ሙስናን ለመዋጋት የሃይማኖት ተቋማት ድርሻ የጎላ ነው

  • PDF

አዲስ አበባዕ  ህዳር 17/2005 (ዋኢማ) - ሙስና በተቀናጀ መልኩ ለመዋጋት በሚደረገዉ ጥረት መልካም ስነ- ምግባርን በኅበረተሰቡ ዉስጥ በማስረፅ ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ ።

ስነ-ምግባርን በዜጎች ውሰጥ በማስፋፋት እና በማስረፅ ረገድ የጎላ ድርሻ ያላቸው የሃይማኖት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የጋራ የዉይት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል፡፡ የፌዴራልና ስነ-ምግባር እና ፀረ-መሰና ኮሚሸን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሡሌማን የፀረ ሙስና ጥምረት አገር አቀፍ ጉባዔ ሲክፍቱ እንደገለጡት መልካም ስነ-ምግባርን የተላበሱ ዜጎችን ማፍራት ሙስናን ለመከላከልና በመዋጋት ረገድ ለእድገትና ብልፅግና የጎላ ድርሻ አለዉ ።

በተለይ የሃይማኖት ተቋማት ከቆሙለት ዓላማ አንፃር የስነ-ምግባር ጉዳይ ዋንኛ ትኩረታቸው በመሆኑ በየቤተ እምነቶቻቸዉ ዜጎች ከጉስቁልና ተላቀዉ የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ መልካም አስተዳደር በማስፈን ሙስናን በመከላከል የድርሻቸዉን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

ኮሚሽኑ መልካም አሰተዳደር በአገር ደረጃ እንዲሰፍን ሃይማኖት ተቋማት ጋር ተባብሮ ለመስራት የሚያስችል አደረጃጀት ፈጥሮ እየሰራ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ መልካም ስነ-ምግባር በመገንባት የፀረ-ሙስና አስተሳሰቦችን በምዕመናን ዘንድ ማስረፅ መቻሉንም ገልጠዋል፡፡

ተቋማቱ በመልካም ስነ-ምግባርና በሙስና ጎጂነት ላይ ለተከታዮቻቸው ትምህርት በመስጠት ረገድ ያሳዩት አፈፃፀም ውጤታማ መሆኑን ተናግረው በ2004 በጀት ዓመት ከ11 ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍልና እንዲሁም በሩብ ዓመት ለ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተከታዮቻቸው ትምህርት መስጠቱንም ተናግረዋል፡፡

በኮሚሽኑ እና በሃይማኖት ተቋማት የጋራ የትብብር አገር አቀፍ ጉባዔ ላይ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች በሰጡት አስተያየት እንደገለጡት ሙስናን ከአገር ለማስወገድ በሚደረገዉ ጥረት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት በህዝብ ዘንድ ካላቸው ተቀባይነትና ከተከታዮቻቸዉ አኳያ ሙስናን በመወጋት መልካም ስነ-ምግባርን ለማስረፅ ያላቸው አቅም በመጠቀም የድርሻቸዉን እንደሚወጡ አስታዉቀዋል።

ዜጎች በመልካም ስነ-ምግባር እንዲታነፁ በአንፃሩ ሙስና ብልሹ አስተዳደር ለመታገል ከሚያደርጉት አስተምሮ በተጨማሪ ለኮሚሽኑ ዓላማዎች ግብ መምታት ተቀናጅቶ እንደሚሰሩ አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ስብሰበላይ በኮሚሽኑና በሃይማኖት ተቋማት የፀረ-ሙስና ጥምረት አገር አቀፍ ጉባዔ ላይ ከኦርቶዶክስ፣ ከእስልምና ፣ ከካቶሊክና ከወንጌላውያን አብያተ ቤተክርስቲያናት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡