ከታዳጊ አገራት ዜጎች የሚላከው ገንዘብ ማደጉን የተመድ አስታወቀ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2005 (ዋኢማ) - በማደግ ላይ ባሉ አገራት ዜጎቻቸው ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ የሚልኩት የገንዘብ መጠን ዕድገት ማሳየቱን የተባበሩት መንግሥታት ንግድና ልማት ጉባዔ የታዳጊ አገራት የ2012 ሪፖርት አመለከተ።

ዜጎቹ የሚልኩት የገንዘብ መጠን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1990 ከነበረው 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን በ2011 ወደ 27 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማደጉን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

በተባበሩት መንግሥታት ንግድና ልማት ጉባዔ የአፍሪካ ታዳጊ አገራት ክፍል ኃላፊ አቶ ተስፋቸው ታፈረ ሪፖርቱን ዛሬ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋ ሲያደርጉ እንደተናገሩት የ48 ታዳጊ አገራት ዜጎች ከውጭ አገር ወደ አገራቸው የላኩት የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል።

ዜጎች ከውጭ አገር ወደ አገራቸው የሚልኩት የገንዘብ መጠን በየዓመቱ ዕድገት እያሳየ በመሆኑ አገሮች ገንዘቡን በአግባቡ ሥራ ላይ የሚያውሉበት ሕግ ሊያወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል። እንዲሁም ዜጎቹ ገንዘባቸውን በሚልኩበት ወቅት ከ12 እስከ 25 በመቶ ክፍያ የሚያስከፍሉ በመሆናቸው በትክክለኛ መንገድ ከመላክ ይልቅ ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ በአብዛኛው እንደሚልኩ ጠቁመዋል።

በኢኮኖሚ ካደጉ አገር ይልቅ ታዳጊ በሆኑት 48 አገራት ዜጎች ከውጭ አገር ገንዘብ በሚልኩበት ወቅት ከፍተኛ ክፍያ የሚያስከፍሏቸውና የባንክ ሥርዓቱ ገና በማደግ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ገንዘባቸውን ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ለመላክ እንደሚገደዱ ጠቁመዋል።

ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ አገራቱ የገንዘቡ ተጠቃሚ ስለማያደርጋቸው በዓለም አቀፍ ያለውን ከ4 እስከ 6 በመቶ አሰራርን ሊከተሉ እንደሚገባም ሪፖርቱ ጠቁሟል። ከ48ቱ ታዳጊ አገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ከሚልኩት ገንዘብ አገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ የዲያስፖራ ፖሊሲ ማውጣቱ እንደ ጥሩ ማሳያ በሪፖርቱ ተጠቅሷል። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የሚልኩት የገንዘብ መጠን የዓለም ባንክ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ሲያስቀምጥ በተባበሩት መንግሥታት ንግድና ልማት ጉባዔ የአፍሪካ ታዳጊ አገራት ክፍል ደግሞ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ይገልጻል።

ታዳጊ አገራት ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ጎራ ለመቀላቀል የአገር ውስጥ የነፍስ ወከፍ ገቢ 1 ሺህ ዶላር ማድረስ፣ የሚሌኒየም የልማት ግቦችን በአብዛኛው ማሳካትና በዓይነትና በብዛት ወደ ውጭ የሚልኩት ምርት ሊኖራቸው ይገባል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ እንደ አውሮፓጳውያን አቆጣጠር በ2020 ከ48ቱ ታዳጊ አገራት ውስጥ ግማሾቹ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ጎራ ሊሸጋገሩ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።