የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ልማት ተግዳራቶችና ስኬት

  • PDF

ተስፋዬ ለማ
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የተመሰረተው ግብርና ላይ ነው። ይህንን ግብርና መር ምጣኔ ሀብትን ወደ ኢንዱስትሪ መር ምጣኔ ሀብት ለማሸጋገር የሚያስችል መሰረት ለመጣል የአምስት ዓመት እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተነድፎ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡

በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የኢንዱስትሪ ልማቱን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ተሰጥቷት እየተሰራ ይገኛል። በተለይም አገራችን የምትመራበትን የምጣኔ ሀብት መሰረት ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለመቀየር በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው።

በዚህ መልክ የስሚንቶ ፋብሪካዎችን የማስፋፋትና አዳዲሶችን የማቋቋም፣ የስኳር ፋብሪካዎችንም በዚሁ መልክ የመፈፀም፣ የብረታብረት ስራዎችን የማስፋፋትና የማጠናከር እንዲሁም የጥቃቅንንና አነስተኛን በተገቢው መንገድ የማስፋፋትና የማጠናከር እቅድች ሰፍረው እየተሰራበት ይገኛል።

ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለአገሪቱ የሚሰጡት ጥቅም እጅግ የጎላ በመሆኑ የሚኖራቸውን ፋይይዳ በወሳኝ መልኩ መወጣት ይችሉ ዘንድ ያሉባቸውን ተግዳራቶች በመፈተሽና መፍትሄ በማበጀት ጠንካራ የምጣኔ ሀብት መሰረት እንዲሆኑ የሚያስችል አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ተግባር መግባት ተችሏል። በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ወሳኝ ተደርገው ከተወሰዱ የልማት ዘርፎች መካከል የጥቃቅንና  አነስተኛ ተቋማት ማስፋፋትና ማጠናከር ይገኛሉ፡፡
የጥቃቅንና አነስተኛ እንዱስትሪ ልማት ቴክኖሎጂን፣ ክህሎትን፣ ካፒታልንና ገበያን ግብአት በማድረግ በማኑፋክቸሪንግና በአገልግሎት በሰፊው የሚሰማራ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ወሳኝ የምጣኔ ሀብት ዘርፍ ነው፡፡ 
በተለይ  ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ከመፍጠር፤ ኢንዱስትሪን ከማስፋፋትና ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልን ከማስገኘት አንፃር የጎላ ድርሻ ያለው የልማት ዘርፍ ነው። 
ይህንን ዘርፍ በማስፋፋትና በማጠናከር የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት በማሳዳግ ረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግስት ዘርፉን በማስፋፋትና በማጠናከር ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ። 
በዚህም ላለፉት ዓመታት ለዘርፉ ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ስትራቴጂና ፖሊሲ ተቀርፆ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በከተማችን ውስጥ ያለውን ስራ አጥነት በዘላቂነት ለማስወገድ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጉልህ ድርሻ ስላላቸው ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶበት በሰፊው ወደ እንቅስቃሴ ተገብቷል፡፡
በአገሪቱ የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍና አስተማማኝ የሥራ ዕድልና የተሻለ  ገቢ ለመፍጠር ብሎም ለኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ መሰረት ለመጣል የጥቃቅንና አነስተኛ የጎላ ድርሻ እንዲኖረው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙትን የዘርፉን አንቀሳቃሾችና አዲስ ወደ ዘርፉ የሚገቡትን በማስፋፋት፣ በማጠናከርና ችግሮቻቸውን በመቅረፍ  ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። 

በጥቃቅንና አነስተኛ የሚሳተፉ ወጣቶችን በማደራጀት፣ በማቋቋምና በማጠናከር ሰፊ የስራ እድል መፍጠርና የነዋሪውን የገቢ አቅም እንዲጨምር በማድረግ ድህነትን ለመቀነስ በሚደረገው ትግል የጎላ ሚና እንዲኖረው ማድረግ በሚያስችል መልኩ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ 

በየጊዜው አዳዲስ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲስፋፉ በማደራጀትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ አዳዲስ የስራ መስኮችን በመፍጠር ስራ አጥነትን ትርጉም ባለው መልክ ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ርብርብ ውጤታማ እየሆነ ይገኛል።

ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለኢንዱስትሪ ልማቱ መሰረት ሆነው ከማገልገላቸውም ባሻገር ከፍተኛ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ስላላቸው በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ  እንደሆነ ይታመናል፡፡

ጥቃቅንና አነስተኛ  በታዳጊ አገራት ቀርቶ በበለፀጉ አገራት ሳይቀር ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡  እንደ አሜሪካ፣ ጃፓንና ቻይና በመሳሰሉ አገራት ጥቃቅንና አነስተኛ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡  በእድገትና በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በግልፅ እንደሰፈረው በአገራችንም የህዳሴው ጉዟችንን ለማፋጠን የሚኖራቸው ሚና በእጅጉ የጎላ ነው፡፡

ቀደም ሲል በአገራችን ከነበሩ ችግሮች መካከል አንዱ ሥራ አጥነት ነው።  በአገሪቱ ወጣቱ የስራ አጥ ሆኖ ለአልባሌ ተግባር የተዳረገበት ሁኔታ ቀላል አልነበረም።

ይህንን ችግር መፍታት የሚቻለው የስራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ በርካታ የልማት ተቋማትን በማስፋፋትና ወጣቱ ራሱ የስራ ፈጣሪ እንዲሆን ለማስቻል የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠትና በፋይናንስ በመደገፍ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህንን በተገቢው መንገድ ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ ከጥቃቅንና አነስተኛ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ማነቆዎችን በመለየትና መፍትሄ በማስቀመጥ ውጤታማ ስራን ለማከናወን እየተሰራ ይገኛል። ከእነዚህ ማነቆዎች አንዱና ዋነኛው የአመለካከት ችግር ነበር፡፡ 

ጥቃቅንና አነስተኛ እንደ ስራ መስክ የማይቆጠሩበትና በዚህ ዘርፍ የሚጠቃለሉ አንዳንድ የስራ ዘርፎች ላይ የተለያዩ መሰረት የለሽ  አስተያየቶች የሚሰነዘርባቸው ሁኔታ ይስተዋል ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞም ጥቃቅንና አነስተኛ  ለመሸጋገሪያነት ብቻ የሚያገለግሉና ከዚያ በኋላ የሚያስፈልጉ የሚመስላቸው በርካታ ወገኖች እንዳሉ አንዳንድ በጥናት ተደግፈው የተጻፉ ዶኩመንቶች ያሳያሉ፡፡ 

በመሰረቱ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ አገራት ወሳኝ ናቸው ሲባል በማደግ ላይ ባሉ አገራት ብቻ የተወሰኑ ሳይሆኑ ባደጉና በበለጸጉ አገራት ጭምር ስራ ላይ ያሉና በምጣኔ ሀብት እድገታቸው ላይ ቀላል የማይባል ሚና ያላቸው እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። እንደ አሜሪካና  ጃፓን በመሳሰሉ አገራት ጥቃቅንና አነስተኛ ባሉበት ደረጃ እየሄዱ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

ለአብነት ያህል በጃፓን አገር ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የጃፓንን ምጣኔ ሀብት ሃምሳ በመቶ የሚሸፍኑ መሆናቸው መረጃዎች ያሳያሉ። በዚያች በኢንዱስትሪ ያደገች አገር ይህንን ያህል ድርሻ ያላቸው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በአገራችን ለመሸጋገሪያ ብቻ አገልግለው ይከስማሉ ብሎ ማሰብ የተሳሳተ አመለካከት የወለደው ድምዳሜ እንደሆነ ይታወቃል። ይህንን አመለካከት በአገራችን አነስተኛ ጥቃቅን በተፈለገው የፍጥነት ደረጃ እንዳያድጉ የተወሰነ ጫና እንደሚያሳድር በመገንዘብ የአመለካከት ስርፀትን ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ሌላው መሰናክል ደግሞ የፋይናንስ አቅም ማነስ ነው። በጥቃቅንና አነስተኛ  የሚሰማሩ ወጣቶች በቂ የመንቀሳቀሻ ፋይናንስ አይኖራቸውም። ወደ ስራ የመግባት ፍላጎት ያላቸው በርካታ ወጣቶች በፋይናንስ ችግር ምክንያት በአልባሌ ቦታዎች እንዲውሉ የሚገደዱበት ሁኔታ አለ። ይህንን ችግር ለመፍታት የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግላቸውና ብድር የሚዘጋጅላቸው መንገድ ተመቻችቷል።

ከጥቃቅንና አነስተኛ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ችግር የስልጠና ጉዳይ ነው። በጥቃቅንና አነስተኛ የሚሰማሩ ዜጎች በሚሰማሩበት የስራ ዘርፍ ውጤታማ መሆን እንዲችሉ ለማገዝ የተለያዩ ስልጠናዎች በመሰጠት ላይ ነው። 

ከላይ የተገለጹትን መሰናክሎች በመቅረፍ በአገሪቱ የሚገኙ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በሚፈለገው መጠን እንዲስፋፉ እየተደረገ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲያመርቱ በማድረግ የገበያ ችግር ለመፍታት ከገበያ ጋር የማስተሳሰር ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በእነዚህ ተቋማት የሚካሄደው እንቅስቃሴ ለአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬትና ለአገራችን የምጣኔ ሀብት እድገት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

ለኢንዱስትሪው ልማት ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ በአገር ውስጥም ሆኑ በውጭ አገራት ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት የማምረት አቅማቸውን በማሳደግ ለአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት ያላቸው ድርሻ የጎላ እንዲሆን ማድረግ በሚያስችል መልክ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ መልክ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለከተሞች እድገት የሚኖራቸው  ፋይዳ የላቀ እንደሆነ ይታወቃል፡፡  እነዚህ ተቋማት አዳዲስ ባለሃብት የሚፈሩባቸውና  ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መክፈቻ ጭምር ናቸው፡፡

መንግስት አነስተኛና ጥቃቅንን ለማበረታታትና ድጋፍ ለማድረግ የፌዴራል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የተቋቋመው ይኸው ኢንተርፕራይዝ ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለያየ መልኩ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት በመደገፍ ላይ ይገኛል፡፡

የኢንተርፕራይዙ ዋና ዓላማ ለኢንዱስትሪ ልማት አስተማማኝና ሰፊ መሰረተ ያለውን ተወዳዳሪ ዘርፍ መፍጠርና ሰፊ የስራ ዕድል በማመቻቸት ድህነትን ለመቅረፍ ለሚደረገው ጥረት አጋዥ ሚና መጫወት ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ብሎም ተወዳዳሪነትና ቀጣይነት እንዲኖረው፣ የአገሪቱን ልማትና ለማፋጠንና የኢንዱስትሪ ዘርፉ አስተማማኝ መሰረት እንዲኖረው ለማስቻል ጥቃቅንና አነስተኛ  የሚኖራቸው ሚና የጎላ ነው፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች ተቋቁመው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስትና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ስራዎች ልማት ኤጀንሲዎች ተቋቁመው ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በዚህ መልክ በአገሪቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ከመቻሉም ባሻገር በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጎች ሰፊ ልምድ እንዲቀስሙ የተለያዩ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል።

የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለቴክኖሎጂ ሽግግር አመቺ ሁኔታ በመፍጠር ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከተለያዩ አገራት የሚገዙ ቁሳቁሶችን በአገር ውስጥ አምርቶ በመተካት ረገድ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

አገሪቱ ከተለያዩ አገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየገዛች የምታስገባቸውን የኢንዱስትሪ ውጤቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ ከሚመረቱ ምርቶች መካከል የብሎኬት ማምረቻ፣ የተሻሻሉ የንብ ቆፎዎች፣ ትራድል ፓምፖች፣ የቀላል ማሽነሪዎች መለዋወጫዎችና ሌሎች ተመሳሳይ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በኢንተርፕራይዞቹ በማምረት መጠቀም የሚያስችል  አሰራር ተዘርግቷል።

በጥቃቅንና አነስተኛ እየተሰማሩ ያሉ ወጣቶች የፈጠራ ችሎታቸውን እያሳደጉገ በመምጣታቸው በርካታ ወጣቶች ስኬታማ እየሆኑ የመጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
አገሪቱ በጥቃቅንና አነስተኛ እያስመዘገበችው ያለው ለውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ የተነሳ በጋና አክራ በተካሄደው 18ኛው የዓለም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች  ጉባኤ ላይ  ኢትዮጵያ 20ኛውን የዓለም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጉባኤን በ2014 ዓ.ም እንድታዘጋጅ መመረጥ ችላለች። ለዚህ ምርጫ የበቃችው በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እያመጣች ያለውን ለውጥ ተከትሎ ነው። 
አገሪቱ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት  ዙሪያ መለስ ርብርብ በመደረጉና በዘርፉ የተሰማሩ አመራርና ሠራተኞችን እንዲሁም የአንቀሳቃሾችን አመለካከት በማስተካከል ለዘርፉ የሚመጥን ልማታዊ አስተሳሰብና ተግባር እንዲፈጠር ለማድረግ ቀላል የማይባል ጥረት ተደርጓል። 

ዘርፉ ከተሰጠው ትኩረት ምክንያት የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርኘራይዝ ልማት አንቀሳቃሾችን 81 G14 የማምረቻ ማዕከላት፣ 81 G14 የምርት መሸጫና ማሳያ ህንፃዎች በማጠናቀቅ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ ተችሏል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በምግብ ዝግጅትና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ አንቀሳቃሾችን የመሥሪያ ቦታ ችግር ለመቅረፍ እስካሁን ከ2586 በላይ ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ሰነዶች ተጠናቀው ወደ ተጠቃሚዎች  መተላለፋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በ2004 ዓ.ም መንግስት እያከናወነ ባለው የግንባታና የሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎች ለበርካታ አንቀሳቃሾች የገበያ ትስስር ተፈጥሮ ተጠቃሚነታቸው እያደገ የመጣበት ሁኔታ አለ፡፡ እንዲሁም ከ393 ሺህ በላይ ዜጎች አዲስ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ከዚህም ጋር በበጀት ዓመቱ ለ110619 ዜጎች የስራ ዕድል አግኝተዋል፡፡

በተጨማሪ ለኢንተርኘራይዞች የገበያ ትስስር ከመፍጠር አንፃር በበጀት ዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር የገበያ ትስስር ተፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም ዘርፉን ለማነቃቃትና ተዘጋጅተው የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርኘራይዞችን የሥራ ውጤቶች የማሳየት፣ የገበያ እድል መፍጠር እና የኅብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዘርፉ ልማት ፕሮግራም ታቅፈው ሲንቀሳቀሱ ከቆዩት ውስጥ ሀብት ፈጥረው ወደተሻለ ደረጃ መሸጋገር የደረሱ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ታዳጊ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር ተችሏል፡፡

ለአብነት ያህል በአዲስ አበባ ከተማ በ2003 ዓ.ም በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ከሚገኙት ውስጥ 84 በኮንስትራክሽን፣ 133 በብረታ ብረትና እንጨት፣ አስር በምግብ ዝግጅት፣ አምስት በከተማ ግብርና፣ ዘጠኝ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ስድስት በመዘጋጃ ቤታዊ እና ሶስት በፕላስቲክ ማስታወቂያ ስራ በአጠቃላይ 250 ኢንተርፕራይዞች 1687 የኢንተርፕራይዙ አባላት ወደ ጀማሪና መካከለኛ ኢንዱስትሪ በመሸጋገር በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና በማግኘት ተሸላሚ ሆነዋል። እነዚህ ኢንተርፕራይዞች  ለ2695 ዜጎች ቋሚና 4523 ጊዚያ የስራ ዕድል ፈጥረዋል።

በኦሮሚያ ክልል በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጀተው ከሚገኙ 35738 ኢንተርፕራይዞች 38881 አባላት ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በ2004 ዓ.ም 68 ማህበራትና አንድ ሺህ ያህል አባላት ወደ ጀማሪ መካከለኛ ኢንዱስትሪነት ባለቤትነት በመሸጋገር በክልሉ መንግስት ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።  

በጥቃቅንና አነስተኛ የተሰማሩ ዜጎችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና ያለባቸውን የእውቀትና የክህሎት ክፍተት ለመሙላት ለአንቀሳቃሾች በተለያየ ጊዜ በምርታማነት ማሻሻያ፣ በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ በኮሌጆችና ተቋማትና  በኮብል ስቶን ኘሮጀክት ጽህፈት ቤት የቴክኒክ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

የጥቃቅንና አነስተኛ ሌላው ተግዳሮት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በዘርፉ የተደራጁ አንዳንድ ኃይሎች በልማታዊ መንገድ ለፍተውና ደክመው ሀብት ከመፍጠር ይልቅ ሁሉንም ነገር ከመንግስት መጠበቅና በአቋራጭ ለመክበር የመፈለግ ዝንባሌና ተግባር መታየቱ አልቀረም፡፡

ሌላው ተግዳሮት ደግሞ በወጣቱ ዙሪያ ይታይ የነበረው ስራ የማማረጥ ሁኔታ አንዳንድ ሃላፊነት የጎደላቸው የግል ሚዲያዎችና የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት ነን ባዮች በየወቅቱ ዘርፉን በሚመለከት የሚሰጡት የተዛባና መሰረትየለሽ  ሃሳብ ነው። በአሁኑ ወቅት ወጣቱ የጥቃቅንና አነስተኛ በስፋት ይታያል፡፡
መንግስት የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን በአገሪቱ በማስፋፋት ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ተግባራትን መፈፀም ችሏል። ጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ስራዎች ተስፉፍተው ቀጣይነት ያለው እድገት በማምጣት የስራ እድልን በመፍጠርና በምርት ውጤት ጉልህ ድርሻ መወጣት ይችሉ ዘንድ  የተመቻቸ ሁኔታ በማኖር፣ የሴክተሩን ልማት አጋዥ ለሆኑ ተቋማት የአሰልጣኞች ሥልጠና፣ ተስማሚ ቴክኖሎጂ፣ የገበያና የምክር አገልግሎቶችን በመስጠት ሰፊ ስራ ተሰርቷል፡፡ 
ከተከናወኑ ተግባራት አንዱ ስለ ጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ሥራዎች ልማትና መስፋፋት የሚያግዙ የፖሊሲና ስትራቴጂክ ሃሳቦችን በማቅረብ በዘርፉ ከሚሰሩ አንቀሳቃሾች ጋር በመወያየት ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ልማቱን  ለማፋጠን አስፈላጊ የሆኑ የሥልጠና ፍላጎቶችን በማጥናት ተስማሚ የሆኑ የአሰልጣኞች ሥልጠና ፕሮግራሞችን በማዕከል እንዲካሄዱ በማድረግ በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በዘርፉ ያሉ ተግዳራቶችን ለመፍታት ከተወሰዱት ሌሎች አበረታች ተግባራት ዋንኞቹ የሙያ ማሻሻያ፣ የቴክኒክና የሰርቶ ማሳያ ማዕከላት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች እንዲቋቋሙ ማበረታታትና ድጋፍ መስጠት ናቸው፡፡
በዚህ መልክ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለአገሪቱ ማበርከት የሚችሉትን ጠቀሜታ እንዲሰጡ በማድረግ ኅብረተሰቡም ከዚሁ ተጠቃሚ እየሆነ የሚገኝበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
የጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ሥራዎች ስለሚለሙበትና ስለሚስፋፋበት ሁኔታ ከክልሎች ጋር የተቀናጀ የሥራ ግንኙነት መፍጠር፤  ለማስተዋወቅና ለማልማት የሚያስፈልጉ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችን በመምረጥ የቴክኖሎጂና የፕሮጀክት ፕሮፋይሎችን ማዘጋጀትና ማሰራጨት የመሳሰሉ ተግባራት በተቀናጀ መልክ እንዲሰራ መደረጉን መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የምርምር ተቋሞች ጋር የስራ ግንኙነት በመፍጠር ለክፍለ ኢኮኖሚው የገበያ፣ የንግድ ሥራዎችና የሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች መረጃዎችን መሰብሰብ፣ ማጠናቀርና ማሰራጨት፣ የንግድ ትርዒቶችን ማዘጋጀትና ማስተባበር፣ በድርጅቶች መካከል የእርስ በርስ ግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ ቁርኝት የማድረግ አስፈላጊነትን በማስተዋወቅ ተገቢውን ሁሉ እገዛ መደረጉን የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ስለ ጠቅላላ ጥራት አስተዳደርና በድርጅቶች መካከል በውል ሊፈጥር ስለሚችል የሥራ ቁርኝት አሠራር ማስተዋወቅና ማዳበር፣ የጥቃቅንና የአነስተኛ ንግድ ሥራዎች የድጋፍ አገልግሎት ለመስጠት አቅም ለሚያንሳቸው ክልሎች አቅማቸውን እስከሚያጎለብቱ ድረስ ማንኛውንም እገዛ  መስጠት፣ ለአገልግሎቶቹ ዋጋ ማስከፈል፣ የንብረት ባለቤት መሆን፣ ውል መዋዋል፣ በስሙ መክሰስና መከሰስ፣ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተግባራት በማከናወን ለጥቃቅንና አነስተኛ መስፋፋት አስፈጊው ሁሉ ለማድረግ ተሞክሯል። 
መንግስት የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የስራ አጥነት ችግርን በመቅረፍና ለኢንዱስትሪው ምጣኔ ሀብት መሰረት መፍጠር የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡

በተጨማሪም ቀደም ሲል ሲሰሩ የነበሩ የማስፋፋትና የማጠናከር ተግባራትን ለማጎልበትና የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ከ2003 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ባለው ጊዜ ለሶስት ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ ተይዞ እየተሰራበት ይገኛል።

ከእነዚህ መካከልም 50 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንደሚሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህንን ተግባር በተገቢው መንገድ ለማፋጠን ደግሞ ሶስት ሚሊዮን ለሚሆኑ አንቀሳቃሾች በተለያዩ ሙያዎች ስልጠናዎች ይሰጣሉ።

በእቅዱ መሰረት በመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን አመርቂ ውጤት የተገኘበት ስራ ተከናውናውኗል።

በዘርፉ ለሚሰማሩ ዜጎች እያጋጠሙ ካሉት ዋናዋና ተግዳራቶች አንዱ የሆነው የፋይናንስ አቅም ማነስ በመሆኑ የብድር አቅርቦት በየበጀት ዓመቱ እመጨመረ መጥቷል፡፡ በ2004 ዓ.ም የቀረበው የብድር አቅርቦት በ2000 ዓ.ም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በሶስት እጥፍ ማደጉን ማየት ይቻላል።

ዘርፉ በርካታ ተግዳራቶች ያጋጠሙት ቢሆንም ተግዳራቶቹን በመፍታት ውጤታማ እየሆነ ያለ የልማት ዘርፍ ነው።
በዘርፉ እስካሁን የታዩትን ስኬቶች በማጠናከር በቀጣይ ሶስት አመታት በሚደረገው የተጠናከረ ጥረት ለኢንዱስትሪው መሰረት የሚጥል ዘርፍ ላይ ይገኛል።