ባህላዊ ወርቅ አውጪዎች በሩብ የበጀት አመቱ 2ሺ 5 መቶ 52 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማዕከላዊ ገበያ አቀረቡ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2005 (ዋኢማ) – በዘንድሮው ሩብ የበጀት ዓመት 132 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ ከ2ሺ 552 ኪሎ ግራም በላይ በባህላዊ መንገድ የተመረተ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክና ለዓለም ገበያ መቅረቡን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ። 

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  አቶ ባጫ ፉጂ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በባህላዊ መንገድ የተመረተው ወርቅ ከትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦችና ከጋምቤላ ክልል የተገኘ ነው።

በዘንድሮው የበጀት ዓመት የተመረተው ወርቅ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ488 ነጥብ 26 ኪሎ ግራም ብልጫ እንዳለው ጠቁመው፤ በገቢ ረገድም በ23 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብልጫ ማሳየቱን አቶ ባጫ ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት 3ሺ 299 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ የነበረ መሆኑን የተናገሩት አቶ ባጫ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈፃፀም የዕቅዱን 77 በመቶ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

በተመሳሳይም በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት 4ሺ 900 ኪሎ ግራም ሌሎች የጌጣጌጥ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 2 ሚሊየን 357 ሺ የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ 4ሺ 867 ኪሎግራም የጌጣጌጥ ማዕድናት ለውጭ ገበያ መቅረቡን አቶ ባጫ ገለጸዋል።

ይህም የዕቅዱ 99 በመቶ አፈጻጸም ማሳየቱን ጠቁመው፤ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በ393 ነጥብ 2 ኪሎ ግራምና በ753 ሺ 667 የአሜሪካ ዶላር ብልጫ አሳይቷል ብለዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ለውጪ ገበያ ከቀረበው 7 ነጥብ 77 ቶን ታንታለም 293 ሺ 971 የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ተናግረዋል።