ፕሬዚዳንት ካቢላ የአማፅያኑን ቅሬታ እንደሚያጠኑ አስታወቁ

  • PDF

አዲስ አበባዕ  ህዳር 17/2005 (ዋኢማ) - የኮንጐ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ ሰሞኑን የሰሜን ኪቩን ዋና ከተማ ጐማን እንደተቆጣጠረ የተነገረለትን «ኤም 23» የተባለ የአማፅያን ቡድን ቅሬታ እንደሚያጠኑ ማስታወቃቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ። ፕሬዚዳንት ካቢላ ይህን ያስታወቁት ከዑጋንዳና ከርዋንዳ መሪዎች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንደሆነ ተገልጿል።

ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ በዚሁ መግለጫ «ኤም 23» ከተባለው የአማፅያን ቡድን ጋር ድርድር ለመጀመር የሚቻልበትን ሁኔታም ለማጥናት እንደተዘጋጁ ማመልከታቸውንም ቢቢሲ ገልጿል። የሦስቱ አገሮች ማለትም የኮንጐ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ፣ የርዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜና የዑጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮወሪ ሙሴቪኒ የተጠቀሰው የአማፅያን ቡድን የማጥቃት እርምጃውን አቁሞ ከጐማ እንዲወጣ መጠየቃቸው በቢቢሲ ዘገባ ተመልክ ቷል።

አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት «ኤም 23» የተባለውና ከኮንጐ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጦር ሠራዊት አፈንግጠው በወጡ ወታደሮች እንደተደራጀ የተነገረለት ቡድን በርዋንዳና በዑጋንዳ እንደሚደገፍ ማመልከቱ ተገልጿል። ሁለቱ አገሮች ግን ይህን ውንጀላ አስተባብለዋል።

የተጠቀሰው የአማፅያን ቡድን የጐማን ከተማ ከተቆጣጠረ በኋላ ከዚች ከተማ ደቡብ 230 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ቡካቩ የተባለች ከተማ ለመቆጣጠር እንደሚያመራ ማመልከቱን ዘገባዎች ገልጸዋል። የአማፅያን ቡድኑ መሪ እንደሆነ የተነገረለት አንድ መኮንን በጐማ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ስታዲየም ለተሰበሰበ ሕዝብ ባደረገው ንግግር፤ አገሪቱን ነፃ የማውጣት ጉዞ እንደተጀመረ ማመልከቱ ተገልጿል።

እ.አ.አ ሚያዝያ 2012 የተመሠረተው ይህ «ኤም 23» በሚል ስም የሚታወቅ የአማፅያን ቡድን የአመፅ እንቅስቃሴውን የጀመርው እ.አ.አ በ2009 በተደረገው ስምምነት መሠረት መንግሥት በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ተገቢ ሥፍራ ለመስጠት የገባለትን ቃል ባለመፈፀሙ ምክንያት እንደሆነ ማመልከቱ ተገልጿል።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ የአማፅያን ቡድኑ እንቅስቃሴ አገሪቱን እ.አ.አ ከ1997- እስከ 2003 እንደተካሄደው ወደሚመስል የእርስ በርስ ጦርነት ሁኔታ ሊያስገባ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።