ባለስልጣኑ በሩብ የበጀት ዓመቱ ከ22 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2005(ዋኢማ) - የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት 21 ነጥብ 492 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 22 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ የተሰበሰበው ገቢ ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች፣ ከብሔራዊ ሎተሪ የተጣራ ትርፍና ከሌሎች የገቢ ርዕሶች ነው።

ባለስልጣኑ የሰበሰበው ገቢ የዕቅዱን 103 ነጥብ 57 በመቶ መሆኑን ጠቁመው፤ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ38 ነጥብ 53 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ብለዋል፡፡

የተገኘው ገቢ በየታክስ አይነቱ ሲታይ 5 ነጥብ 709 ቢሊየን ከቀጥታና 16 ነጥብ 132 ቢሊየን ቀጥታ ካልሆነ ታክስ የተገኘ ሲሆን፤ 397 ነጥብ 82 ሚሊየኑ ከሌሎች ገቢዎችና 21 ነጥብ 04 ሚሊየን የሚጠጋው ከብሔራዊ ሎተሪ የተጣራ ትርፍ የተገኘ ነው ብለዋል።

በሩብ የበጀት ዓመቱ ከተገኘው ጠቅላላ ገቢ 41 ነጥብ 31 በመቶው ከተጨማሪ እሴት ታክስ የተገኘ ገቢ መሆኑንም አቶ ኤፍሬም ገልፀዋል፡፡

የሚሰበሰበው ገቢ በየአመቱ እያደገ መምጣቱን የጠቆሙት አቶ ኤፍሬም በተለይም በዘንድሮው ሩብ የበጀት ዓመት ለተገኘው ገቢ እድገት ዋነኛ ምክንያቱ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት በሕዝቡና በሠራተኛው በኩል የተፈጠረው ቁጭትና መነሳሳት መሆኑን ገልፀዋል።

እንዲሁም የአገልግሎት አሠጣጥ መሻሻልና የግብር ከፋዩ ግንዛቤ መዳበር ለገቢው ማደግ ተጠቃሽ ከሆኑ ምክንያቶች ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል በሩብ አመቱ ከቀረቡት 947 ጥቆማዎች መካከል 769ኞቹ ትክክለኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል በማለት ገልፀዋል።

በመሆኑም ለ31 ጠቋሚዎች፣ ለ21 ያዦችና ለስምንት ተባባሪዎች 6 ነጥብ 17 ሚሊየን ብር የወሮታ አበል መከፈሉን አቶ ኤፍሬም አስረድተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት 53 የጥቆማ ተባባሪዎች ተመልምለውና ሥልጠና ወስደው ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርገዋል ብለዋል።

በሩብ የበጀት ዓመቱ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ በ5ሺ 516 ተጠቃሚዎች 6ሺ 518 የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን አቶ ኤፍሬም መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።