በሙምባዩ አደጋ የተወነጀለው አሸባሪ በሞት ተቀጣ

  • PDF

አዲስ አበባዕ  ህዳር 17/2005 (ዋኢማ) - እ.ኤ.አ ኅዳር 2008 የሕንድ የንግድ ማዕከል በሆነችው ሙምባይ ከተማ ውስጥ ታጅማሃል ሆቴልን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች የ166 ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት የጠፋበትንና ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰውን አደጋ ከፈፀሙት አሸባሪዎች መካከል አንዱ የሆነው አጅማል ካሳብ ሰሞኑን የሞት ቅጣት ተፈጽሞበታል።

ሮይተርስ ከሙምባይ ያስተላለፈው ዜና እንዳመለከተው፤ የ25 ዓመቱ አጅማል ካሳብ በሞት የተቀጣው በሕንድ ላይ ጦርነት ማወጅንና ነፍስ ግድያን ጨምሮ በ86 ዓይነት ወንጀሎች በቀረበበት ክስ ጥፋተኛነቱ በመረጋገጡ ነው።

አጅማል ካሳብ እ.ኤ.አ ኅዳር 2008 ከፓኪስታን እንደተነሱ ከተነገረላቸውና በታጅማሃል ሆቴል፣ በባቡር ጣቢያና በእሥራኤል የባህል ማዕከል ላይ የሽብር ጥቃት ከፈጸሙት አሸባሪዎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ዘጠኙ በጥቃቱ ሂደት ሲገደሉ እርሱ ብቻ ተርፎ በቁጥጥር ስር ውሏል።ድርጊቱ የፓኪስታንንና የሕንድን ግንኙነት ማበላሸቱ ተገልጿል።

በአጅማል ካሳብ ላይ የወንጀል ክስ የተመሠረተው እ.ኤ.አ በ2009 ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2010 የሞት ቅጣት ተወስኖ በታል። ይሁን እንጂ ጠበቆቹ እ.ኤ.አ በ2010 ይግባኝ በመጠየቃቸው ፍርዱ ተግባራዊሳይሆን ቆይቷል። የይግባኝ ጥያቄ የቀረበለት የሙምባይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እ.ኤ.አ የካቲት 2011 ይግባኙን ውድቅ አደረገ። በኋላም የይግባኝ ጥያቄው ለአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢቀርብም ውሳኔውን ሊያስ ለውጥ አልቻለም።

አደጋውን በፈጸመበት ወቅት የ21 ዓመት ወጣት የነበረውና ከአንድ የፑንጃብ ድሃ ቤተሰብ የተገኘው አጅማል ካሳብ ላሽካር ኢታይባ በተባለው የፓኪስታን አሸባሪ ድርጅት ለሽብር ተግባር ተመልምሎ የሠለጠነው ካሽሚር ውስጥ አዛድ በተባለ ስፍራ እንደሆነ የሮይተርስ ዘገባ አመልክ ቷል።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ የተጠቀሰውን ሥልጠና ከተከታተለ በኋላ ወደ ሕንዷ ሙምባይ ከተማ በጀልባ ሰርገው ከገቡት አስር አሸባሪዎች መካከል አንዱ በመሆን የተጠቀሰው አደጋ መፈጸሙ ተረጋግ ጧል።