ኤርትራውያን የአስመራውን መንግስት ለመጣል በሚካሄደው ትግል እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀረበ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2005(ዋኢማ) - መላው ኤርትራውያን አምባገነኑን የአስመራ መንግስትን ለመጣል በሚካሄደው ትግል እንዲቀላቀሉ የኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ብሔራዊ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።  

የምክር ቤቱ ሊቀመንበር አቶ ጸጋዬ ዮሃንስ ዛሬ በአዲስ አበባ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ  ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ እንደተናገሩት፤ በኤርትራ ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ መላው የሀገሪቱ ዜጎች በኤርትራ  መንግሥት ላይ የሚደረገውን ዴሞክራሲያዊ ትግል እንዲቀላቀሉ ጥሪ  አቅርቧል፡፡  

ምክር ቤቱ እ.ኤ.አ. ህዳር 2011 በሃዋሳ ከተማ ከተመሠረተ በኋላ በውጪ በሚኖሩ ኤርትራውያን ወደ ዴሞክራሲዊ ትግሉ እንዲቀላቀሉ የመቀስቀስ ስራ መሰራቱን ጠቁመው፤ ትግሉን በኤርትራ ውስጥ ለማካሄድ አመቺ ባለመሆኑም በውጪ በመሆን ትግሉን ለማካሄድ መምረጡን ገልፀዋል። 

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክር ቤቱን በተለያዩ መንገዶች እየደገፈች መሆኗን የገለፁት አቶ ፀጋዬ፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የኤርትራን ህዝብ ከአምባገነኑ ስርዓት ለማላቀቅ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበሩም አስታውሰዋል።

የብሔራዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ ፍሬወይኒ ሀብተማርያም በበኩላቸው፤ በኤርትራ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ወደ ከፋ ደረጃ በመሸጋገሩ መላው ኤርትራውያን በጋራ በመነሳት አምባገነኑን ስርዓት ለመጣል መታገል ይኖርበታል ካሉ በኋላ ምክር ቤቱም ህብረተሰቡን የማስተባበሩን ስራ በላቀ ሁኔታ ያካሂዳል ብለዋል።

ሌላው የብሔራዊ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዩሱፍ ብርሃን የኤርትራው መንግስት በህዝቡ ላይ ከሚያደርሰው ጭቆና በተጨማሪም በቀጠናው ያለውን ሰላም በማደፍረስ ላይ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ትዕግሰት ብርሃን በዛሬው ዕለት የተጀመረው ውይይት ትግሉን ለማካሄድ እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ ለትግሉ እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ በማውጣት መላው ኤርትራውያንን በአንድ ጠረጴዛ እንዲወያዩ የሚያስችል ነው በማለት ገልፀዋል።

ስብሰባው ከዛሬ ጀምሮ ለሰባት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ ከአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ፣ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የሚኖሩ የኤርትራውያን ሲቪክ ማህበራት፣ የሴቶችና የወጣቶች ማህበራትን የሚወክሉ ተወካዮች መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።