ለከተማዋ ዕድገት የህብረተሰብ ዙሪያ መለስ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2005 (ዋኢማ) - የአዲስ አበባ ከተማ ዕድገት የመላው ህብረተሰብ ዙሪያ መለስ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

ዛሬ በስታዲየም የአዲስ አበባ 125ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር ማጠቃለያ ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የከተማዋን የከተማይቱን ቀጣይና ፈጣን እድገት ለማረጋገጥ መላው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ዙሪያ መለስ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል።

በሀገሪቱ እየተገነባ ያለው የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ለከተሞች ዕድገት መፋጠን ጉልህ ሚና እንዳለውም  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የታላቁ መሪ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ራዕይ ዳር ለማድረስ  የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎችን ለማስቀጠልና በስኬት ለማጠናቀቅ  የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ  መሆኑን ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸዋል።

ከተማዋ የበርካታ ዲፕሎማቶች መኖሪያና የበርካታ አለም አቀፍ ድርጅቶች መገኛ መሆኗን ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ የኢፌዴሪ መንግስት ለከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥና እድገት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በበኩላቸው ቀደምት መንግስታት ለከተማዋ የሰጡት ትኩረት አነስተኛ ስለነበር እድገቷ ተጓቶ መቆየቱን ጠቁመው ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ዕድገትዋ በመፋጠን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት የከተማዋን ህዝብ  የመኖሪያ ቤትና የስራ አጥነት  ችግርን ለመፍታት  ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ከንቲባው ተናግረዋል። 
የአነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት ይበልጥ ተደራጅተው ወደ ኮንስትራክሽንና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መግባታቸውን የጠቆሙት አቶ ኩማ የግንባታ ዘርፉ የከተማዋን የመሰረተ ልማት ችግር ከመቅረፉ ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።