እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን

  • PDF

ሚካኤል ተፈሪ

አንገትን የሚያስደፋው የቀኑ ፀሐይ አልፎ ሙቀትና ነፋሻማ አየር ቦታውን ለቋል፡፡ ከሩቅ እዚህም እዚያም በቡድን በቡድን እየሆነ የተለያዩ አጀንዳዎችን እያነሳ የሚጥል በመቶዎች የሚቆጠር ሰራተኛ ይታየኛል።

የጥበብ ሰዎች አዳራሽ ለወትሮው ሰዎች ሲሰበሰቡበት ውቅያኖስ መሀከል ለብቻዋ የምትንሳፈፍ መርከብ ያህል የሚያሳየው አዳራሽ ዛሬ ከጥግ ጥግ በሰራተኛው ተሞልቶ ሲታይ እንዲህ ነኝ እኔ የሚል ይመስላል።

ስብሰባ ስሙ ራሱ ሲጠራ ያመኛል፤ ድንች ለመግዛት ስብሰባ፣ ደን ለመትከል ስብሰባ፣ ቅርጫ ስጋ ለመከፋፈል ስብሰባ፣ ለልጆች ልብስ ለማሰፋት ስብሰባ ረ ስንቱ ብጠራም ባልጠራም እንደማልሳተፍ የታወቀ ነው።

የዛሬው ስብሰባ ግን ለየት ይላል የራሴ ጉዳይ፣ የልጆቼ ጉዳይ፣ የልጅ ልጆቼ ጉዳይ፣ የአገሬ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከማንም ቀድሜ የፊት ለፊቱን ወንበር በመያዝ የስብሰባውን መጀመር ስጠባበቅ የነበረው።

አጠርና ፈርጠም ያሉት ሚኒስትር የሰራተኛውን በሰዓቱ መገኘት ተከትሎ ነው መድረኩ ላይ ጉብ ያሉት። ሰራተኛው እንግሊዙ ይላቸዋል፤ ሰው ቢጠሉም፣ ቢወዱም፣ ቢናደዱም፣ ቢደሰቱም ፊታቸው ላይ የተለየ ነገር አይነበብም፡፡

በእውቀት ላይ የተመሰረተ አመራር ስለሚሰጡ፣ ሰራተኛውን ባገኙት አጋጣሚ ስለሚያበረታቱ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኛ ይወዳቸዋል። ለዚህም ነው በተከታታይ ዓመታት መስሪያ ቤቱ በሚያስመዘግበው ውጤት ለሽልማት የሚበቃው።

ወደ ዛሬው ስብሰባ ልመለስና የታዘብኩትን አንዳንድ ነገሮች ጣል ላድርግ። አስተባባሪ ኮሚቴው ቀድሞ አጀንዳውን አሳውቆ ነበርና ሰራተኛው በሚገባ ተነጋግሮና ተዘጋጅቶ ነው የመጣው፡፡ አጀንዳው የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ነው፡፡

የመስሪያ ቤቱ ሰራተኛ ታጋይ መለስ ዜናዊ የህዳሴውን ግድብ መጀመር ባበሰሩበት ወቅት የተናገሯትን ንግግር ተከትሎ ማንም ሳይቀድመው ነበር የወር ደመወዙን በዓመት ለመክፈል ቃል የገባው ።

‘‘…ለህዳሴው ግድብ መሀንዲሱ እኛው፣ ቀያሹ እኛው፣ ጠባቂው እኛው፣ የገንዘብ ምንጩ እኛው’’ ያሏትን ቃል ተቀብሎ ነው የተንቀሳቀሰው፡፡ የመጀመሪያውን ዓመት ክፍያ በማጠናቀቅ ቦንዱን ተረክቧል።

ለሁለተኛ ዙር ቃል የሚገባበትን ሰነድ እየተጠባበቀ ነው፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ አዳራሹ በሰራተኞች ተሞልቶ መተንፈሻ እስኪቸግር ድረስ በቦታው በመገኘት የስርዓቱ ተካፋይ የሆነው።

ሚኒስትሩ ከመቀመጫቸው በመነሳት ነው በምስጋና ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡ ቀጥለውም ስለህዳሴው ግድብ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም፤ አገሪቱ በአካባቢው የሚኖራትን ተቀባይነትና ከፍ ያለ ቦታ በመግለፅ በቀጣይ ሰራተኛው የሚጠበቅበትን አገራዊ ኃላፊነት እንዴት ሊወጣ እንደሚችል ጠቆም በማድረግ ነው ለሰራተኛው እድሉን የሰጡት።

ሰራተኛው አንድ በአንድ እየተነሳ ለህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ እስከመጨረሻው ድረስ ባለው አቅም እንደሚረባረብ ሃሳቡን ገለፀ። በስተመጨረሻ አንድ እጅ ከወደ ኋላ ተቀስራ ታየች፡፡ የሶቅራጥስ እጅ ነው፡፡

ሶቅራጥስ ምክንያታዊ ነው፤ የተነገረውን ሁሉ አሜን ብሎ አይቀበልም፤ መረዳት ይፈልጋል፤ የራሱንም ሃሳብ በማከል ያዳብረዋል፤ አንዳንዴም ይፈላሰፋል፤ ለዚህ ነው ጓደኞቹ ሶቅራጥስ ያሉት፡፡

ሁሉም ሰራተኛ ድምፁን ሲሰማ ምን ሊናገር ይሆን? በማለት ነበር በጉጉት የጠበቀው፡፡ የመናገር ዕድሉን በማግኘቱ አመስገኖ ወደ ዋናው ቁም ነገር ገባ።

የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ በመሰረተ ሃሳቡ እስማማለሁ፤ አካሄዱ ላይ ግን ቅሬታ አለኝ፤ አባይ የዘመናት ጥያቄያችን፣ የፀፀታችንና የቁጭታችን ምንጭ ሆኖ እንደኖረ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አይክደውም።

እስካለፈው ዓመት ድረስም በየጊዜው የነገሱ፣ ኢትዮጵያን የመሩና ያስተዳደሩ መሪዎቻችንንና እኛንም ተመሪ ህዝቦችን አንበርክኮ በማሸነፍ ለፈለገው ህዝብና አገር ጥሪታችንን አሟጦ በመዝረፍ

አስረክቧል። ሃያልነቱን በግልፅ አሳይቶናል። ገዝቶናል ኢትዮጵያ አገራችን ጥንት ጨለማው ተገፎ ብርሃን ባልተገለጠበት ዘመን እንኳን ሃብቷን ሊዘርፉ፣ ህዝቧን በቅኝ ሊገዙ፣ በየጊዜው የተነሱባትን ጠላቶቿን አንበርክካ የሃፍረት ሸማ አከናንባ መሸኘቷ እውነት ነው፡፡ ብርሃን ነው፤ የማይሸፈንና የማይካድ የማይደበዝዝ ሀቅ፡፡

ዓባይ ግን፣ ዓባይ ግን፣ ዓባይ ግን፣ አንበርክኮን ነው የኖረው፤ እያስፈራራን፣ ሲያሰኘው እየፎከረብን፣ እያሸማቀቀን፣ ሀብታችንን ሲዘርፍ ነው የኖረው፡፡ ድህነታችንን፣ ኋላቀርነታችንን፣ መከፋፈላችንን ሲገልፅልን ነው የኖረው፡፡

ባለፈው ዓመት ግን በባለራዕዩ መሪና በሚመሩት መንግስትና ድርጅት እንዲሁም በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቆራጥነትና አንድነት ለመንበርከክ በቃ፤ ድል ተነሳ፡፡ ሰራተኛው አላስጨረሰውም አዳራሹን በጭብጨባና በእልልታ አናጋው።

ሶቅራጥስ ቀጠለ፡- የህዳሴው ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ስራ ነው፤ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፤ ጀምረነዋል፤ አሁንም ሰራተኛው በመሀል ገብቶ ‘እንጨርሰዋለን’ በማለት ሲቃ እየተናነቀው ቃል ገባ፡፡

ሶቅራጥስ አሁንም ቀጠለ፡- የህዳሴውን ግድብ በየቀኑ እንደምንመገበው፣ እንደምንጠጣው፣ እንደምንተነፍሰው ያህል እንከታተለዋለን፡፡ የህዳሴው ግድብ ደማችን ነው፤ ሰራተኛው በመሃል ገብቶ ‘አጥንታችን ነው፣ ስጋ እናለብሰዋለን፣ እንዳይበርደው ሸማ እናከናንበዋለን’ በማለት አስተጋባ፡፡

በመሆኑም ስለህዳሴው ግድብ እኛን በልጦ የሚያብራራልን አካል አንፈልግም፤ ጀምረነዋል እንጨርሰዋለን ከመንግስት የምንፈልገው ዓመቱ ሲያልቅ ወይም ተጨማሪ ገንዘብ ሲያስፈልግ ቃል የምንገባበትን ሁኔታ እንዲያመቻችልን ብቻ ነው፤ ከዚህ ውጭ ደራሲም ተደራሲም እኛው ነን፡፡ በአካሄዱ ላይ አልስማማም ያልኩትም ከዚህ የተነሳ ነው፤ በዓባይ ጉዳይ የበላይና የበታች የለም፤ ሁላችንም የበላይ ነን፤ የሁላችንም ደም አንድ ነው፤ አብረን ቁመናል አብረን እየተራመድን ነው፤ ማንም ኢትዮጵያዊ ከሰልፉ ይወጣል ወደ ኋላ ይቀራል ብለን አናስብም፣ አንገምትም፤ እንደጀመርን እንጨርሰዋለን በማለት በጭብጨባ ታጅቦ ንግግሩን ቋጨ፡፡ የእለቱ ስብሰባም ‘‘እንደጀመርን እኛው እንጨርሰዋለን’’ የሚለውን የሰራተኛውን ቃል ተከትሎ ተጠናቀቀ።

ከዚህ ስብሰባ ብዙ ነገር ተምሬ ነው የወጣሁት፡፡ አንድነትን፣ ተነሳሽነትን፣ ቁርጠኝነትን፣ የዓላማ ፅናትን፡፡ ሶቅራጥስ እንዳለው የሰለጠነ፣ አለ የተባለ፣ የዘመኑን የጦር መሳሪያ የታጠቀ፣ ለረዥም ዓመታት አቅዶ የተዘጋጀና የተደራጀ የጠላት ሰራዊት አርበድብዶና አንገት አስደፍቶ ያለፈው ትውልድ የተሸነፈው በሁለት ነገር ብቻ ነው። በዓባይና በድህነት።

አፈሩን ያቅልላቸውና በባለራዕዩ መሪ መለስ ዜናዊና በሚመሩት ፓርቲና መንግስት ፊታውራሪነት በሁለቱም ላይ ጦርነት አውጀን ቆሌያቸውን ገፈናል፤ አንገታቸውን አስደፍተናል፤ ምሽጎቻቸውን ንደናል፤ ከአሁን በኋላ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ የሚመለከት ጭንቅላትም ሆነ ህዝብ የለም።

የህዳሴው ግድብ አገሪቱ ማንንም ሳትጎዳ በራሷ ሃብት የመጠቀም መብት እንዳላት ለዓለም ያሳየችበት ከመሆኑም በላይ የዕድገቷና የሉዓላዊነቷ ማረጋገጫ ነው። ለዚህም ነው ህዝቡ ግድቡ የሚሰራበት ቦታ ድረስ በመሄድና ባለበት ቦታ በመሆን ደጀንነቱን እያረጋገጠ ያለው።

መንግስት ለዘመናት  ለብቸኝነት የዓባይን ውሃና ድልብ የአገሪቱን አፈር ሲጠቀሙ ለነበሩት አገራትና ለዓለም ኅብረተሰብ የህዳሴው ግድብ መገንባት በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትል በተገኘው የዜና አውታርና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በማዘጋጀት ሁኔታውን እየገለፀ ነው፡፡ ይህ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

በአገር ውስጥ ህዝቡ ጥያቄው ተመልሶለታል። የህዳሴው ግድብ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የሚለውን አባባል በተግባር እንደሚተረጉም ተረድቷል፡፡

የህዳሴው ግድብ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ለመጣው የአገራችን ምጣኔ ሀብት የሃይል ፍላጎት በብቃት ለማቅረብ ምጣኔ ሀብቱንም ለማሳደግ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡

ከዚህም ባሻገር የጎረቤት ሃገራትን የሃይል ፍላጎት ክፍተት በመሙላት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ወደላቀ ደረጃ ያደርሳል። የውጭ ምንዛሪንም በማስገኘት የፀረ ድህነት ትግሉን ያፋጥናል። ህዝቡ ይህንንም ተረድቶታል፤ ያልተረዳ አካል ካለ ውጭ የሚኖረው ተቃዋሚ ተብዬ ነው።

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለም፤ በአገሪቱ ውስጥ እየተከናወነ ስላለው ግንባታና እየተመዘገበ ስላለው ፈጣን ዕድገት ግን ከመፃፍና ከመናገር ተቆጥቦ አያውቅም። ለዚህም ነው በተለያየ ወቅት ተቃዋሚዎች አገርንና መንግስትን ለይታችሁ ተመልከቱ የምንለው፡፡

ማንም ተቃዋሚ ግቡ የፖለቲካ ስልጣን ነው። ይህን ለማሳካት አገሪቱን ያሳድጋል፣ ይለውጣል፣ ድህነትን ያስወግዳል፣ መልካም አስተዳደርን ያሰፍናል የሚል ፖሊሲ ቀርፆ ህዝብን በማሳመን በምርጫ ተሳትፎ በማሸነፍ ስልጣኑን ለመቆናጠጥ የሚታገለው፡፡ ከተሸነፈም ሽንፈቱን በፀጋ ተቀብሎ በሚያስማማ የጋራ ጉዳይ ላይ ከመንግስት ጋር ተስማምቶ በማያስማማ ጉዳይ ደግሞ ልዩነቱን ጠብቆ የሚንቀሳቀሰው፡፡ 

ይህ አካሄድ በየትኛውም ሰለጠነ በተባለ አገር ይሰራበታል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ተቃዋሚ ነገ ከነገ ወዲያ እመራዋለሁ የሚለውን ህዝብና አገር የሚጎዳ ተግባር ላይ ከተሳተፈ አጠያያቂ ጉዳይ ይፈጥራል። ለዚህ መነሻዬ ውጭ አገር ካሉ የተቃዋሚ ፓርቲ ልሳኖች የምንሰማው አባባል ነው።

ሰብ ሰሃራን ኢንፎርመር የተባለው ጋዜጣ በርዕስ አንቀፁ ባሰፈረው መልዕክት በመለስ መሪነት የተጀመረው የህዳሴ ግድብ እውን ለማድረግና እርሳቸውን ለመዘከር ከሚደረገው ጥድፊያ በተቃራኒ ይህ የግድብ ግንባታ በትክክለኛው የልማት መስመር የታነፀ አይደለም።

ህዝቡም የህዳሴው ግድብ ከመታቀዱ ጀምሮ በይፋ እስከተነገረበት ጊዜ ድረስ ስለፕሮጀክቱ ምንም የደረሰው መረጃ አለመኖሩ ይባስ ብሎም ከፕሮጀክቱ ዕቅድ አንስቶ በሌሎች ሂደቶች ላይ እንዲሳተፍ ዕድል አለመሰጠቱ ለዚህ ትችት ማሳያ ናቸው ሲል ያትታል።

በተጨማሪም የህዳሴው ግድብ ጉዳይ በከፍተኛ ባለስልጣናት ብቻ በሚስጢር ተይዞ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ ነው ለህዝቡ የደረሰው፤ በህዳሴው ግድብ ላይ የሚካሄድ ማንኛውም የግንባታ ስራን በሚስጢር መያዝ በእሳት እንደመጫወት ሲልም ነው አስተያየቱን የሰጠው።

ጋዜጣው የማንን ፀፀትና ቁጭት ለመግለፅ እንደፈለገ በግልፅ ይታወቅበታል። በመጀመሪያ ደረጃ በየትኛውም አገር የፕሮጀክት ሃሳብ የሚመነጨው ከግለሰብ፣ ከቡድንና ከህዝብ ሊሆን ይችላል።

የህዳሴው ግድብ ስራ በወቅቱ አልተጀመረም እንጂ ጥንት ኢትዮጵያን ሲመሩ የነበሩ ነገስታትም ሳያስቡበት አልቀሩም፡፡ ተከታታይ ትውልዶችም መንግስት ላይ ተፅዕኖ ሳያሳድሩ ያለፉበት ጊዜ የለም፡፡ በጽሁፍም፣ በዘፈንም፣ በስነ ቃልም ብዙ ተብሎለታል ዓባይ፡፡

በሌላ ጎን ዓባይን በብቸኝነት ለመጠቀም ካለው የተሳሳተ አመለካከት በመነሳት ዓባይ ላይ ለሚሰሩ ማንኛውም ግንባታዎች ብድር ከማስከልከል አንስቶ ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት ብለው እንደሚዘምቱም ሲያስፈራሩን የኖሩ አገራትም መኖራቸው ግልፅ ነው።

ይህን የህዝብ ፍላጎትና የውጭ ተፅዕኖ ባቻቻለ መልኩ ዕቅድ በማዘጋጀት ፕሮጀክት ቀርፆ መንቀሳቀሱ የስነ ምግባር ጉዳይ ነው፡፡ የነብር ጅራትን ለመያዝ የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት የፓርቲም ሆነ የመንግስት አመራርን ዲሲፕሊን ይጠይቃል - ነብሩ ሳይንቀሳቀስ ጅራቱን ለመያዝ ተችሏል። ምክንያቱም ሆይ ሆይታና ጫጫታ ነብሩን ያነቃዋልና።

መንግስት ያደረገው መንገዱን ማመቻቸት ነው፡፡ ይህ ሲጠናቀቅ ጅራቱን የመያዝ ስራ የተከናወነው በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንካራና የፈረጠመ ክንድ ነው፡፡

በመሆኑም ህዝቡ ነብሩ እንዲያዝ ጫና ከማሳደር ጀምሮ የነብሩን ጭራ እስከመያዝ ድረስ ከመንግስት ጋር እጅና ጓንት በመሆን ሰርቷል፡፡ በሂደቱ ላይ እንዲሳተፍም ዕድል ከማግኘቱም በላይ የህዳሴው ግደብ ባለቤትም ነው፡፡ ታዲያ ምኑ ላይ ነው ዕድል አልተሰጠውም ብሎ ማላዘን።

እርግጥ ነው የነብሩ ጅራት እንዳይያዝ የሚፈልጉ አገራዊ ራዕይ የሌላቸው አካላት ስራው በሚጀመርበት ወቅት ዜናውን መስማታቸው ሊቆጠቁጣቸው ይችላል፡፡ ፕሮፓጋንዳ የሚነዙበት፣ የህዝቡን ተነሳሽነት በመጠኑም ቢሆን የሚያሟሽሹበት፣ ዕድል አሳጥቷቸዋል።

ከዚህ ውጭ የህዳሴው ግድብ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ ደፋ ቀና ማለት የህዝብን አመኔታ ይጨምር ካልሆነ ችግሩ አይታየንም። ጉዞውም ትክክለኛ የልማት ጉዞ ነው፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ባለን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም ያውም ተያያዥ የሆኑ ጥቅሞች ያሉት፣ ህዝቡን ከድህነት ማጥ የሚያላቅቅ፣ የአገሪቱንም ተሰሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑ ሌላ ታዲያ ምኑ ነው የተሳሳተ መስመር? ከምትፀፀቱ ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን በመቆም ሰጥቶ በመቀበል መርህ በህዳሴው ግድብ ተጠቀሙ እንላቸዋለን።

ሌላው የገረመኝና በውስጤ እንዳፍርባቸው ያስገደደኝ ዘገባ በእኛው አገር የተቃዋሚዎች ልሳን በሆኑ ሚዲያዎች የተላለፈው ነው። እንዲህ ይላል፡- በአባይ ግደብ ላይ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በውጭ አገር አሰሪዎችና ተባባሪ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ተቆጣጣሪዎች በሚፈፀም በደል ስራቸውን እየለቀቁ መሆኑን በድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ገልፀዋል ሲሉ ይነግሩናል፡፡

ሲቀጥሉም በመጀመሪያዎቹ የግንባታ ወራት አገራዊ ስሜቱ ፈንቅሎት ወደአካባቢው በመሄድ ከአንድ አመት ከስድስት ወር በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ወጣት ሰራተኛው በየጊዜው በሚደርስበት በደል በቀን ውስጥ ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ሰራተኞች እንደሚለቁ የሚጠቁም መረጃ መረጃ አለን ሲሉም ዘግበዋል። ይህ ዜና ብዙ ነገሮችን ያጭራል፣ ይገርማልም፣ ያሳዝናልም፣ ያሳፍራልም።

በመጀመሪያ ደረጃ መታወቅ ያለበት በማንኛውም አገር ውስጥ በመንግስትም ሆነ በግል ተቀጥሮ የሚሰራ ሰራተኛ የአገር ልጅም ሆነ የውጭ ተቀጣሪ የሚሰራበት ቦታ፣ የሚያገኘው ምንዳ ቢሮክራሲው ከተመቸው ይሰራል ካልተመቸው ስራውን እርግፍ አድርጎ በመተው አማራጩን ይፈልጋል፡፡ ይህ በየትም ዓለም ያለ አሰራር ነው፤ ታዲያ የመስራትም፣ የመልቀቅም መብት በተከበረላቸው ፕሮፖጋንዳው ለምን አስፈልጎ ይሆን? ይገርማል፡፡

ሌላው የሚያሳዝነው የህዝቡን አገራዊ ስሜት በምንዳ ቀይሮ ማሰቡ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለአገሩ ቀናኢ ነው፡፡ ሟችም ነው፡፡ ይህን በተለያዩ ዘመናት በተግባር ገልጿል፡፡ አሁንም እየተከተለ ያለው አካሄድ ይህኑ ነው፡፡

ታዲያ አገራዊ ስሜት ፈንቅሎት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ቃል በመግባት ወደ ስፍራው የተጓዘው ዜጋ በደል ደርሶብኛል ብሎ ከውጊያ መስመሩ ለቆ ወጥቷል ብሎ ማናፈሱ ንቀት አይሆንም? ህዝብን መናቅ እንኳን ለበደል ለጥይትም ግንባሩን የማያጥፍ ዜጋ እንዳለን እባካችሁ ልብ በሉ፡፡

ያሳፈረኝና እነዚህ ሰዎች ምን ሆኑ እንድል ያደረገኝ ከአንድ ወጣት የሰሙትን /መስማታቸው እርግጠኛ ከሆነ/ አጠቃለው በቀን ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ሰራተኞች ስራቸውን ለቀቁ በማለት ማስተላለፍ ታዲያ ምን ይሉት ቧልት ይሆን?

የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው አለም በስራ አጥነት ስትናጥ፣ ጎዳናዎቻቸው ሁሉ በየዕለቱ በስራ አጥ ወጣቶችና ሴቶች ሰላማዊ ሰልፍ ሲደምቁ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የተለያየ የስራ ዕድል እየተፈጠረ ወጣቱና ሴቱ ድህነትን ደህና ሰንብት በማለት ላይ መሆኑን ነው፡፡

ከእነዚህ የስራ ዕድል አማራጮች መካከል ደግሞ ለወደፊቱ እሰከ አስር ሺህ ዜጎችን ያሳትፋል የተባለው የህዳሴ ግድብ ስራ ነው፡፡ ወጣቱ ከአሁኑ በቡድን በቡድን እየተደራጀ ወደ ግድቡ ግንባታ ስፍራ በመሄድ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ውጤታማነቱን እያረጋገጠ ነው፤ ይህ ሃቅ ነው፡፡ የማይታጠፍ የማይቀለበስ ሃቅ፡፡

ታዲያ ጠላቶቻችንና ተላላኪዎቻቸው ከየት አምጥተው ነው በሬ ወለደ የሚዘግቡበት? ዓላማቸው ግልፅ ነው፡፡ ህዝቡም ቀድሞ ተረድቶታል፤ ይኮሩበትና ይተማመኑበት የነበረው አበዳሪዎች ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር የፋይናንስ ምንጩን የማድረቅ ስትራቴጂ እኛው መሀንዲስ እኛው የፋይናንስ ምንጭ በመሆን እንሰራዋለን በሚለው የታጋይ መለስ ንግግርና በህዝቡ ተቀባይነትና ቁርጠኝነት ከሽፏል።

ህዝቡ ግድቡ የኢትዮጵያ ትንሳኤ መገለጫ ነው፣ የአንድነታችን ውጤት ነው፣ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት መስመራችን ትክክለኛነት ማረጋገጫ ነው በማለት በስጦታ፣ ቦንድ በመግዛት ስራውን እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን በማለት አቋሙን የገለጸው፡፡

ይኸኛው ግንባር አላላውስ ሲል በተላላኪዎች በኩል አጀንዳ መፍጠር ጀመሩ፡፡ ለህዝቡ የግድቡ ስራ በተገቢው መልኩ እየተሰራ እንዳልሆነ ኢትዮጵያውያን ላይ በደል እየተፈፀመ፣ በዚህም ሰራተኞች በየቀኑ እየለቀቁ የግድቡ ስራም እየተፍረከረከ መሆኑን በመግለፅ ተነሳሽነቱን መቀነስ ጥርጣሬን በማጫር ልዩነትን መፍጠር ነው፡፡ ይህም አካሄድ የተበላ ዕቁብ ነው።

ህዝቡ ዓባይን ኢትዮጵያዊ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል፤ በዚህም ተሳክቶለታል፡፡ የቀረው እናንተን ኢትዮጵያዊ ማድረግ ነው፤ ከስልጣንና ከተመቻቸ ኑሮ አርቃችሁ እንድታስቡ ነው፡፡ ነገ ስልጣን ብትይዙ የውጭ ምንዛሪውን ትጠቀሙበታላችሁ፤ በሰላም ለሰላም በመጠቃቀማችሁም ላይ የተመሰረተ ጉርብትና ለማራመድ ለውጭ ፖሊሲ መሰረት ይሆናችኋል እያላችሁ ነው፡፡

በመሆኑም የታሪካዊ ጠላቶቻችን አጀንዳ ይዛችሁ ከምትነሱ ያውም ህዝቡ ቀድሞ የነቃበትን አካሄድና አጀንዳ የህዳሴውን ግድብ ለማጠናቀቅ በሚደረገው አገራዊ ርብርብ ከመንግስትና ከህዝብ ጋር በመሆን አሻራችሁን አሳርፉ፤ የህዳሴው ግድብ የአገር ሀብት ነው፤ የአንድነታችን መለያ ነው።

ለወደፊቱ የዚህ ታሪክ ተቋዳሽ ለመሆን በኢትዮጵያዊነት ስሜት በመነሳት ጠላትን አሳፍሩ፤ በምታገኙት መድረክ ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ ህዳሴ ግድብ አራማጆችን ለማሳፈርና ለማዋረድ ከመንግስትና ከህዝብ ጎን ቁሙ፤ ትንሽ ብትሆኑም ደጋፊዎቻችሁን አስተባብሩና ቦንድ በመግዛት የዜግነት ግዴታችሁን ተወጡ - ይህ የህዝቡ ሃሳብ ነው።

ጊዜው የስራ፣ ጊዜው የተግባር ነው፡፡ መንግስትና ህዝቡ የአምስት ዓመቱን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ አንድነት ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ ነው።

ይህን እውነታ የስልጣኔ ጫፍ ላይ ያሉ አገራት እንኳን እየመሰከሩ ነው፤ የተለያዩ ሚዲያዎችም ይህንኑ እየዘገቡ ነው ።

አገራችንን ከአንበሳ ጋር በማመሳሰል ድንቅ ዘገባ እያቀረቡ ነው፡፡  አንበሳ ፈጣን፣ ጠንካራም ነው፡፡ ኢትዮጵያም የአፍሪካ አንበሳ ለመሆን በፈጣን ሁኔታ እየገሰገሰች ነው፡፡

ይህንኑ ሲያብራሩም በአንድ ወቅት በድህነት ትታወቅ የነበረችው ኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብት ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ለመሆን የተለያዩ ዕድገት መር ፖሊሲዎችን ቀርፃ ውጤት እያስመዘገበች ነው።

በግብርና ዘርፍ መሪነት የተጀመረው ይህ ፈጣን ዕድገት ከእጅ ወደ አፍ የነበረውን የአብዛኛውን አርሶ አደርና አርብቶ አደር ህይወት በመቀየር ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ዕድገት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው፡፡

ዝናብ አጠር እና ለም አፈራቸው በጎርፍ በመታጠቡ ምክንያት ለተደጋጋሚ ድርቅ ይጋለጡ የነበሩ ዜጎችን በምግብ ለስራ ፕሮግራም በማደራጀት አካባቢያቸውን መልሶ እንዲያለሙና አማራጭ የግብርና ዘርፍ ተጠቅመው ኑሮአቸውን እንዲለውጡ የተቀየሰው ፖሊሲም ውጤታማ ሆኖ በድርቅ ከመሞት ድነው ራሳቸውን መቻላቸው ለሌሎች አገራትም ትምህርት ሊሆን ይችላል ብለው መዘገብ ጀምረዋል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት አንጋጠው ሰማይ ሰማዩን ይመለከቱ የነበሩ ዜጎች በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ ሰፈራ ለም ወደ ሆኑ አካባቢዎች በመስፈር ከራሳቸው አልፈው አገር ቤት የቀረውን ዘመዳቸውን መርዳት መጀመራቸውና ትርፍ ጥሪት በመፍጠር ልማቱ ላይ መሳተፋቸው መንግስት እየተከተለ ያለው ፖሊሲ ትክክለኛነት መገለጫ መሆኑንም ያሰምሩበታል።-

እነዚህ የዜና ማሰራጫዎቸና ድረ ገፆች ስለ ከተማ ነዋሪው ህይወት መቀየርና ስለ ከተሞቻችን ዕድገት ሰፋ ያለ ዘገባም አስፍረዋል።

የአፍሪካ ኒውዮርክ በማለት አዲስ አበባን ማቆላመጥ ጀምረዋል፡፡ አዲስ አበባ አሁን የጀመረችውን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ከቀጠለችበት በአጭር ጊዜ ውስጥ የአፍሪካ ኒውዮርክ ልትሆን እንደምትችል ተንብየዋል።

ከተማዋ የጀመረችው የቤቶች ልማት አብዛኛውን ነዋሪ የቤት እጦት ችግር ከመቅረፉም በላይ ለወጣቱና ለሴቶች የስራ ዕድል በመፍጠር በኩልም ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ይገልጻሉ።

ይህም አገሪቱ እየተገበረች ያለው የፀረ ድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ ውጤታማ መሆኑን ነው፤ በከተማዋ በሁሉም አቅጣጫ ሊባል በሚችል መልኩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፤ ይህ የከተማ ነዋሪውን ምቾት ከመጠበቁም በላይ እያደገ ላለው የንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

በሚቀጥሉት ዓመታት የከተማዋን ገፅታ በፍጥነት ይለውጣል ተብሎ የሚገመተው የቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ በቻይና የባቡርና መንገድ ኩባንያ መጀመሩም የከተማዋን ተመራጭነት ከፍ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም አዲስ አበባ በ2013 መጎብኘት ካላባቸው አስር የአለማችን ከተሞች አንዷ እንድትሆን አብቅቷታል።

አገሪቱ እያስመዘገበችው ያለው ፈጣን ዕድገት እየተገነቡ ያሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ የኃይል ማመንጫ ፕላንቶች፣ ለግብርና ኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ የእርሻ መሬቶች፣ በከተሞች እየተስፋፉ ያሉ ለዓይን የሚስቡ ህንፃዎች፣  የህዝቡ ስራ ወዳድነትና እንግዳ ተቀባይነት እንዲሁም ከተረጋጋና ሰላማዊ ከሆነው አገራዊ ገፅታዋ ጋር የብዙዎችን አገሮች ትኩረት እየሳበች መጥታለች፡፡

እነዚሁ የዜና ምንጮች እንደዘገቡት አገሪቱ በትምህርት ስርዓቷ ላይ ስር ነቀል ለውጥ በማድረግ የትምህርት ፕሮግራም ከምጣኔ ሃብት ስትራቴጂው ጋር እንዲጣጣም ያላሰለሰ ጥረት አድርጋለች፡፡

በዚህም የተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ባለፉት አስርተ ዓመታት ውስጥ በትምህርት ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ካሳዩ ጥቂት የአፍሪካ አገራት አንዷ አድርጎ እውቅና ሰጥቷታል።

መንግስት በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ላይ ኢንዱስትሪው የመሪነት ሚናውን ከግብርና እንደሚረከብ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የትምህርት ስርዓቱን በመቀየር ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

በእስካሁኑ ጉዞም በየጊዜው በተከታታይ እየተመዘገበ ባለው ዕድገት ተስበው በመምጣት በአገሪቱ ውስጥ ኢንዱስትሪ እየገነቡ ላሉትም ሆነ ገንብተው ስራ ለጀመሩ የውጭ ኢንቨስተሮች የሰለጠነ የሰው ኃይል በተመጣጣኝ ዋጋ ከአገር ውስጥ እንዲያገኙና ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ ሚና ተጫውታል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለወደፊቱ የአገሪቱ መካከለኛ ኢንዱስትሪ መሰረት ይሆናሉ ተብለው በዕቅድ የተደራጁ የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ተዋናዮች ተፈጥረዋል፡፡ 

በዕውቀቱ ላይ የተመሰረተ ስራ እንዲሰሩ አገሪቱ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በመክፈትና በተጨባጭ ዕድገት መር የሆነ ስልጠና በመስጠት ብዙዎች ስራ ፈጥረው አገራቸውንም ሆነ ራሳቸውን እንዲደግፉ አስችሏል።

የግብርና ዘርፉም በሰለጠኑ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እንዲመራ በቀየሰው ስልት የግብርና ባለሙያዎች በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በማስመረቅ በቀጥታ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ጋር በመሄድ እንዲደግፉ፣ ከባህላዊ አሰራር በማላቀቅ ዘመናዊ ግብዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ህዝባዊ ወገንተኝነቱን አስመስክሯል።

የከተማው ነዋሪም ሆነ የገጠሩ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ጤናው ተጠብቆለት የልማቱ ዘርፍ ተዋናይ እንዲሆን በተቀመጠው ስትራቴጂ መሰረት በትላልቅ እና በአነስተኛ የገጠር ከተሞች የግል የህክምና መስጫ ተቋማት ተከፍተው  አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በትላልቅ ከተሞች የነበሩ ያረጁ የጤና ተቋማትን ከፍተኛ በጀት በመመደብ እንዲታደሱና አገልግሎታቸውን እንዲያሰፉ ሲደረግ በመላ አገሪቱ የጤና ኬላዎች በየቀበሌው እንዲቋቋሙ በማድረግ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው።

የጤና ፖሊሲው በሽታን በመከላከል ላይ በማተኮሩ ከግልና ከመንግስት የጤና ማሰልጠኛዎች ሰልጥነው የወጡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የጤና ኤክስቴንሸን ባለሙያዎችን በየወረዳው በመመደብ ዜጎች በቀላሉ ሊወገዱ በሚችሉ በሽታዎች እንዳይጠቁ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው።

በአጠቃላይ የዓለም ህዝብም ሆነ ተጠቃሚ እየሆነ ያለው የአገሪቱ ህዝብ የሚስማማው ኢትዮጵያ በፈጣን ምጣኔ ሃብታዊ የዕድገት ጉዞ ላይ መሆኗን ነው።

ይህን ተከታታይነት ያለው ፈጣን የምጣኔ ሀብት ጉዞ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ህዝብና መንግስት የማይታጠፍ ቃል ገብተዋል።

ይህ የህዝብና የመንግስት ቃል እንዳይታጠፍና አንድነታችን እንዳይሸረሸር በማር እየተለወሱ የሚላኩልንን መርዞች ለይተን ማክሸፍ ይጠበቅብናል። ቸር እንሰንብት፡፡