በክልሉ ሜጢ ከተማ የመጀመሪያ የሆነ የተሽከርካሪዎች መናኸሪያ ግንባታ ተጠናቀቀ

  • PDF

ጋምቤላ፤ ህዳር 15/2005/(ዋኢማ) - በጋምቤላ ክልል የማጃንግ ዞን ዋና ከተማ ሜጢ  የመጀመሪያ የሆነ የተሽከርካሪዎች መናኸሪያ ግንባታ ተጠናቆ በቅርቡ ለአገልግሎት መብቃቱን የከተማ ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ።  

የማዘጋጃ ቤቱ ምክትል ሹም አቶ ሞገስ ተፈራ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ግንባታው የተጠናቀቀው የተሽከርካሪዎች መናኸሪያው ከ317 ሺ ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።

የመናኸሪያው መገንባት በከተማው ያለውን የትራንስፖርት ችግር የሚያቃልል ከመሆኑም በላይ ባለንብረቶችና ተጓዦች ደህንነታቸውን እንዲጠበቅ የሚያስችል መሆኑን ገልፀው፤ በአካባቢው ያለው የንግድ እንቅስቃሴ እንዲጠናከርም ያስችላል ብለዋል።

በከተማው የተፋሰስ ስራዎችን ለማከናወን ማዘጋጃ ቤቱ 600ሺ ብር የመደበ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም የግንባታው ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አቶ ሞገስ ገልፀዋል።

በከተማዋ የ01ና 02 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አወል ጀማልና አቶ እንዷለም አባትነትህ በሰጡት አስተያየት የሚኖሩበት ከተማ የዞኑ ዋና ከተማ እንደመሆኗ እስካሁን ምንም ዓይነት የጠጠር መንገድ ባለመገንባቱ ቅሬታ ቢሰማቸውም ለጠጠር መንገድ ግንባታው በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።