ትክክለኛውን መስመር የያዘች ሀገር (ክፍል ሁለት)

  • PDF

ያሲን ኑሩ (ህዳር 2005)

በክፍል አንድ ጽሑፌ ላይ ሀገራችን የምትከተለውን ትክክለኛ መስመር መሰረታዊ ጽንስ ሃሳብ ከሀገራችን ታሪካዊ ዳራ ጋር በማያያዝ እንዲሁም በአሁን ወቅት እየተከተልነው ስላለው ፌዴራላዊ ስርዓታችን ልዩ ባህሪያት ለውድ አንባቢዎቼ እንዳስነበብኳችሁ አይነዘነጋም። ተከታዩን ክፍል ደግሞ እንዲህ አቅርቤዋለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡…
በታሪክ ቀዳሚ ናቸው ከሚባሉ ፌዴራል መንግስታት እንደምንገነዘበው፤ ማንኛውም ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀርን የተከተሉ ሀገራት ጉዟቸው እንከን አልባና አልጋ በአልጋ አለመሆኑን ነው፡፡ ሁሉም ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ አልፈዋል፡፡
ዳሩ ግን በርካታ የፌዴራል መንግስታት ካጋጠሟቸው ፈተናዎች ለመውጣት ስርዓቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመምራት፣ በህዝቦች መካከል የመቻቻልና መተሳሰብ እንዲኖር የማድረግ አቅጣጫዎችን በማበጀታቸው ከችግሮቻቸው ለመውጣት ችለዋል፡፡ በውጤቱም እስካሁን ድረስ ሊዘልቁ ችለዋል፡፡
ሁኔታውን ከእኛ ሀገር አንጻር ስንመለከተው፤ የሀገራችን ፌዴራሊዝም ችግሮች አላጋጠሙትም ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም የፌዴራል ስርዓቱ የዛሬ 18 ዓመት ገደማ እውን ሲሆን፤ ያለፉት ስርዓቶች በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል ጥለውት የሄዱት የግንኙነት ችግሮች ስለነበሩ ነው፡፡
ይሁንና እነዚህ ችግሮች ለተወሰኑ ጊዜያት የተከሰቱ ቢሆንም፤ ችግሮቹን ህገ -መንግስታዊ በሆኑ አግባቦችና በህብረተሰቡ የግጭት መፍቻ መንገዶች እልባት በመስጠት በሂደት ለመቅረፍ ተሞክሯል፡፡ በዚህም አጥጋቢ የሆኑ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡
ለአብነት ያህል በአንድ ወቅት በኦሮሚያና በሶማሌ ብሔረሰቦች መካከል የተነሳውን አለመግባባት በህገ - መንግስቱ መሰረትና በባህላዊ አሰራሮች አማካኝነት ለመፍታት መቻሉን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህም የፌዴራላዊ ስርዓቱ በውስጡ ሊከሰቱ የሚችሉ ነባራዊ አለመግባባቶችን የመፍታት አቅም ያለው መሆኑን በግልጽ የሚያመላክት ነው፡፡
ነገር ግን ባለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡት የህዝቦች የተሳሳቱ ግንኙነቶች በአንድ ጀምበር የሚፈቱ አይደሉም - ሂደትን የሚጠይቁ ናቸውና፡፡ ታዲያ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ህገ - መንግስታዊ ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ የኢፌዴሪ ህገ - መንግስትም ለዚህ ጉዳይ የማያሻማና ቁልፍ መርሆዎችን አስቀምጧል፡፡
በተለይም “…መጪው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል …”  የሚለው የህገ - መንግስቱ ክፍል፤ በህዝቦች መካከል የነበረው የተዛቡ አመለካከቶች በዴሞክራሲያዊ አኳኋን መፈታት እንዳለባቸው የሚያስረዳ ነው፡፡
የሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓትም እነዚህን ስር ሰደው የቆዩ አመላካከቶችን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ከመፍታት ባሻገር፤ በህዝቦች መካከል መቻቻልና መከባበር እንዲሰፍን ብሎም ያለፈውን ቁርሾ ሳያስታውሱ እጅ ለእጅ ተያይዘው አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት የድርሻ ቸውን እንዲወጡ ሲያደርግ ቆይቷል —ላለፉት 18 ዓመታት፡፡
በዚህም በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀደም ሲል በነበሩት መንግስታት በተፈጠሩ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ይነሱ የነበሩት ጥቃቅን የውስጥ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና ለአመረዳዳት በህገ - መንግስቱ መሰረት ዴሞክራሲያዊ በሆነ አኳኋን መፍትሄ ሊያገኙ ችለዋል፡፡ ይህም ፌዴራላዊ ስርዓቱ የሚከሰቱ ችግሮችን በአፋጣኝ የመፍታት አቅሙን እያጎለበተ መምጣቱን የሚያሳይ ሁነኛ አስረጅ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ወደፊትም ቢሆን የፌዴራል ስርዓቱን ሊፈትኑ የሚችሉ ችግሮች ቢከሰቱ እንኳን፤ አሁን ተጠናክረው በመቀጠል ላይ የሚገኙት የልማትና የመልካም አስተዳደር ትሩፋቶች ይበልጥ እየጎለበቱና እየዳበሩ ስለሚመጡ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ ያረጋግጣሉ፡፡ ይህም ይከሰቱ የነበሩበት ጥቃቅን አለመግባባቶች በሂደት መክሰማቸው እንዲቀር ማድረጉ አይቀርም፡፡
ታዲያ ያኔ ህብረ - ብሔራዊነቱ በማይነቃነቅ የብረት ምሰሶ ላይ ስለሚመሰረት ለየትኛውም ጊዜያዊ እንቅፋት የማይበገር መሆኑን ማረጋገጡ እሙን ነው፡፡ ታዲያ እዚህ ላይ ከፌዴራላዊ ስርዓቱ ምን ጥቅምና ውጤት አገኘን?...በዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ዘንድስ ተቀባይነታችን ምን ያህል ነበር?’ የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተን ማውጋት ያስፈልጋል፡፡
እንደሚታወቀው ለፌዴራል ሥርዓቱ መፈጠር አነሳሽ የሆነው ምክንያት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላለፉት ሥርዓቶች በጫንቃቸው ላይ ተጭኖ የነበረውን ብሔራዊ ጭቆና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሽቀንጥረው ለመጣል መፈለጋቸው ነው፡፡ ይህ የህዝቦች ብሶት የወለደውና በፈቃዳቸው እውን ያደረጉት ህገ - መንግሥታዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሀገራችን በርካታ ጠቀሜታዎችን አስገኝቷል፡፡
በዚህም ቀደም ሲል በህዝቦች ሲነሱ የነበሩት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በአዲሲቷ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ የማያዳግም ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ባለፉት ስርዓቶች ህዝቡ በጭቆና፣ በብሔራዊ አፈና እንዲሁም በፀረ - ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ስር ይማቅቅ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
ይህም በአንድ በኩል ለሠላምና ለዴሞክራሲ የሚታገል ኃይልን የፈጠረ ሲሆን፤ በሌላ ወገን ደግሞ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን በአፈና እና በፀረ - ዴሞክራሲያዊ መንገድ አፍኖ ለመያዝ የሚፈልግ ኃይል ይህን እንቅስቃሴ ለመጨፍለቅ ጥረት እንዲያደርግ በር ከፍቷል፡፡ ሁኔታውም በሀገሪቱ ውስጥ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ የእርስ በርስ ግጭት ፈጥሯል፡፡
በግጭቱም መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጦርነት ሰለባ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ይሁንና ምንጊዜም ቢሆን ድል ከመላው ህዝብ ጋር ነወና ከ17 ዓመታት መራርና ፈታኝ ትግል በኋላ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የሀገሪቱን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከጦርነት ስጋት ነፃ ሊያደርጓቸው ችለዋል፡፡
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ በደርግ ውድቀት ዋዜማ ወቅት በአፍቃሪ ፊውዳልና የደርግ ስርዓት ቅሪቶች “ሀገራችን ልትበታተን” ነው ተብሎ የተነገረው አስገራሚ ሟርት ነው፡፡ በወቅቱ አንዳንድ ሟርተኞች፤ “ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያ የትርምስ ማዕከል ትሆናለች፡፡ እንደ ሶቭየት ህብረትና ዮጎዝላቪያ ትበታተናለች፤ህዝቦቿ እርስ በርሳቸው ይፋጃሉ” የሚሉ አስገራሚ ትንበያዎችን ሰጥተዋል፡፡
እነዚህ የ “ሊሆን ይችላል” ሟርቶች ግን በወቅቱ በተወሰደው ትክከለኛ ውሳኔ የህልም ዓለም ቅዠቶች ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ይህ ውሳኔም ፌዴራላዊ ስርዓትን መመስረት ነበር፡፡ እናም ውሳኔው ሀገራችንን ከብተና ከማዳኑም ባሻገር፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሰላም አየርን እንዲተነፍሱ አድርጓቸዋል፡፡
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ልዩነታቸው የስጋት፣ የአደጋ ብሎም የጦርነት ምንጭ ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ በመሰረቱት ፌዴራላዊ ስርዓት ጥላ ስር ሆነው በአስተማማኝ የሰላም ጎዳና ላይ መጓዝ ከጀመሩ እነሆ 18 ዓመታትን ሊያስቆጥሩ ችለዋል፡፡ በድላቸው ባረጋገጡት አስማማኝ ሰላምም፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በህገ - መንግስቱ ዓላማ ጥላ ስር ሆነው የልማት ተጠቃሚነታቸውን በየደረጃው ይበልጥ ዕውን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ውጤቶች በፌዴራል ሥርዓቱ አማካኝነት ያገኘናቸው ትሩፋቶች እንደመሆናቸው መጠን፤ ፌዴራሊዝም የጦርነት ደመናን ገፍፎ በሠላም መንደር ውስጥ እንድንኖር ብሎም የታላቁ መሪያችንን ራዕይ እውን እንድናደርግ ያስቻለን ወደፊትም የሚያስችለን እንዲሁም ውጤቱን በገሃድ እንድናይ ያደረገን እና የሚያደርገን ስርዓት ነው ማለት እንችላለን፡፡
የፌዴራል ስርዓቱ የራሳችንን የውስጥ ችግር ፈትተን በሰላምና መረጋጋት ውስጥ እንድንኖር ያደረገን ከመሆኑም ባሻገር፤ የሌሎች ሀገሮችን ሰላም ለማስጠበቅም እንድንሰራ ሰፊ ዕድል ፈጥሮልናል፡፡
በመሆኑም የፌዴራሊዝም ጠቀሜታ የሀገራችንን አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የአንዱ አለመኖር በሌላው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳረፉ አይቀርም፡፡ የአንዱ በተሟላ ሁኔታ መገኘት ደግሞ ሌሎቹም እንዲያብቡና እንዲጎለብቱ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል፡፡
በፌዴራላዊ ስርዓቱ የተረጋገጠው አስተማማኝ ሰላም፤ ለሀገራችን ልማትና ዴሞክራሲ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በቀደምት ስርዓቶች በሰላም እጦት ሳቢያ የድህነት መዘባበቻ የነበሩት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዛሬ በፌዴራላዊ ስርዓታቸው እውን ባደረጉት ሰላም አማካኝነት የራሳቸውን ጥሪት በማፍራት አንገታቸውን ቀና አድርገው መሄድ ጀምረዋል፡፡
በተለይም ባለፉት ስምንትና ዘጠኝ ዓመታት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በልማታዊው መንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ ያስመዘገቡት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ሀገራችን በአጭር ጊዜ ከድህነት መላቀቅ እንደምትችል አስመስክረዋል፡፡
በእነዚህ ተከታታይ ዓመታት ህዝቦች ያስመዘገቡት ከ10 በመቶ በላይ አማካይ ዕድገት በአንድ የጋራ ጥላ ስር የተሰባሰበ ህዝብ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ህያው ምስክር ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡
ይህ ዕድገት ዓለም በከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ በነበረበት ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ያለምንም ችግር ሳይስተጓጎል የቀጠለ መሆኑም በህገ - መንግስታዊ ስርዓቱ አማካኝነት የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ለመቀየር የተቀረጹት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ትክክለኛና ማንኛውንም ጊዜያዊ ችግር የመቋቋም ብቃት ያላቸው መሆናቸውን በተግባር ማረጋገጥ ችለዋል፡፡
ዕድገቱ ዛሬ እያንዳንዱን ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ እርግጥ ይህ ተጠቃሚነት ህዝቦች ለሀገራቸው በጋራ መስራት እንዳለባቸው በማመን በልማት ስራው ውስጥ ባከናወኑት ተግባር መሰረት ያገኙት ውጤት መሆኑ አይካድም፡፡
ይሁንና ውጤቱ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድና በመተባበር እንዲሁም በፈቃዳቸው ለመሰረቷት ሀገር አንድ በመሆን እጅ ለእጅ ተያይዘው ያስገኙት ድል መሆኑ መዘንጋት አይኖርበትም ፡፡
እነዚህ ህዝቦች በፌዴራላዊ ስርዓት ውስጥ ባይኖሩ አሊያም ስርዓቱን በፈቃዳቸው ባይመሰርቱ ኖሮ እንኳንስ አሁን ያገኙትን የልማት ተጠቃሚነት እውን ሊያደርጉ ቀርቶ፤ ያለፈው ታሪካቸውን እየደገሙና እየደጋገሙ በጦርነት አዙሪት ቀለበት ውስጥ አስከፊ ህይወት ላለመኖራቸው ማንም እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይችልም፡፡
ይህ እንዳይሆን ግን ህዝቦች በቃል ኪዳናቸው ያሰሩት ፌዴራላዊ ስርዓት ቤዛ ሆኗቸዋል፡፡ በዚህም ነዳጅ ከሌላቸው ከሰሃራ በታች ከሚገኙ ህዝቦች ግንባር ቀደም ዕድገት እንዲያስመዘግቡ አድርጓቸዋል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በሁለት ዓመት ጉዞው ውጤታማ መሆን በቻለው የአምስት ዓመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሸን ዕቅድ ላይም በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ የ11 በመቶ ቢበዛ ደግሞ የ14 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ እንዲተጉ ሁኔታዎችን አመቻችቶላቸዋል፡፡
በዚህ አጠቃላይ ውጤትም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ባጸደቁት ህገ - መንግስት ላይ ለመፍጠር ያሰቡትን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብን እውን የማድረግ ታላቅ ተልዕኮን ገቢራዊ ማድረግ ችለዋል፡፡ እናም ለዘመናት ተንሰራፍቶ የነበረውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለመሰናበትና መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ መደላድል መፍጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡
የፌዴራሊዝም ጥቅም ሰላምና ልማትን ከማረጋገጥ ባሻገር፤ መሰረታዊ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድም ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀደም ባሉት ስርዓቶች ያነሷቸው የነበሩ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በህገ -መንግስታዊ ስርዓቱ ውስጥ አግባብ ባለው ሁኔታ ምላሽ ሊያገኙ ችለዋል፡፡
ህገ - መንግስቱ የሀገራችንን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማረጋገጥ ዜጎች ክብራቸውና መልካም ስማቸው እንዲጠበቅ አድርጓል፡፡ በተለይም ህገ-መንግስቱ ለዴሞክራሲያዊ መብቶች 16 አንቀፆችን መስጠቱ የዴሞክራሲ ጥያቄ በሀገራችን ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ምላሽ ማግኘቱን በማያሻማ ሁኔታ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ይህም የሀገራችን ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው በመከበራቸው ሳይሸማቀቁ በነጻነት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ እንዲኖሩ አስችሏቸዋል፡፡
ዛሬ እንደቀደምት ስርዓቶች የፖለቲካ ስልጣን በጥቂት ፈላጭ ቆራጮች ስር አይደለም፡፡ ህዝቡ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት በመሆኑ በምርጫ ካርዱ ያሻውን ፓርቲ የመሾምና የመሻር ስልጣንን ተጎናጽፏል፡፡
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ይህን ስልጣናቸውን በመጠቀም ለአራት ጊዜያት ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ተዓማኒና ምሳሌ ሊሆን የሚችሉ ምርጫዎችን አካሂደዋል፡፡
በ2002 ዓ.ም በፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ያካሄዱትን 4ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ብንመለከት እንኳን ለሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት መጠናከር እንዲሁም ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን መጎልበት ይበጃል ያሉትን ፓርቲ መምረጣቸው በስልጣን ባለቤትነታቸው ለፀረ-ህገ - መንግስት ኃይሎች ህገ - መንግስታዊ ስርዓቱን “ከመቆፈር”  እንዲቆጠቡ የሰጡት ምላሽ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ለወደፊቱም ቢሆን ማንኛውም ኃይል በሰላማዊ ፓርቲነት ተሰልፎ ህገ -መንግስቱን ተጻርሮ የሚቆም ከሆነ፤ “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ” እንዲሉ በምርጫ ካርዳቸው ከጨዋታው ውጪ እንደሚያደርጉት አመላክተው አልፈዋል፡፡
ደሩ ግን ምንም እንኳን የሀገራችን ዴሞክራሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የሄደ ቢሆንም፤ ያለፉት ስርዓቶች ጥለውት ከሄዱት ፀረ -ዴሞክራሲ አስተሳሰቦች ጋር የሚደረገው ትግል በሂደቱ ላይ የራሱን አሉታዊ ጫና ማሳረፉ አልቀረም፡፡
እርግጥ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የተሟሉ የሚሆኑት የዴሞክራሲ ተቋማትና ድርጅቶች እንዲሁም በዜጎች ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አመለካከቶች የበላይነታቸውን ሲቀዳጁ መሆኑ እሙን ነው፡፡ እንኳንስ እኛ ቀርቶ የዳበረ ዴሞክራሲ  ገንብተዋል የሚባሉት ሀገሮችም በረጅም ጊዜ ሂደት ነው - እነዚህን ሁኔታዎች ሊያማሉ የቻሉት፡፡
ፌዴራሊዝምን በምትከተለው ባለፉት 21 ዓመታት ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለመገንባት በተደረገው ጥረት በሂደት ከፍተኛ ውጤቶች እየተገኙ ነው፡፡ በተለይም ህብረተሰቡ በዴሞክራሲ መሰረታዊ መርሆዎች ላይ አንድ ልዩነት የጋራ አቋምና እምነት እንዲይዝና ልዩነቶችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የማስተናገድ ባህል እየዳበረ ሊመጣ ችሏል፡፡
እዚህ ላይ ህብረተሰቡ በመሰረታዊ መርሆዎች ላይ አንድ ዓይነት የጋራ አቋም መያዝ አለበት ሲባል፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ምንም ዓይነት ልዩነት የሌለው ወጥ አቋም ያራምዳል እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ነገር እንኳንስ በኛ ሀገር ሁለት አስርታትን ጥቂት እልፍ ባሉ ዓመታት ብቻ ባስቆጠረ ጅምር ዴሞክራሲ ቀርቶ የዳበረ ዴሞክራሲ ገንብተዋል በሚባሉት ሀገሮች ውስጥም የለም—የተለያዩ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በውስጣቸው ይዘዋልና፡፡
ይህ እውነታም ሀገራዊ የጋራ አመለካከት መያዝ ማለት እያንዳንዱ ዜጋ ወጥ የሆነ አመለካከት እንዲይዝ ማድረግ ሳይሆን፤ አብዛኛው ህዝብ በመሰረታዊ መርሆዎች ላይ የጋራ አመላካከት እና አቋም እንዲኖረው ማድረግ መሆኑን የሚያስገነዝበን ነው፡፡
ሀገራዊ መግባባትን ከሀገራችን አኳያ ስንመለከተው ላለፉት 21 ዓመታት የተከናወኑት ስራዎች በሂደት ዴሞክራሲያዊ የጋራ አስተሳሰቦችን በሂደት በህብረተሰቡ ውስጥ ለመገንባት ተችሏል፡፡ በዚህም ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከሰሙ መጥተዋል፡፡ የዜጎችን መብት በማክበርና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ እንዲሁም መብትን በሰላማዊ ሁኔታ የማስጠበቅ ብሎም ሊከሰቱ የሚችሉ ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት በድርድርና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የመፍታት የጋራ አስተሳሰቦችም በመጎልበት ላይ ይገኛሉ፡፡
እንዲህ ዓይነቶች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብቶችም ፌዴራላዊ ስርዓቱ እስካለ ድረስ ተጠብቀው የሚቆዩና በሂደትም የሚጠናከሩ መሆናቸውን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
እስካሁን ድረስ በተሰሩት ስራዎች የተፈጠረው ሀገራዊ (ብሔራዊ)  መግባባትም የሀገሪቱን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ለአንድ ሀገር በጋራ እንዲሰሩና እጅ ለእጅ ተያይዘው በዕድገት ጎዳና እንዲተሙ አድርጓቸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም በምሳሌነት መጠቀስ የምንችል የፌዴራል ስርዓት ተከታዮች መሆናችንንም ማረጋገጥ ችለዋል፡፡
ውድ አንባቢዎቼ እንደምታስታውሱት ታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ ህንድ -ኒውደልሂ ላይ በተካሄደው 4ኛው የዓለም ፌዴራሊዝም ጉባዔ ላይ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት 5ኛው ዓለም አቀፍ የፌዴራሊዝም ጉባዔ በ2003 ዓ.ም ሀገራችን ውስጥ እንዲካሄድ በዓለም የፌዴራል ስርዓትን የሚከተሉ ሀገራት ያለምንም ማቅማማት ይሁንታቸውን ሰጥተው ነበር፡፡
ታዲያ በወቅቱ የተሰጠው ይህ ይሁንታ ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት አወቃቀር ገና አዲስና ጀማሪ እንደመሆኗ መጠን ነባር ፌዴሬሽኖች እያሉ ለምን ዕድሉ ተሰጣት? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ከአፍሪካስ በተለየ ሁኔታ የታየችበት ምስጢር ምንድነው? ብለን መጠየቅም አግባብነት ያለው ነው፡፡ ነገሩም ወዲህ ነው፡፡…
በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት፤ ሀገራችን በወቅቱ የፌዴራሊዝም ጉባዔውን እንድታዘጋጅ የተመረጠችበት ምክንያቶች በርካታ ናቸው፡፡ ይሁንና ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ዋነኛ ጉዳዮች ጉልህ ስፍራ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ እነርሱም ለአፍሪካ ሞዴል የሆነ ፌዴራላዊ ስርዓት መገንባት መቻሏ እንዲሁም በሀገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እየጎበተ መምጣቱ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገቧ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነት እየጨመረ መምጣቱ ነው፡፡
በሀገራችን ውስጥ የሚገኙት ከ80 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተቻችለውና ተፋቅረው በልዩነታቸው ውስጥ ባለው አንድነታቸው ተጠቅመው የተረጋጋና ሰላማዊ የፌዴራላዊ ስርዓት መመስረታቸው ለአፍሪካ በምሳሌነትና የሚጠቀስ ስርዓት ባለቤት መሆን መቻላቸው ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ይሁንታውን እንዲቸረን አድርጓል፡፡
እጅግ አነስተኛና ከቁጥር የማይገቡ ብሔረሰቦች ያላቸው አንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች በሰላም እጦትና መረጋጋት ችግር እየታመሱ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፤ ከ80 በላይ ብሔረሰቦችን አቅፋ በሰላማዊ መንገድ ዕድገቷን በማረጋገጥ ላይ የምትገኘው ሀገራችን በእርግጥም በአፍሪካ በአብነት የምትጠቀስ ሀገር ናት፡፡
ታዲያ ይህን ምስጢር ለማወቅ የሚሹት የዓለማችን ፌዴራላዊ ሀገራት ከሀገራችን ልምድ ለመቅሰምና ያላቸውንም ልምድ ለማካፈል በወቅቱ ጉባዔውን ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ መምረጣቸው ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡
በወቅቱ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ይህ ጉባዔ በሀገራችን እንዲዘጋጅ የተፈለገበት ሌላው ጉዳይ ፌዴራላዊ ስርዓታችን ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን በማጎልበት የተጫወተውን ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
በፌዴራል ስርዓት እየተመሩ ዕድገታቸውን ሳይስተጓጉሉ በፍጥነት ማደግ ከቻሉ ጥቂት የዓለማችን ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗ ለጉባዔው አዘጋጅነት የመመረጧ ሌላኛው ምስጢር መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ሀገራችን በህዝቦቿ የጋራ ጥረት ላለፉት ዓመታት በተከታታይ በአማካይ የ10 በመቶ በላይ ዕድገት አስመዝግባለችና፡፡
ዓለም በምጣኔ ሀብት ቀውስ በተመታበት ወቅት ይህ ዕድገት ይስተጓጎል ግለቱን ጠብቆ መቀጠሉ የፌዴራል ስርዓቱን ምስጢራዊነት ይበልጥ አጓጊ ያደርገዋል፡፡ እናም ይህን በመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም በህዝቡ ብሔራዊ መግባባት የጋራ ርብርብ የተገኘውና ፈጣንና ተከታታይነት ያለውን ዕድገት ስኬት ምስጢሮች ሌሎች የዓለም ፌዴራል መንግስታት ልምድ ሊቀስሙበት ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም የዚህ ምስጢር ባለቤት የሆነችው ሀገራችን ጉባዔውን እንድታስተናግድ መመረጧ ትክክለኛ ምርጫ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ እናም በሌሎች ሀገሮች የተቀባይነታችን ምስጢር ይኸው ነው፡፡
የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለፉት ሥርዓቶች ጥለውት የሄዱትን የድህነትና የኋላቀርነትን ጠባሳ ሽረው ገጽታቸውን በልማትና በዴሞክራሲ ሂደቶች ቀይረዋል፡፡ የነበሩባቸውን ችግሮች ሁለት አስርት ዓመታት ባልሞሉ ጊዜያት ውስጥ ቀርፈው ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሰላምና መረጋጋት ግንባር ቀደም ደራሽ ለመሆን ችለዋል፡፡
ይህም ሀገራችን በክፍለ አህጉራዊና በአህጉራዊ ብሎም በዓለም ህዝቦች ዘንድ በጥሩ ገጽታዎች እንድትታወቅ አድርጓታል፡፡ አመኔታንና ከበሬታንም ተጎናጽፋለች፤ ተደማጭነቷንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጎለበተች ሄዳለች፡፡ የስርዓቱ ትክክለኛ መገለጫም ይኸው ነው።
እነዚህ ሁሉ በፌዴራላዊ ስርዓቱ እውን መሆን ሀገራችን የተጎናጸፈቻቸው ውጤቶች እርግጥም ፌዴራሊዝም የሀገራችን ብቸኛው አማራጭ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው — ቀጣዩን የዕድገት መሰላል መወጣጫችንም የሚያመላክቱ ጭምር በባህር ዳር የሚካሄደው 7ኛው የሀገራችን ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ላይ የታላቁን መሪያችንን ራዕይ እውን ለማድረግና ፈለጋቸውን ለመከተል የምንገባውን ቃል እንደ ዜጋ ዳግም በማደስ ዕለቱን በታላቅ ድምቀት ማክበር ይኖርብናል። መልካም በዓል! ቸር እንሰንብት፡፡