ኤጀንሲው ከ16 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ፕሮጀክቶች ፈቃድ ሰጠ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2005(ዋኢማ) - የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ በሩብ የበጀት ዓመቱ ከ16 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ፕሮጀክቶች ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ።

በኤጀንሲው የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አስቻለው ታደሰ ዛሬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ ፈቃዱ የተሰጠው በኢንዱስትሪ፣ በኮንስትራክሽን፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ ግብርናና በሌሎች የኢንቨስትመንት መስክ ለማሰማረት ጥያቄ ላቀረቡ 220 ፕሮጄክቶች ነው።

ፈቃድ የተሰጣቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከባለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በፕሮጀክቶች ቁጥር በ87 እንዲሁም በካፒታል መጠን ደግሞ ከ4 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ብልጫ ማሳየቱን አቶ አስቻለው ተናግረዋል።

የፕሮጄክቶቹ ቁጥርና የካፒታል መጠኑ ሊጨምር የቻለው ኤጀንሲው ለደንበኞቹ የሚሰጠው የድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ እንደሆነ ባለሙያው ገልፀዋል።

ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀመሩ ለ19ሺ ሰዎች ቋሚና ለ83ሺ ሰዎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ አቶ አስቻለው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ግዴታቸውን ባልተወጡ 306 በሚሆኑ ባለሀብቶች ላይ የፈቃድ ስረዛ ማድረጉን ባለሙያውን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።