በክልሉ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ገለፁ

  • PDF

ጋምቤላ፤ ህዳር 15/2005(ዋኢማ) - በጋምቤላ ክልል ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማስቻልና ድህነትን ለማስወገድ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

በጋምቤላ ከተማ "ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት የመቀነስ ቀን" ከትናንት በስቲያ በተከበረበት ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ ኡቻን ጋርኮት እንደገለፁት፤ በክልሉ ለሰው ሰራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ በሆኑ ምክንያቶች የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረት ይብልጥ ሊጠናከር ይገባል።   

እንደ ተወካዩ ገለፃ የጋምቤላ ክልል በተደጋጋሚ ለሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ በመሆኗ ምክንያት በክልሉ እየተካሄደ የሚገኘውን ልማት በተያዘለት ፍጥነት እንዳይጓዝ ችግር ሲፈጥር እንደነበር ይስተዋላል ካሉ በኋላ አደጋውን ለመቀነስ የተለያዩ የልማት አጋሮች ጥረትና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ዩኤንዲፒ ከክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ህብረተሰቡን በምግብ ራሱን ለማስቻል ያከናወናቸው ተግባሮች የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው፤ የክልሉ መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፓል ቱት በበኩላቸው፤ ጎርፍ፣ ድርቅና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የክልሉ ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ኤጀንሲው ከዩኤንዲፒ ጋር በመሆን በላሬና በጋምቤላ ገጠር ወረዳዎች አደጋዎችን ለመቀነስና በምግብ ራስን ለማስቻል በተደረገው ጥረት ሞዴል አርሶ አደሮች ማፍራት ተችሏል ብለዋል።

የሞዴል አርሶ አደሮቹን ምርጥ ተሞክሮዎችም ወደ ሌሎች ወረዳዎች ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል የዩኤንዲፒ ተወካይ አቶ ማርክ ኡሞድ እንደገለፁት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በላሬና ጋምቤላ ገጠር ወረዳዎች አካባቢ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ በማድረግ ከ9ሺ 500 በላይ አርሶ አደሮች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከተሳተፉት ውስጥም 12 ሞዴል አርሶ አደሮችና የእርሻ ባለሙያዎች ለሽልማት ማብቃት ተችሏል ብለዋል።

በዓሉ “ሴቶችና ልጃገረዶች አደጋን ለመቋቋም ግንባር ቀደም ሚና አላቸው! “በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን፤ በክልሉ ላሬና ጋምቤላ ወረዳዎች የሚገኙ ሞዴል አርሶ አደሮችና የእርሻ ባለሙያዎች ላፕቶፕና የምስክር ወረቀት ተሸልመዋል።

ከተሸላሚዎች መካከል አቶ ኩቺንጊ ኡሜድና ቶክ መጃግ በሰጡት አስተያየት በምግብ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ትርፋማ እንዲሆኑ  መንግስትና ምግባረ ሰናይ ድርጅቶቹ ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ ያገኙትን ምርጥ ተሞክሮ ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋፋት ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አረጋገግጠዋል ፡፡

የበዓሉ አከባበር አንዱ በሆነው የፓናል የውይይት መድረክ ላይም የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

በውይይት ወቅትም ከተለያዩ ቢሮዎችና ወረዳዎች የመጡ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የእርሻ ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮችናጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች አካላት መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።