ምርጫው ይሳካል! ሴራውም ይከሽፋል!!

  • PDF

አስቻለው ይልቃል

ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ75 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአዳማ ከተማ ጥሪ አደረገ፡፡ በመጪው ሚያዝያ በአዲስ አበባና በክልሎች የሚካሄደውን የማሟያ ምርጫ በተመለከተ ውይይት ለማድረግ ነበር፡፡ ውይይቱ ስለመጪው ምርጫ እንጂ ስላለፉት ምርጫዎች አልነበረም፡፡

ባለፉት ምርጫዎች ሂደትና አሰራር ላይ መነጋገር አለብን፤ ከዚህ ቀደም የነበሩ ምርጫዎች ሁሉ የየራሳቸው ችግር ነበራቸው የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ተሰነዘሩ፡፡
ስለዚህም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለተባሉት ጥያቄዎች መልስ መስጠት ጊዜ ይጠይቃል በማለቱ ስብሰባው በሌላ ቀጠሮ  ተላለፈ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከአዳማው ስብሰባ በፊትና በኋላ በተናጠል ፓርቲዎቹን ወይንም ድርጅቶቹን የማስተባበርና ወደ አንድ አቋም የማምጣት ስራ ሲከውን የከረመው አንድነት /መድረክ/ ፓርቲ ነው፡፡

የአዳማውን ስብሰባ በመነሻነት በመጠቀም ጥቅምት 25 ቀን 2005 ዓ.ም በጽህፈት ቤቱ ፓርቲዎች የጋራ ስብሰባ እንዲያካሂዱ ባደረገው ጥሪ ከ75ቱ ውስጥ  34 ድርጅቶች ተገኙለት፡፡

እነዚህ ድርጅቶች አብዛኛዎቹ ክልላዊ ናቸው፡፡ ጥቂቶች ብቻ ናቸው በብሔራዊ ደረጃ የተደራጁት፡፡ የምርጫ ሰሞን ብቻ እየተደራጁ ብቅ የሚሉ የመስቀል ወፎችም አሉ፡፡ ኢትዮጵያን በመሰለ አገር 75 ፓርቲ ወይንም የፖለቲካ ድርጅት ምን እንደሚሰራ መቼም ጉድ ያለው ነገር ነው፡፡

ከአንድ ወዳጄ ጋር በቅርብ ቀን በዚሁ ጉዳይ ላይ ስንነጋገር ኢትዮጵያ ውስጥ ቀላሉ ነገር የፖለቲካ ፓርቲ ወይንም ድርጅት ብለህ ማቋቋም ነው፡፡ ስሙን መያዝ ብቻ የሚፈልጉ

ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ፈተናና ችግር እንዳለው ከባድ ኃላፊነትም እንደሆነ በውል አይረዱትም አለ፡፡

አሁንማ የጉዱ ጉድ  ወርደው በየቀበሌው አንድ አንድ ፓርቲ ማቋቋም ነው የቀራቸው፡፡ በምጣኔ ሀብት እድገት የላቁና የበለፀጉ አገራት ግፋ ቢል ከአራትና ከአምስት የዘለለ ፓርቲ የላቸውም፡፡

ከእነዚህም ዋና የሚባሉት  የዴሞክራቲክ ፓርቲ፤ የሌበር ፓርቲ፤ የሪፐብሊካን ፓርቲ ወይንም የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ለሆኑ ይችላሉ፡፡ እንደ ግሪን ፓርቲ፣ ኮሚኒስት ፓርቲ የሚባሉም ይኖራሉ፡፡ የትም ዓለም ላይ ቢኬድ በድሀውም ሆነ በበለፀገው አገር የእኛ  ዓይነት 75 ፓርቲ ያለው አገር የለም፡፡

በትላልቅ ብሔራዊ ዓላማዎች ዙሪያ  በእምነት፣ በአስተሳሰብና በርዕዮተ ዓለም መሰረት ተደራጅተው በጋራ ቆመው ለአገራቸው ይሰራሉ እንጂ እንዲህ ዓይነት ክስተትና ክፍተት አይታይም፡፡ ወደፊት የሚያስፈራው 80 ሚሊዮን ፓርቲ በዚህች ድሀ አገር እንዳይኖር ነው፡፡ ያኔ ነው መፍራት አለኝ ወዳጄ፡፡

በየራሳቸው የውስጥ ምክንያት ተተብትበው  ያሉ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የአገር አደራ ለመረከብ ቀርቶ  የራሳቸውን ችግር ፈትተው፤ መደማመጥን አጎልብተው፤ በጋራ  ለመቆም በጋራ ለመስራት የሚያስችል የሰለጠነ  ፖለቲካዊ ባህል አላዳበሩም፡፡ አልገነቡም፡፡

ከበርካታ ዓመታት ተሞክሮ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያየነው ተደጋጋሚና ያፈጠጠ የማይካደው እውነት ይኸው ነው፡፡ በአንድነትና በፍቅር  ሊሰባሰቡና ሊደማመጡ አይችሉም፡፡ ቢሰባሰቡም ቆይታቸው ጥቂትና የወረት ነው፡፡ ወዲያው መባላት ይጀምራሉ፡፡ ግርግር ሲፈጥሩ፤ ሕዝቡንም ጋራ ሲያጋቡት፤ በፕሮፖጋንዳ ሲያምሱት፤ በሌለ ነገር እውነት አድርገው የተጨበጠ ያህል ሲናገሩ፤ በበነጋታው ውሸት ሆኖ ሲገኝ ነው ሕዝቡ ያየው፡፡ የሚመሰክረውም፡፡


አንቱ የተባሉት ምሁራን፣ እድሜ የጠገቡ አዛውንቶች  ለአገር መላ ያመጣሉ ሲባል እንደ አፍላ ጎረምሳ ቡጡ ሲሰናዘሩ፤ ሲፈናከቱ፤ እጃቸውን ለቦክስ ሲጠቀልሉ፣ በስም መጠፋፋት ሲወነጃጀሉ፤ አንዱ አንዱን ሲከስ፣ በሌላው ሲረማመድ ነው ስንትና ስንት ዓመት የታዘብናቸው፡፡ በቃችሁን የማለት ሙሉ መብት አለን፡፡

የሰለጠነ ችኮ መንቻኬ ከሆነ አንጆ ፖለቲካ የወጣ፤ ጥላቻን በቀልን የረገመ፤ ቂም አርግዞ የጥፋት ቀንን የሚጠብቅ ሳይሆን ለሰላምና ለአገር እድገት የሚሰራ ተቃዋሚ ነው የሚያስፈልገው፡፡

ለውጥ እናመጣለን ብለው ከውጭ የሚመጣ ገንዘብ ረጭተው፤ ወጣቱን በስሜታዊነት ቀስቅሰው፤ እሳት ውስጥ ማግደውት የሕይወት ዋጋም አስከፍለውት ሲያበቁ እነሱ መሰስ ብለው አውሮፓና አሜሪካ ገብተው ሲቀመጡ ነው ያየናቸው፡፡

ዛሬም መቼም አመል አይደል  አውሮፓና አሜሪካ ሆነው ያንኑ ገንዘብ እያሳባሰቡ ወደ አገር ቤት እየላኩ፤ የድሀውንና የለፍቶ አዳሪውን ልጅ ውስጥ ለውስጥ እየቀሰቀሱ፤ በጥላቻ ባህር እንዲዋኝ፤ ወጥቶም እንዲበጠብጥ፣ እንዲረብሽ፤ የአገር ሰላም እንዲታወክ፤ እዚህ ካሉ ጎምቱ ጀሌዎቻቸው ጋር እያሴሩ፤ እየመከሩ፤ እየዶለቱ ነው፡፡ ሕዝብም ልጆቹም ከትናንትም፣ ከታሪክም እነዚህ ዓይነት ተቃዋሚዎች እነማን እንደሆኑ ጠንቅቆ አውቋቸዋል፡፡ ለእነሱም መሳሪያ አይሆንም፡፡ 

በአዲስ አበባ የአካባቢና የማሟያ በክልሎች ደግሞ የማሟያ ምርጫ በሚያዝያ ወር ውስጥ ይካሄዳል፡፡ ይህን በተመለከተ የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ሁነኛ ምንጫቸው ወደሆነው የአውሮፓና የአሜሪካ ነዋሪ ዲያስፓራ አንድነትና የመድረክ አመራሮች በተደጋጋሚ ተጉዘዋል፡፡ ምክርም ውይይትም አድርገዋል፡፡

በዚህ ፈንድ የማሳበሰብ ዘመቻ አሜሪካን ከሄዱት እነ ስዬ አብርሃ፣ በሌላም በኩል በፅንፈኛት ከተሰለፋት ተቃዋሚዎች ጋር ሀሳብ መለዋወጣቸውም ይታመናል፡፡ አንድነትና

/መድረክ/  ከዲያስፓራው በአፅንኦት የተሰጣቸው ማሳሰቢያ በቀጣዩ የሚያዝያ ምርጫ በአድማቂነትና በአጃቢነት መሳተፍ የለባችሁም የሚል ነው፡፡

ሌሎች ተቃዋሚ ነን የሚሉ ፓርቲዎችን በጋራ ማስተባበር፤ ምርጫ  ቦርድም ሆነ ኢሕአዴግ በባሕርይው ሊመልሳቸው የማይፈልጋቸውን ጥያቄዎች በጋራ  ፊርማ ማቅረብ፤ መልስ አልሰጥም ሲል ሕዝቡን ቀስቅሶ ማስወጣት፤ የግል ጋዜጦችንና መጽሄቶችን በገንዘብ መደገፍና በተደጋጋሚ እየተከታተሉ እንዲዘግቡ ማድረግ፤ የውጭ ሚዲያን መጠቀም፤ ውጥረቱን ማባባስና የኢሕአዴግን መንግስት በፍጥጫ ማስገደድ  ወቅታዊ ስልታቸው ነው፡፡

እንደ ቀድሞው ሁሉ በገንዘብ በኩል ችግር አለ ብላችሁ እንዳታስቡ፡፡ ገንዘቡ ይኽው፤ ከእናንተ የሚጠበቀው  ፈጥኖ መንቀሳቀስ ብቻ ነው የሚለውን ቀጭን ትዕዛዝ ተቀብለው በመምጣት ነው እነ አሥራት ጣሴ ሥራ የጀመሩት፡፡

እነዚህን ፓርቲዎች ወይንም የፓለቲካ ድርጅቶች ያስተባበረው  አንድ አቋም ይዘው 18 ጥያቄዎች ወጥቶ በቅድሚያ በአንድነት /በመድረክ የወጡ ናቸው የይስሙላ ውይይት ተደርጎ እንዲፈራረሙ ለምርጫ ቦርድም እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ምርጫ ቦርድ  ግዜ ይሰጠኝ ብሏል፡፡ ሌሎች 41 ፓርቲዎች ደግሞ ከምርጫ ቦርድ ጋር ተመካክረው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

አንድነት /መድረክ/ በራሳቸው በኩል ባደረጉት ግምገማ በተለይ አንድነት በአዲስ አበባ ደረጃ በትክክል አለኝ ብሎ ያስቀመጠው አባል ከ500 አይበልጥም፡፡ አዲስ የተመሰረተውም ሰማያዊ ፓርቲ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ የሚመራው ገና ወራት ያስቆጠረ ፓርቲ ነው፡፡ ከልምድም ከተሞክሮም አንፃር ብዙ ይቀረዋል፡፡

በመድረክ ስር የተደራጁት፤ በዓላማ፤ በግብ፤ በርዕዩተ ዓለም፤ ጭርሱንም የማይገናኙ ናቸው፡፡ ያሰባሰባቸው ዋና ጉዳይ ኢሕአዴግን በጋራ ተረባርበን መጣል አለብን የሚለው ነው፡፡ በኋላስ የሚለው ጉዳይ በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፋክክር ሕዝቡንና አገሪቱን የማያባራ ቀውሰ ውስጥ ሊከት የሚችል መሆኑን ምንም አያስተውሉም፡፡ ደንታም የላቸውም፡፡

በመድረክ ውስጥ አንድነት ፓርቲ፣ አረና ፓርቲ (ስየና ገብሩ)፤ ኦብኮ (የዶክተር መረራ ጉዲና)፤ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ (የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ)፤ ኢፌዴን (የእነ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ)፤ ሌሎችም ይገኛሉ፡፡ የሊበራል ዴሞክራሲ፤ የሶሻል ዴሞክራሲ መርህ፤ ሌሎችም በጎሳ ላይ የተመሰረተ ፓለቲካ አራማጆች ናቸው፡፡ 34 የተባሉት ፓርቲዎች በዚሁ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡

34ቱ ፓርቲዎች /ድርጅቶች/ ከኢሕአዴግ ጋር በመሆን የሚመካከሩበትና ችግሮቻቸውን በጋራ የሚፈቱበት የጋራ ምክር ቤት አላቸው፡፡ መድረክ ደግሞ የሥነ ምግባር ደምቡን አልፈርምም በማለቱ በጋራ ምክር ቤቱ አባል አይደለም፡፡ ይህም ኢዴፓ የሚባል ፓርቲ ባለበት አልሳተፍም በማለቱ ነው፡፡

ይህ ደግሞ መስረታዊ ስህተት ነው፡፡ ኢዴፓ ራሱን የቻለ የራሱ አመለካከትና መስመር ያለው ሕጋዊ ፓርቲ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊ ፓርቲነቱ በምክር ቤቱ የመገኘት መብት አለው፡፡ መድረክ ኢዴፓን ያለመፈለግ መብቱ የተጠበቀ  ቢሆንም ሕጋዊነቱን የመሰረዝ ወይንም በምክር ቤቱ አልይህ የማለት መብት ግን የለውም፡፡

34ቱ ፓርቲዎች አምነውና ፈርመው የተቀበሉት አይዲኤ ያወጣውና ተተርጉሞ ወደ አማርኛ የተለወጠው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፓርቲዎች ስነ ምግባር ደምብ እያለ ይህንን አልቀበለም ያለው መድረክ እንዴት አድርጎ ፓርቲዎቹን ማሰባሰብ ቻለ? እነዚህ 34 ፓርቲዎች አለ የሚሉትን ችግር በጋራ መድረካቸው ላይ ለምን አያነሱትም ነበር? ከዚህ ውጪ መሄድስ ለምን አስፈለገ?

ለመድረክ አጃቢነት ወይንስ መድረክ ጥያቄዎቹ ካልተመለሱ ሕዝባዊ ንቅናቄ እፈጥራለሁ፣ ሰላማዊ ስልፍ እጠራለሁ፤ ለሚለው ሕገ ወጥ አካሄዱ ተባባሪና  አጋዥ ወይንም  ተዋናይ ለመሆን?  አንድነት ፓርቲ ህዳር 7 ቀን 2005 ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለመፍጠር ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ይህንንም ልብ ይሏል፡፡
አንድነትና መድረክ አሁን ገዥው ፓርቲ ካለው አምስት ሚሊዮን አባላት አንፃር በየቀበሌውም ብንወደደር አናሽንፍም፣ ይህንን ሽንፈት ተሰልፈን ከምንቀበል፤ ማን አሸናፊ እንደሚሆን ስለሚታወቅ “ ምርጫው ተጭበርብሯል!” ማለታችን አይቀርም፡፡ ከዚህ ሁሉ ከምርጫው በፊት የማይመለሱ ጥያቄዎች አቅርበን ግርግርና ሁከት መፍጠር አለብን ብለው ነው የተነሱት፡፡

ይህማ ባይሆን ኖሮ ስለ ወደፊቱ ምርጫ እንነጋገር ሲባል የለም ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ስለነበረና ስላለፈው ምርጫ ነው መነጋገር ያለብን እንዴት ይባላል? ለዚያውም ባለፉት ምርጫዎች ላይ ሁሉ የተደረሰበትን ውጤት ምርጫ ቦርድ ተቃዋሚዎችን ጠርቶ አወያይቷል፡፡  ሀሳባቸውንም፣ አስተያየታቸውንም ተቀብሏል፤  ይታረም ይስተካከል ያሉትን ሁሉ፡፡ እናሳ ምን እየተደረገ ነው?

በአንድነትና በመድረክ መሪነት ሌሎችን አጋፋሪ በማድረግ ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥ ምርጫ ቦርድ ኢሕአዴግ ነው፣ በምርጫ ቦርድ ውስጥ መግባት አለብን፣ ፍርድ ቤቶች ነፃ አይደሉም፣ ለተቃዋሚው መተንፈሻና ልሳን የነበሩት አንድም ነፃ ፕሬስ በአገሪቱ ውስጥ የለም (ያሉት ሁሉ ፎርቹን፣ ካፒታል፣ ሪፖርተር፣ አዲስ አድማስ፣ ሰንደቅ፣ የኛ ፕሬስ፤ ሰሞኑን ደግሞ ልዕልና እና  ኢትዮ ምሕዳር ወጥተዋል - በእነሱ ዓይን ኢህአዴግ ናቸው፡፡)
ጋዜጦችና መፅሄቶች እንዳሻቸው የሚፅፉትና የሚነቅፉትን ሁሉ የኢሕአዴግ ናቸው ማለት ነው) ሲቪክ ማህበራትን ለ97 ምርጫ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡   አሁን የሉም .. የታሰሩ አባሎቻችን ይፈቱ ወ.ዘ.ተ… መቋጪያው እነዚህ ጥያቄዎች  ካልተመለሱ፤ በቀጣዩ ምርጫ አንሳተፍም፤ እንዲያውም ሕዝቡን ቀስቅሰን ሆ! ብለን ስልፍ እንወጣለን! እናስወጣለን ነው፡፡ ሴራው፡፡ መጀን! አሉ የአገሬ ሼሆች! አገር ላይ እሳት ለማንደድ መክለፍለፍ ምን የሚሉት እርግማን ነው?

ሲመኙት፤ ሲጓጉለት፤ ብዙ ውስጥ ውስጡን መክረውም ያልተሳካላቸውን የዐረቡን ዓለም አብዮት ዓይነት ኢትዮጵያ  ውስጥ እናመጣለን፤ ቢፈልግ እሳት ይንደድ፤ ይቀጣጠል፤ የወደመው ይውደም፤ የጠፋውም ይጥፋ፣ ልማትም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታም ይቁም፣ ያለቀው አልቆ እኛ ብቻ በኃይልና በአመፅ ለስልጣን መብቃት አለብን ነው የሚሉት፡፡
በአጭሩ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ የምርጫ ሂደትን አንቀበልም፡፡ ብንወዳደርም እንሽንፋለን፣ ስለዚህ ያለን እድል ረብሻና ብጥብጥ መፍጠር ነው ብለው ወስነዋል፡፡

ለእዚህ ተግባራቸው እንዲረዳቸውም ጥቂት አክራሪ ፅንፈኛ ሙስሊሞች ለመጫር የሞከሩትን እሳት ሕጋዊ እንቅስቃሴና የመብት ጥያቄ ነው በማለት በመግለጫና በየጋዜጣው እያበረታቱ አንድነትና መድረክ ከጎናችሁ ነን እያሏቸው ነው፡፡ አሜሪካን የሚገኘውና ጦርነት ያወጀው የዶክተር ብርሃኑ ነጋ ግንቦት ሰባትም ከጀርባ ሁኖ እየገፋ ይገኛል፡፡

ይህ ኃላፊነትና የዜግነት አገራዊ ግዴታን በውል መገንዘብ ያልቻለ፤ በኢትዮጵያ ብጥብጥ ሁከትና ደም መፋሰስ እንዲነሳ፤ ሥርዓተ አልበኝነት እንዲሰፍን፣ አገሪቱ የጀመረቻቸው ተስፋ ሰጪ የልማትና የእድገት ጉዞዎች እንዲገቱ፤ የትርምስ ማዕከል እንድትሆን የተጠነሰሰውን ሴራ ሕዝቡ አስቀድሞ ተገንዝቦታል፡፡

አገርም ሕዝቡም ተጠቃሚ የሚሆኑት፤ የሚያድጉት፤ ሰላም ሲኖርና ተባብሮ መስራት ሲቻል ብቻ ነው፡ ይህንኑ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ አንድነትና መድረክ ወጣቱን ዓላማ አድርገው፤ በየመንደሩና ሰፈሩ፤ በየትምህርት ቤቱ፣ በኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በነጋዴውና በሠራተኛው፤ በነዋሪው ውስጥ ውስጡን መርዘኛ ቅስቀሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ በቤተክርስቲያናትና በየእድሩም ሳይቀር፡፡

መስጂዶችን  ለእነዚያኞቹ  ትተው እየተደጋገፉ ነው፡፡ በሰላም አገር ሕግን አክብሮ መስራት መነጋገር እየተቻለ፤ በአገርና በሕዝብ ላይ እሳት በመቆስቆስ፤ የጥፋትና የውድቀት ድግስ መደገስ አገርን ለማጥፋትና ለማውደም ማሴር ጤነኛ ዜጋ የሚያስበው ሀሳብ ሊሆን አይችልም፡፡

እኛ ስልጣን ካልያዝን አገር ትውደም፤ ወጣቱም ይለቅ፣ ለምን ዙሪያውን እሳት አይነድበትም የሚሉ፤ በጥላቻ  ያበዱ አውሬ ፓለቲከኞችን ይህቺ አገር አታስተናግድም፡፡ እድሉን ቢያገኙ እጅግ ደም የጠማቸው አምባገነኖች እንደሚሆኑ ድርጊታቸውና አስተሳሰባቸው  በተጨባጭ ይናገራል፡፡
እነዚህ ወገኖች  ያልተረዱት ነገር ቢኖር የጫሩት ወይንም ያስነሱት እሳት በቅድሚያ እነሱን የሚያነድና የሚያቃጥል መሆኑን ነው፡፡ ማንም በአገር ሰላምና እድገት ላይ ሊቀልድ አይችልም፡፡ እሳት ለኩሶ ከዳር ተቀምጦ መሞቅም አይቻልም፡፡

ወጣቱም ሕዝቡም ለእዚህ  እኩይ ዓላማቸው መጠቀሚያ መሳሪያ አይሆንም፡፡ የራሱንም የአገሩንም ሰላም አጥብቆ ይወዳልና፡፡ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ይመርጣል፡፡ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ የተጠነሰሰውም ሴራ ከሽፎ በድል ይጠናቀቃል፡፡ ህዝቡ አያችሁ! አያችሁ! ከኢህአዴግ ውጭ አማራጭ የለውም፡፡ አማራጭ ለመሆንም አልቻላችሁም፡፡ ያፈጠጠው እውነት ይኸው ነው፡፡