ለአረንጓዴ ልማት መሳካት ወጣቶች ድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል-ፕሬዝዳንት ግርማ

  • PDF

አዲስ አበባዕ  ህዳር 17/2005 (ዋኢማ) - ለአረንጓዴ ልማት መሳካት ወጣቶች አካባቢያቸውን በማልማት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አስገነዘቡ፡፡

ፕሬዝዳንት ግርማ ዛሬ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ከ31 ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንደተናገሩት የአካባቢ ጥበቃ የሁሉም ጉዳይ ስለሆነ ለአረንጓዴ ልማት መሳካት ወጣቶች የበኩላቸውን መወጣት ይገባቸዋል፡፡

አረንጓዴ ኢኮኖሚን በአገሪቱ በመገንባት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማትን ማረጋገጥ የህይወት ጉዳይ በመሆኑ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሰቲዎች የተቋቋመው የ13 ወር አረንጓዴ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት የበላይ ጠባቂ የሆኑት ፕሬዚዳንት ግርማ እንዳሉት ፕሮጀክቱ በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ ያከናወነው ተግባር አመርቂ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት እያካሄደ ላለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት መረጋገጥ ፕሮጀክቱ አስተዋፅኦ የላቀ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል፡፡

መንግሥት ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ማህበረሰቡና ባለድርሻ አካላት ለአረንጓዴ ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ አክሊሉ ታደሰ በበኩሉ በ31 ዩኒቨርስቲዎች ፕሮጀክት በመቅረፅ የአካካቢ ጥበቃ ክበባት በማቋቋም የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባር ተከናውኗል ብሏል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ በዚህም ባለፈው ክረምት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከ76 ሺህ በላይ የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውንና ከ60 ሺህ በላይ የሚሆኑት መፅደቃቸውን ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም በዘንድሮ ዓመት ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን የተለያዩ ተግባራት ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡