የጋምቤላ ክልልን ልማት ለማሳካት የልማት ኃይሎች ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ተባለ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2005 (ዋኢማ) - በጋምቤላ ክልል የተነደፈውን የአምስት ዓመት የልማት እቅድ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የልማት ማህበራት የተቀናጀ ተሳተፎ መጠናከር እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስገነዘቡ።

የኢትዮጵያ ኑዌር ልማት ማህበር ሰሞኑን በጋምቤላ ከተማ ባካሄደው የገቢ ማሰባቢያ መርሃ ግብር ግማሽ ሚሊዮን ብር አሰባሰቧል። ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ኡሞድ ኡቦንግ በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት በክልሉ የተነደፈውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እውን በማድረግ ህዝቡን ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለማላቀቅ በሚደረገው ጥረት የልማት ማህበራት የተቀናጀ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ዜናዊ የተቀየሱ ዘመን ተሻጋሪ ምቹ ፖሊሲዎችን ወደ ተግባር በመለወጥ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ማስቀጠል የሚቻለው ህዝባዊ የልማት ማህበራት ተሳትፎን ማጠናከር ሲቻል እንደሆነም ተናግረዋል።

በተለይ በመንግስት ሊደረስባቸው ያልቻሉ የልማት ክፍተቶችን መሙላት የሚቻለው በህዝባዊ የልማት ማህበራት የተቀናጀ ጥረት መሆኑን አቶ ኡሞድ ገልጠዋል። በክልሉ ለተነደፈው የልማት እቅድ እውን መሆን የብዙኃን ማህበራት አደረጃጀታቸውን በማጠናከር ከክልሉ መንግስት ጎን ተሰልፈው የድረሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኑዌር ልማት ማህበር በኑዌር ዞንና በክልሉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማገዝ የጀመራቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች በሌሎችም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋልዋክ ቱን በበኩላቸው በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ወደ ልማት በመለወጥ የህዘቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኑዌር ልማት ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቾል ኮር እንደተናገሩት ልማት ማህበሩ ባለፈው ዓመት የተመሰረተ ቢሆንም በተፈለገው መጠን ፈጥኖ ወደ ልማት ሳይገባ ቆይቷል።

ሆኖም ልማት ማህበሩ በአሁኑ ወቅት በዞኑ ብሎም በክልሉ የተጀመሩ የመልካም አሰተዳደርና የልማት ሥራዎችን ለማገዝ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል። ማህበሩ በተለይ በመንግሰት ያልተደረሰባቸውን የግብርና፣ የጤና የትምህርት፣የንፁህ መጠጥ ውሃና ሌሎች የልማት ክፍተቶች ለመሙላት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጠዋል።

ልማት ማህበሩ በጋምቤላ ለሁለት ቀናት ባካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግበር ከግለሰቦች፣ ከድርጅቶችና ከተለያዩ ተቋማት ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ አሰባሰቧል