የእሥራኤልና የሐማስ የተኩስ ማቆም ስምምነት በዘላቂነት እንዲከበር ተጠየቀ

  • PDF

አዲስ አበባዕ  ህዳር 17/2005 (ዋኢማ) - የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታ ምክር ቤትና የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን በእሥራኤልና በሐማስ መካከል ካይሮ ውስጥ የተደረሰውን የተኩስ ማቆም ስምምነት አድንቀው ስምምነቱ በዘላቂነት እንዲከበር መጠየቃቸውን የድርጅቱ ዜና ማዕከል አስታውቋል።

በግብፅና በሌሎች ድጋፍ ሰጪ አገሮች አደራዳሪነት በእሥራኤልና የጋዛ ሰርጥን ተቆጣጥሮ በሚገኘው ሐማስ መካከል የተኩስ ማቆም ስምምነት የተደረገው ከትናንት በስቲያ እንደሆነ ሲታወቅ፣ ስምምነቱን ይፋ ያደረጉት የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሐመድ ካመል አምር እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን ካይሮ ውስጥ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

በግብፅ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሞርሲ፣ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተንና በፍልስጥኤም ባለሥልጣኖች መካከል ከፍተኛ ድርድር ከተካሄደ በኋላ የየተደረሰው ስምምነት ሐማስን ጨምሮ የተለያዩ በፍልስጥኤም ቡድኖች ሮኬቶችን ወደእ ሥራኤል ከመተኮስ እንዲታቀቡ፣ እሥራ ኤልም በጋዛ ሰርጥ ላይ የምትፈ ፅመውን ጥቃት እንድታቆም የሚጠይቅ እንደሆነ ተረጋግጧል። እሥራኤል የሐማሱን ኢዛዱን ካሳም ብርጌድ አዛዥ አህመድ ካሊል አልጃባሪን ከገደለች በኋላ ለስምንት ቀናት በተካሄደው የሐማስና የእሥራኤል ግጭት 139 ፍልስጥኤማውያን እንደተገደሉ፣ ከ900 በላይ እንደቆሰሉና አሥር ሺ ያህል ሰዎች እንደተፈናቀሉ ተገልጿል። ከተገደሉት ፍልስጥኤማውያን መካከል ሰባው ሰላማዊ ሰዎች እንደሆኑ ታውቋል። ከእሥራኤል በኩል አራት ሰዎች ሲገደሉ 219 ሰዎች እንደተጐዱ ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን የተኩስ ማቆም ስምምነቱን አድንቀው በዘላቂነት እንዲከበር በጠየቁበት መልዕክታቸው በግጭቱ ሂደት በሁለቱም ወገኖች በኩል ሕፃናትን ጨምሮ ንፁኃን ሰዎች መገደላቸውንና መጐዳታቸውን አመልክተው ይህ ሁኔታ መደገም እንደማ ይኖርበት ገልጸዋል።

የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን በእዚሁ መልዕክታቸው የአካባቢው ሁኔታ አሁን በሚገኝበት ሁኔታ እንዲቆይ ለማድረግ የሚቻል ካለመሆኑ አንፃር ለጋዛ ሰርጥ በአጠቃላይም ለፍልስጥኤም ችግር ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት የሚታለፍ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

ፀጥታ ምክር ቤት የተኩስ ማቆም ስምምነቱን በመደገፍ ባወጣው መግለጫ ደግሞ እሥራኤልና ሐማስ እዚህ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉትን የግብፅ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሞርሲንና ሌሎችን ድጋፍ የሰጡት አገሮች አድንቋል።
ፀጥታ ምክር ቤት በእዚሁ መግለጫ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የጋዛ ሰርጥ ሕዝብን አሁን ከሚገኝበት አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ለማውጣት አስፈላጊውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክትም ጥሪ አድርጓል።

የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን የተኩስ ማቆም ስምምነቱ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ በዘላቂነት እንዲከበር የጠየቁበትን መልዕክት ያስተላለፉት በእሥራኤል ውስጥ ጉብኝት በአደረጉበት ወቅት ነው። ባን-ኪ-ሙን ሰሞኑን በመካከለኛው ምሥራቅ በተገኙበት ወቅት ከግብፁ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሞርሲ፣ ከዓረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ ናቢል ኤላራቢ፣ ከእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ ከፍልስጥኤም አስተዳደር ፕሬዚ ዳንት ማህሙድ አባስ፣ ከዮርዳኖስ ንጉሥ አብዱላና ከተለያዩ የአካባቢው ባለሥልጣኖች እንዲሁም ግጭቱንና አጠቃላዩን የአካባቢ ጉዳይ ለሚመለከት ተልዕኮ በእዚያ ከነበሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን ጋር መነጋገራቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል ሲኤንኤን የተባለው የአሜሪካ ቴሊቪዥን የተኩስ ማቆም ስምምነቱ ካይሮ ውስጥ ይፋ ከተደረገ በኋላ የሐማስ ተዋጊዎች አምስት ሮኬቶችን ወደደቡባዊ እሥራኤል በመተኮስ ስምምነቱን እንደጣሱ የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ቃል አቀባይ ሌተና ኮሎኔል አቢታል ሊቦቪች ቢያመለክቱም፤ ስምምነቱ ተግባራዊ መሆኑን ከያቅጣጫው የደረሱ መረጃዎች ማመል ከታቸው ተገልጿል። ሲኤንኤን በአሜሪካ የእሥራኤል አምባሳደር ማይክል ኦሬንን ጠቅሶ እንዳመለከተው ተኩሱ በእርግጥም ቆሟል።
የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንሁ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አገራቸው የወሰደችውን እርምጃ መደገፋ ቸውን በማመልከት ያመሰገኑ ሲሆን፤ የተኩስ ማቆም ስምምነቱ ዘላቂነት እንዲኖረው ዕድል ለመስጠት ዝግጁ እንደሆኑም ገልጸዋል።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ እሥራኤል ከጋዛ በኩል በማንኛውም ቡድን ለሚሰነዘር የሮኬት ጥቃት በኃላፊነት ተጠያቂ የምታደርገው ሐማስን እንደሆነ ማመልከቷ በሲኤንኤል ዘገባ ተመልክቷል።