ለመሆኑ የቴሌ ሪፎርም ምን ፈየደ?

  • PDF


ተዘራ ማሩ

በአምስት ዓመቱ የእድትና ትራንስፎርማሽን እቅድ የአገሪቱን ልማት ለማጠናከርና አገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ በተቀመጠው አቅጣጫ የመሰረተ ልማት ግንባታ  በዋናነት ከተያዙት ዓበይት የልማት ዘርፎች አንዱ ነው። በአምስቱ ዓመቱ ከመቸውም በተለየ መልክ ሰፊ መሰረተ ልማት እንደሚሰራ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል።

በጥራትና በዋጋ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ መሰረተ ልማት የመዘርጋቱ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል። ይህ ተግባር በቀጥታ የሚያያዘው ከዘላቂው የህዳሴ ጉዞ ጋር በመሆኑ ምክንያት ባልተቆራረጠ መልኩ ልማቱ ቀጥሏል።

የስልክ መሰረተ ልማትን ከመቃኘታችን በፊት ስለ መንገድ፣ ኤሌክትሪክ ሃይልና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በጨረፍታ ማየቱ ለአጠቃላይ ግንዛቤ ሊጠቅም ይችላል የሚል እምነት በመያዝ በሚከተለው መልክ ለመቃኘት እንሞክራለን።

የመሰረተ ልማት ግንባታ የአገሪቱ እድገት ሌላው ገጽታ ነው፡፡ በዚህ ጽሁፍ በዋናነት የምናየው የስልክ ሆኖ  የመብራት፣ የመጠጥ ውሃ እና  የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ደግሞ ለግንዛቤ ያህል  በጨረፍታ አይተናቸው እናልፋለን፡፡ 

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በአገሪቱ የነበረው የመሰረተ ልማት ግንባታ በጣም ዝቅተኛ ነበር፡፡ እንደ መንገድ፡ ስልክና መብራት የመሳሰሉት ዋና ዋና  የመሰረተ ልማት አውታሮች በከተሞች ብቻ የታጠሩ ነበሩ፡፡ ከ85 በመቶ በላይ  በገጠር የሚኖረውና በግብርና የሚተዳደረው የአገሪቱ ህዝብ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ባለመኖሩ  ለከፍተኛ ችግር ይዳረግ ነበር፡፡

ምርቱን ወደ ገበያ የሚያወጣበት አመቺ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ከሚያመርተውን ዝቅተኛ ምርት ሌሎች ለዕለታዊ ፍጆታው የሚያስፈልጉ የፋብሪካ ውጤቶችን ለመግዛት ሲፈልግ ምርቱን የሚሸጠው በርካሽ ዋጋ ነበር፡፡ እናቶች በምጥ በተያዙ እና ህጻናትና አረጋውያን በታመሙ ጊዜ   ወደ ህክምና ቦታ ለመድረስ ይቸገሩ ነበር፡፡ በአቅራቢያቸው የጤና ተቋም ባለመኖሩና ወደ ሌላ

አካባቢ ለመሄድ ደግሞ መሰረተ ልማት ባለመዘርጋቱ የትራንስፖት አገልግሎት ስለማያገኙ፡፡ የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት የነበረው የነበረው የመብራት መሰረተ ልማትም እንደ ሌሎቹ ሁሉ በዝቅተኛ ደረጃ ነበር፡፡ በአገሪቱ የነበረው የመብራት ሽፋን ስምንት ከመቶ ብቻ ነበር፡፡ ይህ አሃዝ በያዝነው ዓመት 47 ከመቶ ደርሷል፡፡ አጠቃላይ የአገሪቱ ሃይልን የማመንጨት አቅምም 2123 ሜጋ ዋት ደርሷል፡፡ በእድገትና ትራንሰፎርሜሽን መጨረሻ ዓመት ሽፋኑን  75 ከመቶ ለማድረስ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ይህም በነፍስ ወከፍ ሲሰላ 20 ኪሎ ዋት ይደርስ የነበረው ወደ 100 ሜጋ ዋት ማድረስ መቻሉን ያሳያል፡፡

የማይታሰብና ተረት ተረት የነበረው የአባይ ወንዝ ሳይቀር ለልማት የሚውልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሁሉም መስክ ዓለም አቀፍ ደረጃውን አሟልቷል፡፡ ፕሮጄክቱ ከአገር አልፎ የአካባቢውን አገሮች ህዝቦች ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር የሚያጠናክር ነው፡፡ የውሃ ብክነትን በማስቀረት ሁሉንም የተፋሰሱ አገሮች ተጠቃሚ ያደርጋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዜጎች ለዘመናት ሲመኙት የኖረ የህልም ዳቦ ተደርጎ የሚታይ ነበር፡፡ አገሪቱ የራሷን አቅም ገንብታ፤ የውጭ ሃይሎችን ተጽዕኖ ተቋቁማ በራሷ  አቅም አባይ ላይ እንደዚህ ዓይነት ትልቅ ልማት ትገነባለች የሚል እምነት አልነበረም፡፡ አባይን ማልማት የማይደረስና የማይቻል እንደሆነ ታምኖበት ለዘመናት ጥቅም ላይ ሳይውል ቆይቷል፡፡ ዛሬ ግን የማይቻል የሚመስለው እየተቻለ ነው፡፡ 

ከጥንት ጀምሮ ህዝቡ ለአባይ ያለውን ህዝቡ ቁጭቱን የተለያዩ ግጥሞችና እንጉርጉሮዎችን በመደርደር ይገልጽ ነበር፡፡ አሁን እንጉርጉሮው ቀርቶ ዜማው ሁሉ ልማት ሆኗል፡፡ አባይም ማደሪያ እያገኘ ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ በአገር ልጅ በአገር ሃብት፡፡ ያ እምነት አሁን ተሰብሯል፡፡


ኢትዮጵያ የራሷን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብሩ በርካታ ዓበይት ፕሮጄክቶችን የምትተገብርበት አቅም ገንብታለች፡፡ የህዳሴው ግድብ የዚሁ ማሳያ ነው፡፡ ይህ በውስጥ አቅም የሚገነባ ትልቅ ፕሮጄክት ነው፡፡

መንገድ ሌላው የመሰረተ ልማት አውታር ነው፡፡ በአገራችን የመገንድ ግንባታ ከመቼውም በላቀ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ከ1983 በፊት በመላ አገሪቱ የነበረው የመንገድ ሽፋን 18081 ኪሎ ሜትር ብቻ እንደነበር ከመንገዶች  ባለስልጣን የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው የመንገድ ሽፋን 53997 ኪሎ ሜትር ደርሷል፡፡ በመላ አገሪቱ የተገነቡት መንገዶችም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የተደረጉ አንዳንድ ጥናቶች እንዳመላከቱት  በአገሪቱ ከተገነቡት መንገዶች 81 በመቶ የሚሆኑት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡

ሌላው ደግሞ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ነው፡፡ በንጹህ መጠጥ ውሃ እጦት ለበርካታ ውሃ ወለድ በሽታዎች በመጋለጥ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ችግሩ የበለጠ የሚጎላው ደግሞ በገጠር አካባቢ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት በገጠር አካባቢዎች በነፍስ ወከፍ በ1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ ንጹህ የመጠጥ ውኃን ለማዳረስ የተደረገው ጥረት በህዝብ፣ በመንግስትና በመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ሊሳካ መቻሉን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡ 

በአገሪቱ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 73 ከመቶ ደርሷል፡፡ ይህ የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ከተቀመጠው 70 በመቶ ግብ በላይ መሆኑንም መረጃው ያሳያል፡፡

አጠቃላይ የመሰረተ ልማቱን መስፋፋት በዚህ መልክ ከቃኘን በኢትዮጵያ በቴሌ የተካሄደው ሪፎርም ምን ውጤት እያስገኘ ነው? ከዚያ በፊትስ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? አሁን ያለለበት ደረጃ እንዴት ይገመገማል? በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የስልክ ልማት በምን መልክ ተቀርጿል? የሚሉት ተዳሰዋል። የስልክ መሰረተ ልማትና  በኢትዮጵያ የተጀመሩበት ጊዜ ሩቅ ቢሆንም ለበርካታ አስርት ዓመታት መጀመሪያ ሲቋቋሙ ከነበረበት ደረጃ ፈቀቅ ሳይል ቆይቷል። ከአንድ መቶ  ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ በጣም አዝጋሚ የሆነ ለውጥ ማደረጉ ይታወቃል። 

የስልክ አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ከተጀመረ 119  ዓመታትን አስቆጥሯል።  በአንድ መቶ ዓመት ውስጥ በስልክ ልማት እድገት የነበረው ሁኔታ እጅግ አዝጋሚ እንደነበር ለመገመት አያዳግትም።  የስልክ መሰረተ ልማት ለበርካታ ዓመታት የተጓዘበት ጉዞ   አዝጋሚና ፈጣን ስለነበር ህዝቡ በዘርፉ ማግኘት የሚገባው አገልግሎት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡

ከ119 ዓመታት በፊት በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት በአገራችን የቴሌ ግራፍ አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣው። በ1986 ዓ.ም ከሐረር ወደ አዲስ አበባ በተዘረጋው 477 ኪሎ ሜትር የቴሌግራፍና የቴሌፎን መስመር የስልክ አገልግሎት መጀመሩን የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡

ይህ ረዥም እድሜ ያለው የስልክ መሰረተ ልማት የዕድሜውን ያህል ማደግ የቻለበት ሁኔታ  አልታየም፡፡  በአገራችን ልማታዊ መንግስት ወደ ሃላፊነት ከመምጣቱ በፊት የነበሩት ስርዓታት የስልክ መሰረተ ልማት ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚኖረው ፋይዳ በውል  አልተገነዘቡትም ማለት ይቻላል። ዘርፉን ለማስፋፋት ያደረጉት ጥረት በጣም አናሳ ስለነበር አዝጋሚ በሆነ መልክ ነበር እያደገ የመጣው። 

በመሆኑን በኢትዮጵያ አሁን ያለው ልማታዊ መንግስት ወደ ሃላፊነት ከመምጣቱ ከ1983 ዓም በፊት በአገሪቱ  የነበረው የመደበኛ ቴሌፎን ደንበኞች ቁጥር  133091 ብቻ ነበር። በአገሪቱ  በ1984 ዓ.ም የነበረው ስርጭትም 0 ነጥብ 23 በመቶ ብቻ እንደነበር ከኢትዮ-ቴሌኮም የተገኙ መረጃዎች  ያሳያል፡፡

የስርጭቱ ማነስ አንድ ነገር ሆኖ የስርጭቱ ፍትሃዊነት ሲታይ ደግሞ ራሱን የቻለ ችግር እንዳለው ለመረዳት ይቻላል። ከ70 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሚኖርባትና ከዚህም ህዝብ ከ85 በመቶ በላይ ኑሮው በገጠርና የኑሮ መሰረቱም በግብርና በተመሰረተ ህዝብ የስርጭቱ ሁኔታ በአገሪቱ ዋና ከተማ ብቻ የታጠረ እንደነበር መረጃው ያሳያል።

በአገሪቱ ከነበረው አጠቃላይ ስርጭት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ እንደነበር መረጃው ይጠቁማል። ቀሪው 30 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በአገሪቱ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች የታጠረ ነበር። በዚህ ምክንያት አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የዚህ መሰረተ ልማት አገልግሎት ተጠቃሚ ሳይሆን ለዘመናት ዘልቋል።

በአገሪቱ የነበረው  የዓለም አቀፍ መስመሮች ብዛትም 274 ብቻ ነበር፡፡  ይህ አገሪቱ ምን ያህል ከዓለም የተገለለች እንደነበረች አንድ ማሳያ ነው። ለዚህ ደግሞ የነበረው ስርዓት የትኩረት አቅጣጫ ልማት ስላልነበረ ለዚህ ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት በጣም ዝቅተኛ ነበር።

ከሃያ ዓመታት በፊት የአገሪቱን መሰረተ ልማት ለማስፋፋት መንግስት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ መንቀሳቀስ በመጀመሩ የነበረው ሁኔታ እየተቀየረ መምጣት ችሏል። 

አገሪቱ ከድሀነት አረንቋ ለመላቀቅ በሚታደርገው ጥረት የመሰረተ ልማት አስፈላጊነትን ግምት ውስጥ በማስገባት ዘርፋን ለማስፋፋት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ እቅድ ታቅዶ በመተግባር ላይ ይገኛል።

ድህነትን ታሪክ በማድረግ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ አገሪቱን የነደፈችውን የልማት ዕቅድ እውን ለማድረግ መንግስት በወሰዳቸው የተለያዩ የመሰተ ልማት የማስፋፊያና አዳዲሶችን የመገንባት ስራ ምክንያት  ከጊዜ ወደ ጊዜ ግንባታው  እየተሻሻለ መምጣቱን ማየት ይቻላል፡፡

በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፉ ካሉ መሰረተ ልማቶች መካከል አንዱ ስልክ ነው። ስልክ ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገት የሚኖረውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት ዘርፉን በገጠርና በከተማ ለማስፋፋት በተያዘው ዕቅድ መሰረት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ዓለማችን በዘርፉ የደረሰችበትን ደረጃና በመጠቀም ላይ ያለን ቴክኖሎጂ በአገራችንም እንዲስፋፋ በመደረግ ላይ  ነው፡፡  በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ መስመሮች ብዛት 6543 መድረሱን ከቴሌኮም የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡ ይህ አገሪቱ ከዓለም ሕብረተሰብ ጋር ያላት ቁርኝትና ግንኙነት እየሰፋ መምጣተንም ያሳያል።

በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣው የሞባይል ስልክ፣ የሽቦ አልባ ስልክ፣ የብሮድባንድ ኢንተርኔት፣ የብሮድ ባንድ መልቲ ሚዲያ አገልግሎት፣ የብሮንድ ባንድ ቪላት አገልግሎት፣ የገጠር መገናኛ ስልክ፣ የስኩልኔትና የወረዳኔት፣ የአግሪኔት እና የተለያዩ አገልግሎቶችን በማስፋፋት በቀጣይ ሶስት ዓመታት ህዝቡን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዚህ መሰረት የመደበኛ ስልክ ደንበኞች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ መጥቶ በአሁኑ ወቅት
809554 ደርሷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ የጥሪ መስመሮችም ከ6543 በላይ መድረሱን ከኢትዮ-ቴሌኮም የተገኘ መረጃ ያሳያሉ፡፡

በአገሪቱ ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም የተጀመረው በ1991 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ  የነበረው አጠቃላይ አቅም የ36 ሺህ መስመሮች  ብቻ ነበር፡፡  በወቅቱ የደንበኞቹ ብዛት
6740 ብቻ እንደነበር መረጃው ያሳያል፡፡ ይሰጥ የነበረው  አገልግሎትም በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የታጠረ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አገልግሎቱ ደረጃ በደረጃ እየሰፋ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት ከ15 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አቶ በላይነህ የ50 ዓመት አዛውንት ናቸው። ነዋሪነታቸው በሁመራ ገጠር ገበሬ ማህበር ነው፡፡   የሚተዳደሩትም በግብርና ስራ ነው፡፡ ባለፉት ስርዓታት ከእጅ ወደ አፍ ብቻ ያመርቱ እንደነበርና ካመረቱት ምርት ለሌላ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች መግዣ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ከምርታቸው ለገበያ የሚያቀርቡትን በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ ይገደዱ ነበር። ወደ አቅራቢያቸው ወደሚገኝ ከተማ ወስዶ ለመሸጥ የመሰረተ ልማት ችግር በመኖሩና ወደ አካባቢያቸው መጥተው ለሚገዙ ነጋዴዎች ዋጋ ለመደራደርም በከተሞች ያለውን ዋጋ ለማወቅ የሚችሉበት አጋጣሚ ስላልነበረ ምርታቸውን በርካሽ ለመሸጥ ይገደዱ እንደነበርይናገራሉ

በዚህ ምክንያት ተጠቃሚነታቸው ዝቅተኛ ነበር። የለፉትን ያህል ሳይጠቀሙ ለነጋዴ ሲሳይ የሆኑ እንደነበር ያስታውሳሉ። “ያ ዘመን ግን አሁን ሙሉ ሙሉ ተቀይሯል። በአሁኑ ወቅት የማመርተው ምርት መጠን ከማደጉም በላይ በአካባቢዬ ያለውን የግብይት ሁኔታ ቀርቶ አዲስ አበባ ላይ በምን ያህል እንደሚቀና ለማወቅ የሚያስቸግር ነገር የለም። ስልክ ደውለን እዚያ ያለውን ዋጋ በማወቅ ከዚህ አዲስ አበባ ድረስ ለመውሰድ የሚያስፈልገንን ወጪ ግምት ውስጥ በማስገባት ተደራድረን ምርታችንን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸጥ የሚያስችለን ሁኔታ ተፈጥሯል።” ይላሉ።

እንደ አቶ በላይነህ ገለጻ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአካባቢው የመሰረተ ልማት መስፋፋትን ተከትሎ ምርታቸውን በቀላሉ ለገበያ ማቅረብ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ገበያ ከመውጣታቸው በፊት እቤታቸው ሆነው የገበያውን ሁኔታ ማረጋገጥ የቻሉበት ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በአገሪቱ የገጠሩ ክፍል ተንቀሳቃሽ እና ሽቦ አልባ ስልክ መስፋፋት ከጀመረ ወዲህ ህዝቡን ከፍተኛ ተጠቃሚ እያደረገው ይገኛል፡፡  በተንቀሳቃሽ እና በሽቦ አልባ ስልክ አማካይነት የገጠሩ ህብረተሰብ ገንዘቡን፣ ጉልበቱንና ጊዜውን መቆጠብ መቻሉን አቶ በላይነህ ይናገራሉ፡፡

በመላ አገሪቱ እየተስፋፋ ያለው የስልክ አገልግሎት ሕብረተሰቡን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እያደረገ መምጣቱን ለመረዳት አያዳግትም። በተለይ በአገሪቱ የትምህርት ተቋማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ወደተለያዩ ከተሞች ለትምህርት የሚሄዱ ልጆቻችን ጋር በቀላሉ ለመገናኘትም ሆነ ትምህርታቸውን ጨርሰው በስራ በሚመደቡበት ወቅት ሁኔታቸውን ለመከታተልና ለማወቅ   በቀላሉ መገናኘት የምንችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል ይላሉ።

የተንቀሳቃሽ ስልክ በአጭር ጊዜ ከመስፋፋቱ በተጨማሪ በአገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት  እያደገ የመጣበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ የዳታና ኢንተርኔት አገልግሎት ደንበኞች ብዛት 173117 መደረሱን ከኢትዮ-ቴሌኮም የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡

ተቋሙ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎትን ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር በማጣጣም የዓለም አቀፍ መረብ ውስጥ መግባት የሚያስችለውን ዘመናዊውንና ከፍተሻ የመረጃ ፍሰት አቅም ያለውን የብሮድባንድ ኢንተርኔት መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይን በማፍሰስ  በአገሪቱ ለማምጣት የሚጠበቀውን ለውጥ ለማረጋገጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ እሙን ነው፡፡

መንግስት አገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ የሚያስችል ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፎ በመተግበር ላይ የገኛል። ባለፉት ሁለት የእድገትና ትራንስፎርማሽን ዘመን የመጀመሪያ ዓመታት በዘርፉ የነበረው አፈጻጸም አበረታች ነው።

በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የስልክ መሰረተ ልማትን ለማጠናከር የሚያስችሉ መሰረታዊ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። በተቀመጠው እቅድ መሰረትም ባለፉት ሁለት ዓመታት መሰራት ይኖርባቸዋል ተብለው የተለዩ ተግባራት በሚጠበቀው መጠን መከናወናቸውን መረጃው ያሳያል።

የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው የተዘረጋውን ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን መረብ ጥራቱን ማረጋገጥ ነው። ከስልክ የኔትወርክ መጨናነቅና ከኢንተርኔት ፍጥነት ጋር ተያይዘው የሚነሱና በተጨባጭም ሲያጋጥሙ የነበሩ የጥራት ችግሮችን በተገቢው መንገድ መፍታት አንዱ አቅጣጫ ነበር።

ከዚህ አንጻር ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ረዥም ርቀት መሄድ ተችሏል። በተለይም ከፋይበር መቆረጥ ጋር ተያይዞ በኢንተርኔት ላይ ያጋጥም የነበረውን ችግር ለመፍታት ህብረተሰቡ ነቅቶ ንብረቱን እንዲጠብቅ ለማስቻል በርካታ የማነቃቂያ ስራዎች ከመሰራታቸውም በተጨማሪ ከየአካባቢው የፖሊስ ሰራዊት ጋር በመተባበር አጥፊዎች ወደ ህግ የሚቀርቡበት ሁኔታዎችን በመፍጠር ችግሩን ለመቀነስ የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ከዚህ ጎን ለጎን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በሰፊው እንዲያስተናግድ ለማስቻል ይደረጉ የነበሩ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል። በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው ተግባርም ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ በመሆኑ በቀጣይ ሶስት አመታት አጠናክሮ በመቀጠል የሕብረተሰቡን የዘርፉ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችል መሰረት ላይ እንዳለ ለመረዳት ይቻላል።

ከዚሁ ተለይቶ የማይታየው ደግሞ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሰራርን መዘርጋት ነው። ተገልጋዮች ያለምንም ውጣ ውረድ ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኙበትና ከእነሱ የሚፈለገው ነገርም ቀድመው ማሟላት ይችሉ ዘንድ ግልጽነት ያለው አሰራር መዘርጋት ተችሏል። በዚህ መልክ በዋጋ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል አሰራርን ዘርግቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን መረጃው ያሳያል።

ከ2003 እስከ  2007 ዓ.ም ባለው ጊዜ ለመፈፀም በተያዘው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት በማስፈፀሚያ ጊዜው የመጨረሻ ዓመት ላይ የመደበኛ ስልክ ደንበኞችን ቁጥር 
3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዷል። ከዚህም በተጨማሪ  የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ደንበኞችን 40 ሚሊዮን፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ደንበኞች ብዛት 3 ነጥብ 69 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዶ ይህንኑ እውን ለማድረግ በላቀ ሁኔታ ርብርብ አየተደረገ እንደሆነ መረጃው ይጠቁማል።

ሌላው ዓቢይ ተግባር ደግሞ ተቋሙ በዋጋና በጥራት ተወዳዳሪ የሆነ አገልግሎት መስጠት የሚችል ተቋማዊ ብቃት እንዲኖረው ማድረግና ለዘርፉ ውጤታማነት መሰናክል እየሆኑ ያሉ አንዳንድ  ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡

የሞባይል ስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት የጥራት ደረጃ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተሰሩ እንዳሉ የጠቆመው መረጃው ባለፉት 11 ዓመታት የተለያዩ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል፡፡  

ከተግዳራቶቹ መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የማስፈፀም አቅም ውስንነት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታትም የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአስተዳደሩን ጉዳይ ለፈረንሳይ የስልክ ኩባንያ ተሰጥቷል፡፡ ይህ በዘርፉ ያሉ አስተዳደራዊ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላሉ ተብለው ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል አንዱ እንደሆነ እሙን ነው።

ሌላው ደግሞ የፋይናንስ ጉዳይ ነው። ይህ መሰረተ ልማት የሚፈልገው ገንዘብ በጣም ከፍተኛና በአብዛኛው ደግሞ የውጭ ምንዛሪ በመሆኑ የተነሳ አገሪቱ ካላት አቅም አንጻር አንድ ፈተና እንደሆነ ቢታመንም ይህንን ችግር ለመፍታት ሁለት መንገዶችን መከተል እንደተቻለ ለማወቅ ተችሏል።

አንደኛው የውስጥ አቅምን በማሳደግ መሰራት ያለባቸውን ነገሮች በቅደም ተከተል በመፈጸም ዘርፉን ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ለህዝብ ማቅረብና በዚያ ልክ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ መከተል ተችሏል። በሌላ በኩል ደግሞ ለዘርፉ ልማት የሚያስፈልጉ ተጨማሪ ገንዘብ ተቋሙ በራሱ አገልግሎቱን በማሻሻል የሚያግዝበት ሁኔታ በመፍጠር እንደሆነ ለመገንዘብ ይቻላል። 

በአገሪቱ ያለውን የኢንተርኔት ሽፋን አገልገሎት አሰጣጥን ለማሻሻልም በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በቅርቡ ከመገናኛና ኢንፎርሜሽ ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘ አንድ መረጃ እንደሚያሳየው የሞባይልና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለማሳደግ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተያዘውን በእቅዱ ማብቂያ በተገቢው መንገድ  እንደሚያሳካ ይፋ አድርጓል።

የፓርላማው የሳይንስ፣ መገናኛና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የ2005 ዓ.ም በጀት ዓመት አንደኛ የሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ለመረዳት እንደቻለው   ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በመላው አገሪቱ ለማዳረስ ጠንክሮ እየሰራና ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ነበር።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው አቅም አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ  ሰዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ በእድገትና ትራንስፎርማሽኑ የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል መሰረት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለውን 19 ሚሊዮን የሚጠጋ የሞባይል ተጠቃሚ በዕቅዱ ዘመን ማብቂያ 45 ሚሊዮን ለማድረስ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል ስራ እየተሰራ ይገኛል።

የሞባይል አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻልም የተለያዩ ጥረቶች እየተከናወኑ መሆኑን መረጃው ይጠቁማል። ከዚሁ ጋር ተያይዘው ያጋጠሙ ችግሮች  የተገልጋይ ቁጥር መበራከትና የበርካታ ህንጻዎች መገንባት ይገኙበታል።

ችግሩን ለማስተካካል የሞባይል ጥራት ቡድን ተቋቁሞ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለሰ በግምገማው ወቅት እንደተናገሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት የያዘውን አቋምና እያከናወነ ተግባርራ እንደ ጥሩ እንቅስቃሴ የሚታይ ነው፡፡

በተለይ ተደራሽነቱ በገጠርና በከተማ አጠናክሮ መቀጠል የሚያስችል ራዕይ የሰነቀ መሆኑን አንዳንድ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገው እንቅስቃሴ አበረታች እንደሆነ ገልጸዋል። በሌላ በኩል የመንግስት መስሪያ ቤቶች በመሰረተ ልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ሁሉም ባንኮች ዘመናዊ አሰራርን እንዲከተሉ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ተጠቃሽ እንደሆነ አበረታች እንደሆነ ተገልጿል።

በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ ሪፎርም በማካሄድ ጥሩ ውጤት መገኘቱ ይታወቃል። የለውጡ ዓላማ ኩባንያው አፍርሶ መገንባት ያህል እንደነበር ይታወቃል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ምርጥ የዓለም ተሞክሮ ተጠንቶ ነበር ወደ ስራ የተገባው። ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም በውጭ አገር አማካሪዎችና በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ተተግብሯል።

የኩባኒያው ዓቅም አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስም በጨረታ ላሸነፈው ታዋቂው ፍራንስ ቴሌኮም ሃላፊነቱ ተሰጥቷል።  ከዚህ አኳያ ኩባኒያው ፈርሶ በአዲስ መልክ እንዲገነባ ተደርጓል። አጀማመሩም የሚያበረታታ ሆኖ መገኘቱን በርካቶች ይስማሙበታል። 

ኢትዮ-ቴሌኮም ቀላል የማይባል ርቀት መጓዝ መቻሉን በገሃድ  ማየት ተችሏል። የዚህ መሰረተ ልማት መጠናከርና ተወዳደሪ የሆና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት በአገሪቱ ልማት መፋጠን ላይ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ እንደሆነ ይታወቃል።

በመሆኑም በቴሌ ላይ የተካሄደው ሪፎርም መጠነ ሰፊ ለውጥን ለማረጋገጥ አስችሏል። ይህ ተጠናክሮ በቀጣይ ሕብረተሰቡን የበለጠ ተደራሽ እንደሚያደርግና ቀልጣፋ አገልግሎትና በቂ ሽፋን በመስጠት ዓለማችን  በዘርፉ የደረሰችበትን ደረጃ በመድረስ የህዝቡን ሙሉ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት  መጣሉን በርካቶች ይስማሙበታል።