን ጥላቻ ካልወጣ ብሎም ሰላማዊ የሆነ ፖለቲካዊ ሂደት ካልተፈጠረ፣ በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ እንደሚታወቀው ቀደም ሲል በሀገራችን የነበረው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ በተወሰኑ ጭፍን የፖለቲካ አራማጅ ወገኖች እየተንፀባረቀ ያለው የጥላቻ ፖለቲካ  የሀገሪቱን የሠላም እና የልማት ውጥን ከማደናቀፍ ውጪ የሚፈይደው አንዳችም ነገር የለም፡፡

ሀገር የጋራ ነው። ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በሀገር ጉዳይ እኩል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት እናሳድግ ሲባልም የኢትዮጵያ ህዝቦች እና በምርጫው ተሳታፊ በመሆን በምረጡኝ ዘመቻ የሚሳተፉ  የፖለቲካ ኃይሎችም ህገ- መንግስታዊ አና ሀገራዊ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሀገር እና የሀገር ፍቅር ያለው ትርጉም ከቃሉ የዘለለ ጥልቅ ትንታኔ ሊሰጥ የሚችልበት ጉዳይ ነው፡፡ እውነት አንድ ዜጋ ሀገሩን የሚወድ ከሆነ፤ ለሀገሩ ሠላም እና መረጋጋት ጸንቶ መታገል እና ሌላውም እንደሱ እንዲታገል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ እውነት አንድ ዜጋ ሀገሩን የሚወድ ከሆነ ለሀገሩ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ እውነት አንድ ዜጋ ሀገሩን የሚወድ ከሆነ ሀገሩ በምትገነባው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዕድገት ላይ የራሱን አሻራ ማኖርም ግድ ይለዋል፡፡

በአንዲት ሀገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በሚደረገው ጥረት ዜጎች እና በሀገሪቱ ያሉ መላው የፖለቲካ ድርጅቶች የሚጫወቱት ሚና የላቀ ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውን በማጎልበት ረገድ ዜጎች የስልጣን ባለቤትነታቸው የሚያረጋገጡበት የምርጫ ሂደት ወሳኝ ነው፡፡

ህዝቦች የሚያከናውኑት የምርጫ ሂደትም ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና እንከን የለሽ መሆንም አለበት፡፡ የምርጫው ዴሞክራሲያዊነትም በዜጎች እና በተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች እጅ ይገኛል፡፡ ይህ ሲባል በእኩል የሂሳብ ስሌት ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች አንድ ሀገር ለምታከናውነው ነጻ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ኃላፊነት አለባቸው ማለት ነው፡፡

ቀደም ሲል በሀገራችን የተከናወኑትን የምርጫ ሂደቶች ብንመለከት በየወቅቱ በምርጫ የሚሳተፉ የመራጩ ህዝብ ቁጥር ተሳትፎ ብሎም የፖለቲካ ድርጅቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ ዕድገቱ በቁጥር ብቻ ሳይሆን፤ ዜጎች ከዴሞክራሲ የሚያገኙት ጠቀሜታ የላቀ በመሆኑ ግንዛቤያቸውን እያደገ መጥቷል። ለምርጫ ያላቸውም አስተሳሰብም ጎልብቷል፡፡ በሀገራችን ባለፉት አራት ጊዜያት የተከናወኑ የምርጫ ሂደቶችም ከላይ የጠቀስናቸው ሁኔታዎችን ያሟሉ ነበር ቢባል ይህን ሃቅ የሚያጠናክር ነው፡፡

እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ የሀገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዕድሜ በዴሞክራሲ ከዳበሩ ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር ከአስር እጥፍ በላይ የሚያንስ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓትና ባህል ግንባታ ዕድገት ከዕድሜው አኳያ ፍጹም ዳብሯል ባይባልም፤ ካስቆጠረው ዕድሜ አኳያ ግን አበረታች ውጤት የተገኘበት ነው፡፡

ይህ ሲባል ግን ሀገራችን ገና ዴሞክራሲ እየገነባች ያለች ሀገር እንደመሆኗ መጠን የፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫ ያላቸው እሳቤ ያን ያህል ያልጎለበተ በመሆኑ የተወዳዳሪ ፓርቲዎች አቅም ያለ ማደግ ይታያል— በተለይም በተቃዋሚው ጎራ። ይህንንም ባለፉት አራት የምርጫ ሂደቶች እያየነው መጥተናል፡፡

እነዚህ ችግሮች በታዳጊ ዴሞክራሲ ሀገሮች ውስጥ የሚያጋጥም ነባራዊ ሁኔታ ቢሆኑም፤ ሁኔታውን በማሻሻሉ ረገድ የፖለቲካ ድርጅቶች አስተሳሰብ መለወጥ እና ማደግ አለበት፡፡
እርግጥ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በምርጫ የሚያደርገው ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን አሽንፎ ስልጣን ላይ ለመውጣት እንደሆነ ማንም ይገነዘበዋል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች መሰረት የሌለው ምክንያቶችን ከምስጢር ኪሳቸው እያወጡ ከምርጫው እራሳቸውን ለማግለል የተለያዩ መሰረተ-ቢስ ሃሳቦችን ሲያነሱ ይስተዋላል። ከእነዚህ ሰበቦች መካከል የሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ጠቧል የሚል ሰንካላ አመክንዩ ይገኝበታል፡፡

በ2005 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ላይ ለሚከናወነው የአካባቢ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤቶች ምርጫ ለመሳተፍ አንዳንድ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጀቶችና የፖለቲካ ምህዳር ጠቧል እያሉ ነው፡፡ በምርጫ አንሳተፍም የሚል መሰረት የለሽ ምክንያቶችንም በጭፍን ይደረድራሉ፡፡ ፓርቲዎቹ ይህን ውሃ የማይቋጥርና ሚዛን የማይደፋ አስተሳሰብ ለማንሳት የሚሹበት ዋነኛው ምክንያት አሁን የሚገኙበት ዝቅተኛ የተወዳዳሪነት ደረጃ መሆናቸውን በማወቃቸው ነው።
የምህዳር መጥበብ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚያነሱ እነዚሁ ፓርቲዎች ተቃውሞቸውን ያለአንዳች ሃፍረት እየሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ የመከራከሪያ ነጥባቸው ምን ያህል እውነት ያዘለ ነው ለሚለው ጉዳይ ራሳቸውም ቢሆኑ አያውቁትም-ፍላጎታቸው የጭፍን ፖለቲካን ማራመድ ነውና፡፡ ለምን ቢባል የእነዚህ ፓርቲዎች የመከራከሪያ ነጥብ ምን ያህል ሚዛን ደፍቷል ተብሎ ቢጠየቅ ድንብርብራቸው ስለሚወጣ ነው፡፡

በሚያዚያ ወር የሚከናወነው የአካባቢ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤቶች ምርጫ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ገና ከወዲሁ ሰበብ መደርደራቸው እና ማብዛታቸው በምርጫው ውስጥ ተፎካካሪ ሆነው ለመቅረብ ያላቸውን ድክመት ለመሸፈን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ፍትሃዊ፣ ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ተገቢ ዝጅት እና ለምርጫው አስፈላጊ ነው የሚባለው የስልጠና ክትትል እየሰጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት በመድረክ አጫፋሪነት የሚመሩ ፓርቲዎች የምህዳሩ ጠቧል ሰበብን እያነሱ ከምርጫ ራሳቸውን ለማግለል መግለጫዎች መስጠታቸው ለመራጩ ህዝብ ያላቸውን ንቀት ያሳያል፡፡

ባለፉት ጊዜያት በሀገራችን የተከናወኑ የምርጫ ሂደቶች በተጨባጭ የተመለከትን እንደሆነ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መንግስት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ ገዢው ፓርቲ ሀገራችን የምትመራባቸው ህጎች ዴሞክራሲያዊ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲተገበር ሰፋፊ የግንዛቤ መድረኮችን አዘጋጅቶ ገቢራዊ አድርጓል፡፡ ይህ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያትም መንግስት እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች አንድ የዴሞክራሲ ተቋም እንደሆኑ ካለው ቁርጠኝነት በመነሳት ነው፡፡

ውድ አንባቢዎቼ “የምርጫ ትርጉም ምንድነው?” ቢባል፤ የህዝቡን የስልጣን ባለቤትነት ማረጋገጥ መሆኑ ከማናችንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በመሆኑም የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸው ኃይሎች ለህዝቡ ይበጃል የሚሉትን የአማራጭ ሃሳቦች በማፍለቅ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆነው በምክር ቤት ወንበር ለማግኘት ከመጣር ይልቅ፤ መሰረተ የሌለው ምክንያት እያነሱ ከምርጫው ራሳቸውን ማግለል ለሀገር እና ለህዝብ ምን የሚፈይደው ጉዳይ አይኖርም፡፡

እናም እነዚህ “በየትም ፍጪው ስልጣኑን አምጪው” የዜሮ ድምር ፖለቲካ አራማጅ የከሰሩ ፖለቲከኞች ምህዳሩ ጠቧል በሚል ሰበብ ራሳቸውን ከምርጫው ለማራቅ ማሰባቸው፤ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ይበልጥ ከህዝቡ ሊነጠሉ እንደሚያደርጋቸው ያወቁት አይመስለኝም፡፡

ሀገር እና ህዝብ ለመምራት የተዘጋጀ አንድ የምርጫ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅት ትግሉን ማከናወን ያለበት መሰረት ባለው እና እውነትን በያዘ ሁኔታ እንጂ አሳማኝ ባልሆነ አሉባልታ መሆን የለበትም፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደራጁበት ዋነኛ ዓላማ በምርጫው ተሳታፊ ለመሆን ብቻ አይደለም። ይልቁንም ብርቱ ተፎካካሪ ሆነው በማሸነፍ መራጩ ህዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ነው፡፡ ታዲያ ለዚህ ዴሞክራሲያዊ ተግባር ፓርቲዎቹ ያላቸውን ፕሮግራሞች ለህዝቡ በግልፅ በማቅረብ የምርጫ ሂደቱን በሚገባ መጠቀም ይገባቸዋል፡፡
በመድረክ ጋሻ ጃግሬነት ከመሰንበቻው የሚካሄደው “ጉሮ ወሸባዬ” ግን በምርጫው ላለመሳተፍ የምህዳር ጠብቧል መሰረት የለሽ ምክንያት ከዕቃ ዕቃ ጨዋታነት የሚዘል አይመስለኝም። ድርጊቱ በመራጩ ህዝብ ማሾፍ ነውና  ሁሉም ፓርቲዎች መራጩ ህዝብ የሚቀበለውን እና የሚደግፈውን አስተሳሰብ በማፍለቅ በምርጫ አሸናፊ ለመሆን ከመጣር ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡
ይህን በተመለከተም  በኢፌዴሪ ህገ - መንግስት አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀጽ ሶስት ላይ በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ለኃላፊነት ቦታዎች የሚካሄዱ ምርጫዎች ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፈጸም እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  ጽህፈት ቤት የተመዘገቡ እና ዕውቅና የተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች 75 ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 55ቱ በክልል ደረጃ የሚወዳደሩ ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ናቸው፡፡

የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በሀገራችን ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተግባራዊ እየሆነ መጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦችም የተሰጣቸውን ህገ-መንግስታዊ መብት ተጠቅመው  የስልጣን ባለቤትነታቸውን በሚገባ ተግብረዋል፡፡ ባለፉት 21 ዓመታት የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማጠናከር በተደረገው ጥረት፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና መላው ህዝብ ያሳየው ርብርብ የማይናወጥ መሰረት ጥሎ ዛሬ ላይ አድርሶናል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚቻለው በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲኖሩ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህም የፖለቲካ ኃይሎች በሚያፈልቋቸው መሰረታዊ ሃሳቦች እየተመረኮዙ ህዝቡ ይበጀናል የሚለውን ለመምረጥ እንዲያስችለው ያደርጋል፡፡ ታዲያ እነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች  የሀገራችን ህገ - መንግስት በሚፈቅደው መሰረት በመደራጀት አጀንዳቸውን ለህዝቡ ዴሞክራሲያዊ በሆነና በሰለጠነ አካሄድ  ይፋ በማድረግ መመረጥ የሚችሉበትን አሰራር መከተል የጠነከረ የዴሞክራሲ  ባህልን ማዳበር ነው፡፡

ዳሩ ግን  ማንኛውም ፓርቲ በአካባቢ እና በአዲስ አበባ ምክር ቤቶች ምርጫ ውስጥ ወንበር አግኝቶ ድምፁን ማሰማት የራሱ፣ የፓርቲውም ሆነ የደጋፊው ፍላጎት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው፡፡ ምክንያቱም በተሻለ መልኩ በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት ለህገ-መንግስቱ ታማኝ በመሆን የጠራ መስመር የማስተዋወቅ፣  የመናገር፣ ተናግሮ የማሳመን እና ላቅ ያለ አስተሳሰብ የማፍለቅ አቅም ያለው ፓርቲ፤ በዚያኑ ልክ የመደመጥ እና የመመረጥ ዕድሉ የሰፋ እንደሆነ በተጨባጭ ካለፉት ጊዜያት ከተከናወኑ ምርጫዎቸ መገንዘብ ይቻላል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ-መንግስቱን የሚረግጡ፣ትክክለኛና ሰላማዊ የሆነ የምረጡኝ ዘመቻ ወደ ጎን በመተው ህዝብን በማደናገር ተግባር ላይ የሚሰለፉ ከሆነ ግን ለውድቀት መዳረጋቸው አይቀሬ ነው፡፡ ባለፉት ምርጫዎችም ይህን መንገድ የተከተሉ ኃይሎች ዕጣ ፈንታቸው የነበረው ይሄው እንደነበር ታሪክ ያስውሰናል።

መቃወም ሲባል ተቃዋሚዎቻችን እንደሚያራግቡት የተሰራና እየተሰራ ያለውን ፍፁም ሃቅ ሽምጥጥ አድርጎ መካድ ሳይሆን፤ ጭፍን የፖለቲካ አካሄድ ወደ ጎን በመተውና ሃቁን በማስቀመጥ በክርክር አሸናፊ ለመሆን መጣር ተመራጭ ነው፡፡ ይህም ሲባል የሀገሪቱን ህገ - መንግስት ተከትሎ ከመስራት እና ለህዝቡ የተሻለ አስተሳሰብ አቅርቦ መመረጥ የላቀ ይሆናል ማለት ነው። እናም ትርጉም የለሽ እና መሰረት የሌለውን የጥላቻ ስሜት በማንጸባረቅ የሚደረግ የምረጡኝ ዘመቻ ህሊና ከማቆሸሽ ውጪ ለሀገር እና ለህዝብ የሚፈይደው ነገር የሌለ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡
በመጪው ሚያዚያ የሚከናወነው የአካባቢ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤቶች ምርጫ የሴቶችን እና የወጣቶችን አደረጃጀቶች በማስፋት ተሳታፊነታቸው በማረጋገጥ በኩል ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም ይጠበቃል፡፡ ካለፉት ጊዜያት በተለየ መልኩ ይህን ምርጫ የተሻለ ለማድረግ እንቅስቃሴው ቀጥሏል፡፡

የዘንድሮው ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች ለየት ከሚያደርጉት አንዱ ነጥብ የመራጩ መዝገብና ካርድ የተዘጋጀበት ሂደት ነው፡፡ ይኸውም ህብረተሰቡ በሚገባው ቋንቋን አንብቦ ለመረዳት አማርኛ ቋንቋ ብቻ ስራ ላይ መዋሉ የሚታወስ ሲሆን፤ ዘንድሮ ግን ህብረተሰቡ በሚገባው ቋንቋ መጠቀም እንዲችል የምርጫ ካርዶችን በአምስት ቋንቋዎች እንዲዘጋጁ ተደርጓል፡፡
ይህም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰነዶችን የማዘጋጀት እና አትሞ የማውጣት  አቅሙን በማሳደግ በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በኦሮምኛ፣  በአፋርኛ እና በሶማሊኛ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ሰነዶችን አዘጋጅቷል፡፡ ከሰነዶቹ በተጨማሪ በምርጫ ወቅት ሊነሱ የሚችሉ ቅሬታዎች በምን መልኩ መፈታት እንዳለባቸው የሚያመላክቱ ቅድመ- ስልጠናዎች እና ዝግጅቶችም እየተጠናቀቁ ነው፡፡

ለምርጫው በወጣ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የእጩዎች እና የመራጮች ምዝገባ ከታህሳስ 22 እስከ ጥር 21 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ይከናወናል፡፡ ሚያዝያ 6 ቀን 2005 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ ድምጽ ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በአካባቢ ምርጫ የወረዳ፣ የቀበሌ፣ የማዘጋጃ ቤት፣ የከተማ አስተዳደር እና የዞን ምክር ቤቶች አባላትም ይመረጣሉ፡፡
በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እያበበ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ በየወቅቱ የሚፈጠሩ መልካም ዕድሎችን መጠቀም ብልህነት ነው፡፡ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የበለጠ የመደመጥና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት አጋጣሚ ያለው በደረጃው በሚገኙ ምክር ቤቶች ውስጥ ወንበር ያለው ፓርቲ ነው፡፡ ስለዚህ ፓርቲዎች ቦርዱ ባወጣው የምርጫ አፈጻጸም የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማከናወን የሚገባቸውን ሁሉ ማድረግ ብስለት ሲሆን፤ ከስልጠና፣ ከገንዘብና ከመገናኛ ብዙሃን ጀምሮ ያሉትን የተመቻቹ ዕድሎችም በመጠቀምም በምርጫው ንቁ ተሳታፊ መሆን ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ እንዲያብብ የበኩላቸውን ሚና መወጣት መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡

ዜጎች በአንድ በኩል በሚያምኑበት የፖለቲካ ድርጅት የመሳተፍ መብታቸው  ተከብሮላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሚመራቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች ስልጣን የመስጠትና በትክክል አይሰራልንም የሚሉትንም የማስወገድ የፖለቲካ ስልጣን አካሄድ ተጎናጽፈዋል፡፡ ይህን ህገ-መንግስታዊ መብት ማንም አይነጥቃቸውም፡፡ የሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት መገለጫም ይኸው ነውና፡፡
ስለሆነም ዜጎች ድምጽ የመስጠት ህገ - መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም በአንድ በኩል የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ለማጠናከርና ውጥን  የሠላም እና የልማት ስራዎችን ከግብ ለማድረስ እንዲሁም የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማሳደግ በምርጫው ንቁ  ተሳታፊ መሆን ይገባናል፡፡

ምርጫውን ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ተዓማኒ እና እንከን የለሽ ለማድረግም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን የምርጫ ስርዓት ተከትለው የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲያብብ እና የሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ይበልጥ ለማስፋት የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ የተቃውሞው ጎራም መሠረት የሌለው ምህዳር ጠብቧል ወደ ጎን በመተው ማንነታቸውን በመፈተሽ በተለይም የሚወዳደሩበትን ህገ - መንግስታዊ ስርዓትም ይሁን ህገ-መንግስቱን በማክበር በምርጫው ሊሳተፉ ይገባል። አሊያ ግን እንዳለፉት ጊዜያት በህዝቡ ካርድ “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ…” ተብለው እንደሚወረወሩ ማወቅ ይኖርባቸዋል—“ዳኛውም ፈራጁም ህዝቡ ነው” እንዳሉት ታላቁ መሪያችን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ። ቸር እንሰንብት።