ትክክለኛውን መስመር የያዘች ሀገር (ክፍል አንድ)

  • PDF

ያሲን ኑሩ (ህዳር 2005)

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድ የጋራ ማህበረሰብ መስርተው በፌዴራላዊ ስርዓት ጥላ ስር መኖር ከጀመሩ እነሆ ሁለት አስርት ዓመታትን ሊደፍን ነው፡፡ 18ኛውን የመቻቻልና ተከባብሮ የመኖር ጥበብን በማዳበር ለውጤታማነት የበቁበትን ዕለት ለ7ኛ ጊዜ በቅርቡ በባህርዳር ከተማ ያከብራሉ፡፡
ግና የሀገራችን ህዝቦች በፌዴራላዊ ሥርዓታችን ለድል የበቁበትን ምክንያት ከማብራራቴ በፊት፣ ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስለ ሥርዓቱ አጠቃላይ የአመጣጥ ሂደትንና ምንነትን መለስ ብዬ ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡
በዓለማችን ላይ በአንድ አሃዳዊ መንግስት ከሚተዳደርበት ሥርዓት ይልቅ፣ ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር በበርካታ ህዝቦች ዘንድ ተመራጭ እየሆነ መምጣቱን ድርሳናት  ያወሳሉ፡፡ እርግጥ ለፌዴራላዊ ሥርዓት ተመራጭነት በርካታ ጉዳዮች በምክንያትነት ለሚጠቀሱ ቢሆንም፤ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በዓለማችን የተፈጠሩትና እየተፈጠሩ ያሉት ተከታታይ ክስተቶች የመጀመሪያውን ስፍራ ይዘዋል፡፡
ክስተቶቹ ቀደም ሲል በቅኝ ግዛትነት ተይዘው የነበሩ ሀገራት ነጻ ለመውጣትና በአሃዳዊ አገዛዝ ሥር የነበሩትም በአንድነት ለመሰባሰብ እንዲሁም ለአምባገነናዊና ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ የመንግስት መዋቅር ራሳቸውን ለማላቀቅ ያደረጉት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ክስተቶቹ የእነዚህ ሁነቶች ድብልቅ የሆነው በየሀገራቱ መታየታቸው ፌዴራሊዝም ተመራጭ እንዲሆን አድርገውታል፡፡
በዓለም ላይ ያሉ ህዝቦች ወካይ መሆናቸው የሚነገርላቸው የእነዚህ ታሪካዊ ክስተቶች ድምር ውጤትም በአሁኑ ወቅት በመንግስታቱ ድርጅት በአባልነት ከሚታወቁት 193 ሀገሮች ውስጥ 28 የሚሆኑት ፌዴራላዊ መዋቅርን እንዲመርጡ አድርጓቸዋል፡፡ እርግጥ የሀገራቱ ቁጥር ትንሽ ይምሰል እንጂ፤ ከህዝብ ብዛት አንጻር ውጤቱ ሲለካ ከዓላማችን ህዝብ ውስጥ 49 በመቶ የሚሆነው በፌዴራል ስርዓት ውስጥ ታቅፎ የሚኖር መሆኑን ስንመለከት የሥርዓቱ ተመራጭነት ምን ያህል እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡
ታዲያ እዚህ ላይ “ለምንድነው ፌዴራላዊ ሥርዓት በህዝብ ተመራጭ የሆነው?”  የሚል ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር በህዝቦች ተመራጭ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት እያንዳንዱ ህዝብ በሚፈጠረው አዲሱ ፌዴራላዊ ማህበረሰብ ውስጥ የጋራ ጥቅሞችን እየተጋራ የየራሱን የራስ ገዝነት ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችለው በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁኔታም በጋራ ማዕቀፉ ውስጥ ያለው ህዝብ ከተመቸው የፌዴራል ሥርዓቱ አካል የመሆን፤ ካልተመቸው ደግሞ ከአባልነቱ ራሱን ሊያገል የሚችልበት ልዩ መብት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡
ይህን መስሉ የሥርዓቱ ልዩ ልዩ ሁኔታዎችን የማስተናገድ ብቃትና ባህሪ በዓለማችን ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው አስር ሀገራት ውስጥ ስድስቱ እንዲሁም ከአስሩ የዓለማችን ሰፋፊ ሀገራት ስምንቱ በፌዴራላዊ ስርዓት እንዲታቀፉ ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
በፌዴራልዝም ዙሪያ ምሁራዊ መጽሐፍቶችን በማቅረብ የሚታወቁት ጆርጅ አንድርሰን “የፌዴራላዊ መንግስት አወቃቀር መነሻ ነጥቦች” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት፤ በፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀርን የሚከተሉ ሀገራት ከአሜሪካ ጀምሮ እስከ ማይክሮኔዥያና ኔቪስን የተባሉ ትናንሽ ደሴቶች ድረስ ታቅፈው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያ ጨምሮ ጀርመን፡ ህንድ፣ ሩሲያ፣ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ብራዚል፣ ቤልጅየም፣ ካናዳ፣  ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሜክሲኮ፣ ፓኪስታን፣ ቬንዙዌላ ወዘተ በፌዴራል መንግስት አወቃቀራቸው ከሚጠቀሱት ሀገራት ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እርግጥ ሀገራቱ በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ስብጥራቸው እንዲሁም አወቃቀሩን ለመከተል ከወሰኑበት ምክንያት በመነጨ በፌዴራል ስርዓቶቻቸው በእጅጉ ይለያያሉ፡፡ በሀገራቱ ውስጥ የሚገኙት የፌዴራሉ መንግስት አባላት (ክልሎች) ከሁለት እስከ 80 እንዲሁም ከዚያ በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ ግልጽ የሆነ የስልጣን ክፍፍል ያላቸው ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ የተሟላ አሰራርን በመከተላቸው ይታወቃሉ፡፡
በፌዴራል ስርዓታቸው አወቃቀር ጠቅላይ ሚኒስትርና ፓርላሜንታዊ መንግስት ያላቸው ሀገራት እንዳሉ ሁሉ፤ በፕሬዚዳንትና በምክር ቤት ተቋማት የመንግስትነት አካሄዱን የሚከተሉ የፌዴራል ስርዓት ተከታይ ሀገራትም ጥቂት አይደሉም፡፡ ይህን መሰሉ ልዩነት አንድ የፌዴራል መንግስት ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ከሌላው ጋር የግድ ግልባጭ (Carbon Copy) መሆን አለበት የሚል እምነት የሌለ መሆኑን ያመላክተናል— “ወፍ እንዳገሩ ይጮሀል” እንዲል  የሀገራችን አርሶ አደር፡፡
ይሁን እንጂ፤ ይህ ማለት ግን በዓለም ላይ የሚገኙ የፌዴራል ስርዓት ተከታይ መንግስታት የጋራ የሚያደርጋቸው ባህሪያት የሏቸውም ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም አንድን የመንግስት አወቃቀር ፌዴራላዊ ነው ወይም አይደለም ከሚያስኙት ባህሪያት ውስጥ አንዱ ለጠቅላላው ሀገር ሌላው ደግሞ ለክልሎች የሚያገለግል ቢያንስ ሁለት መዋቅሮች አሉት፡፡
እነሱም ፌዴራል መንግስቱ ብቻ ሊያሻሻለው የማይችለው የተጻፈ ህገ - መንግስት ያላቸው እንዲሁም በአባል ክልሎች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች የሚፈቱበት የግልግል ስርዓት በፍርድ ቤት ወይም በህዝብ ውሳኔ አሊያም በፌዴራሉ የላዕላይ ምክር ቤት አማካኝነት የሚከናወን እንዲሁም በአባል ክልሎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት የሚያመቻቹና ስራውንም የሚያካሂዱ አሰራሮችና ተቋማት ያላቸው መሆናቸው ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ባህሪያት ናቸው፡፡
ታዲያ እነዚህ የፌዴራል መንግስታት የጋራ ባህሪያት እንደተጠበቁ ሆነው ከሂደት እንደታየው ሁሉም ፌዴራል መንግስታት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ በመሰረታዊ ህገ - መንግስታዊ ለውጥ ውስጥ ያለፉ ሲሆን፤ ሌሎቹ ደግሞ በአመዛኙ ህገ - መንግስታቸውን ጠብቀው ቢጓዙም፤ በለውጥ ሂደት ውስጥ ያለፉ ናቸው፡፡
ለአብነት ለመጥቀስ ያህል አንጋፋው የአሜሪካ ፌዴራል መንግስት የመጀመሪያው ህገ - መንግስት (The first amendement) እስካሁን ድረስ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ የቆየ ሲሆን፤ 27 ለውጦች ብቻ የተደረጉበት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የስድሳ ዓመታት ዕድሜ ባለቤት የሆነው የህንድ ህገ - መንግስትም ቢሆን 94 ማሻሻያዎችን አድርጓል፡፡
በአሁኑ ወቅት በማደግ ላይ ያለችው ብራዚልም ከነጻነቷ በኋላ ሰባት ጊዜ ማሻሻያዎችን ስታደርግ፣ ሜክሲኮና ቬንዙዌላ ደግሞ በቅደም ተከተላቸው ስድስት እና 26 ህገ - መንግስታዊ ለውጦችን ማድረጋቸው የየሀገራቱ ታሪክ ያስረዳል፡፡
ምንም እንኳን የፌዴራሊዝም የሂደት ማሻሻያዎች በእነዚህ ሀገራት የታየ ቢሆንም ሌሎች ሀገራት ግን በህገ - መንግስታቸው ፀንተው በቁጥርና በባህሪ መለወጣቸውን የተጓዙባቸው ታሪክ ያወሳል፡፡
እርግጥ ማንኛውም የዚህ ጽሑፍ አንባቢ “ታዲያ ተመራጭ የሚባለው ፌዴራሊዝም የትኛው (የየት ሀገር) ነው?” የሚል ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፡፡ ጥያቄው ተገቢ ቢሆንም በዓለማችን ላይ እንዲህ ዓይነት የፌዴራሊዝም ዓይነትን ሀገራት ሊከተሉ ይገባቸዋል የሚባል አንድ ወጥ እሳቤ የለም፡፡
ከዚህ ይልቅ ክልላዊ አሰፋፈር፣ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥርና ሰፊ ግዛት ያላቸውና ብዙሃነትን አካትተው ለያዙ ሀገራት ፌዴራሊዝም ፍቱን መድኃኒት መሆኑ በስፋት ይታመንበታል፡፡
ነገር ግን ሀገራቱ እነዚህን ባህሪያት አካትተው ቢይዙም ዴሞክራሲያዊ ካልሆኑ ፌዴራሊዝም ለማራመድ እጅግ በጣም ሊከብዳቸው እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ፌዴራሊዝም መሰረቱን በህገ - መንግስታዊነትና በህግ የበላይነት ላይ ስላደረገ ነው፡፡ እናም አንድ ሀገር ፌዴራሊዝምን በሚመርጥበት ወቅት ብዙሃነትን የያዘ ቢሆንም፤ ዴሞክራሲያዊ መሆኑንም ማረጋገጥ የውዴታ ግዴታው ይሆናል ማለት ነው፡፡
ስለ ፌዴራሊዝም አንኳር ነጥቦች በጥቅሉ ይህን ያህል ካልኩ ዘንዳ፤ በውጤታማነቱ ስለተመሰከረለት እና ሀገራችን በትክክለኛው መስመር እንድትጓዝ ስላደረጋት ፌዴራላዊ ሥርዓት አንዳንድ ጉዳዮችን ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ለመሆኑ ሀገራችን ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ስርዓትን ለምን መረጠች? ፌዴራላዊ ስርዓታችንን ከሌሎች ልዩ የሚያደርገውስ ምንድነው?፤ ፌዴራሊዝም ምን ጠቀሜታ አስገኘልን? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት የግድ ይለናል፡፡ ዳሩ ግን ጥያቄዎቹን ከመመለሳችን በፊት በታሪክ ጅረት ወደ ኋላ ተጉዘን የሀገራችንን ቀደምት ጉዞ እንዲህ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡
ከመቶ ዓመታት በፊት የሀገራችን ህዝቦች ራሳቸውን የቻሉ ነጻና ከፊል ነጻ በሆኑ መንግስታት ይተዳደሩ እንደነበር ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ በሀገራችን ሰሜንና ማዕከላዊ አካባቢዎች ከሰፈሩት የአማራ፣ የትግራይና የአገው ህዝቦች በተጨማሪ በመላ ሀገራችን ይገኙ የነበሩት የኦሮሞ፣ የሶማሌ፣ የአፋር፣ የሲዳማ፣ የወላይታ፣ የከፋ፣የጉራጌ፣ የሀድያ፣ የከንባታ፣ የሐረሪ ወዘተ ህዝቦች በራሳቸው ጠንካራ አስተዳደር ይመሩ ነበር፡፡
ታዲያ እነዚህ ህዝቦች የነበራቸው አስተዳደር ፈርሶ በአንድ አሃዳዊ አገዛዝ ስር እንዲጠቃለሉ የተደረጉት በአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ ይህ ሁኔታም የዛሬዋ ኢትዮጵያ የአሁኑን ቅርፅና የህዝቦች ጥንቅርን ይዛ እንድትፈጠር ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡ 
ታሪክ እንደሚያስረዳን እነዚህ ህዝቦች ወደ አንድ አሃዳዊ አገዛዝ እንዲገቡ የተደረጉት በአስገዳጅነትና ተከታታይነት ባለው ከፍተኛ እልቂትን ባስከተለ ጦርነት አማካኝነት ነው፡፡ በወቅቱም አጼ ምኒሊክ እነዚህን ህዝቦች ወግተውና አስተዳደራቸውንም አፍርሰው በራሳቸው የጦር ሹማምንቶችና ነፍጠኞች ስር እንዲተዳደሩ አድርገዋቸዋል፡፡ ኋላ ላይም የአጼ ምኒሊክን ስልጣን የጨበጡት አጼ ኃይለስላሴ የተፈጠረውን የተማከለ አሃዳዊ አገዛዝ ይበልጥ አጠናክረው ቀጠሉበት፡፡
የአጼው ስርዓት የገጠር መሬት ከበርቴዎች የሚደገፍና እጅግ የተማከለ አገዛዝን በመመስረት በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላይ ከባድ የብሔራዊ ጭቆና እና የብዝበዛ ቀንበር ጫነ፡፡ ይህ የፊውዳል ስርዓት የገባርና የጭሰኛ ህግ በማውጣት ህዝባችን በይዞታው ለፍቶ ያፈራውን ሀብት ለባለባቶችና ለነፍጠኞች እንዲያስረክብ አስገደደው፡፡
ታዲያ ይህ ስርዓት መንሰራፋትና የገዥው መደቦች ግፍ ምሬት የወለደውን የህዝብ ትግል ሊያመክነው አልቻለም፡፡ እናም በብሶት ሳቢያ በገጠርና በከተማ በግብታዊነት የተቀጣጠለው የህዝብ አመጽ የአጼውን ስርዓት ቢያንኮታኩተውም፤ የህዝቡ ድል “ደርግ”  በሚል ስያሜ በተሰባሰቡ በጥቂት ወታደራዊ መኮንኖች ተነጠቀ፡፡
ወታደራዊው የደርግ ሥርዓትም እንደ ቀደምት ገዥዎች ሁሉ የሀገራችንን ህዝቦች ጥያቄዎች ውድ ጎን አሽቀንጥሮ በመጣል የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና የህዝቦችን የመብት ጥያቄ በአፈሙዝ ኃይል የማንበርከክ ጥረቱን ቀጠለ፡፡ “ይሳካልኛል” በሚል ቀቢጸ - ተስፋም በአፍሪካ ግዙፍ የሚባል ጦር ገንብቶ በህዝባዊው ትግል ላይ ተከታታይ ዘመቻዎችን አደረገ፡፡ 
መላው የሀገራችን ህዝቦች ከቀደምት ስርዓቶች ፀረ -ዴሞክራሲያዊና ኢ- ፍትሃዊ አገዛዝ ለመላቀቅ ያደርጉት የነበረውን ትግል በደርግ ስርዓት ላይም አጠናክረው በመቀጠላቸው ለዘመቻው አልተበገሩም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የደርግ መንግስት የህዝቡን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ሊያዳፍን ባለመቻሉ ትግሉን ያበረደው መስሎት ለኤርትራ፣ ለትግራይ ለአሰብ፣ ለድሬዳዋና ለኦጋዴን አካባቢዎች የይስሙላ “ራስ ገዝ አስተዳደር”  ለመስጠት ተገደደ፡፡ ይሁንና እጅግ ከተማከለ አሃዳዊ አገዛዝ ግን አንድም ስንዝር ፈቀቅ ማለት አልቻለም፡፡
ይህ የደርግ አካሄድ በደንብ የገባቸው የኢትዮጵያ ህዝቦችም ለዴሞክራሲ፣ ለነጻነት ለልማትና ለሰላም የሚያደርጉትን ተጋድሎ በህዝባዊና ድርጅታዊ አመራር በማጠናከር የደርግ ስርዓትን ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ግብዓተ መሬቱ እንዲፈጸም አድርገዋል፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላስ?... ህዝቦች ያካሄዱት ትግል ምን ውጤት አመጣ ? … ምን ዓይነት ስርዓትስ የህዝቡን ጥያቄዎች መለሰ?... ቀጥሎ የምንመለከታቸው ወሳኝ ቁም ነገሮች ናቸው፡፡
የህዝቦችን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን አፍኖ ከነበረው አምባገነናዊ ስርዓት ውድቀት በኋላ በሀገራችን የነበረው ሁኔታ በጥልቀት ተፈተሸ፡፡ እናም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነፍጥ አንስተው ያለፉት ስርዓቶችን ያስወገዱበት መነሻ ጥያቄዎች በትክክል መመለስ ነበረባቸው፡፡
በመሆኑም ከ1983 ዓ.ም እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ የዘለቀው የሽግግር መንግስቱ ቻርተር ለጥያቄዎቹ ምላሽ ሰጠ፡፡ ቻርተሩ ተጨባጭ ለሆኑና አፍጥጠው ለመጡት የህዝብ ሉዓላዊነት እንዲሁም ለብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማንነትና እንዲሁም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄዎች ብሎም ሰር ሰደው ለቆዩት የዴሞክራሲ ጥያቄዎች መሰረታዊ መፍትሄ ሊሰጥ ችሏል፡፡ እዚህ ላይ እነዚህን ቁልፍ የሀገራችንን ህዝቦች ጥያቄዎች ከአሃዳዊ የመንግስት አወቃቀር መመለስ የማይቻሉ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
በአሃዳዊ መንግስት ጥያቄዎች ምላሽ ያግኙ ቢባሉ እንኳን እንደ ቀደምት ስርዓቶች በማያባራ ብጥብጥና ሁከት ውስጥ ላለመግባታችን አንዳችም ማረጋገጫ ማግኘት አንችልም፡፡ እንዲያውም ለብጥብጥና ለብተና መጋለጣችን አይቀሬ ይሆን ነበር፡፡
ስለሆነም ይህን ችግር ለመቅረፍ በቻርተሩ መሰረት የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን የሚያቋቁም አዋጅ እንዲወጣ በማድረግ  የተረጋገጠው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የማስተዳደር መብት ተግባራዊ ሆነ፡፡ እናም በወቅቱ በቻርተሩ አማካኝነት ይህ መፍትሄ ባይሰጥ ኖሮ፤ ዛሬ ያለችው ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ከዓለም ካርታ ላይ ላለመጥፋቷ በእርግጠኝነት ለመናገር አይቻልም፡፡
በመሆኑም ምላሽ የተሰጣቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከ80 በላይ ስለሆኑ እነዚህን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩነታቸውን አቻችሎ በጋራ እንዲኖሩ ለማድረግ ፌዴራሊዝም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነበር፡፡ እናም ሀገራችን የፌዴራል የመንግስት አወቃቀርን ለመከተል ችላለች፡፡
ቀደም ሲል በህዝብ የተመከረበትና ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ጸድቆ ስራ ላይ የዋለው የኢፌዴሪ ህገ - መንግስትም በቻርተሩ ምላሽ ያገኙ መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ መረጋገጥ ቁልፍ መርሆዎችንና ድንጋጌዎችን እንዲይዝ ተደርጎ ተግባራዊ ተደርጓል— የዛሬ 18 ዓመት፡፡
እርግጥ እዚህ ላይ ስለ ሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት ስናነሳ ምንጊዜም በግንባር ቀደምትነት የሚወሳው የሽግግሩ ወቅት ቻርተር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ታዲያ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ የሀገራችን ፌዴራሊዝም ምን ዓይነት ነው?... ለየት የሚያደርጉት ባህሪያትስ ይኖሩት ይሆን?... የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ነው፡፡…
…የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ለየት ያሉ ባህሪያት የሚመነጩት ከሀገሪቱ ፖቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ነው፡፡ እነዚህ ተጨባጭ ሁኔታዎችም  በህገ -መንግስቱ ላይ በግልጽ ስፍረዋል፡፡ በመሆኑም የሀገራችንን ፌዴራሊዝም ገጽታዎች ህገ -መንግስቱን መሰረት አድርጎ መመልከቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ህገ- መንግስቱ በሀገራችን ለዘመናት ምላሽ ሳይሰጣቸው ለኖሩት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስፋት ባለው ህዝብ ተሳትፎ ምላሽ እንዲሰጣቸው ያደረገ በመሆኑ የፌዴራል ስርዓታችን ልዩ ባህሪያትም የሚመነጩት ከዚሁ ህገ - መንግስት ነው፡፡
የፌዴራል ስርዓታችን ልዩ የሚያደርገው አንደኛው ጉዳይ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸው ነው፡፡ ይህም የፌዴራሉ መንግስት ቅርፀ- መንግስትነት ከሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የመነጨ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ከዚህም እነዚህ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች የፌዴራሉን ስርዓት በራሳቸው ይሁንታና ስምምነት መፍጠራቸውን መገንዘብ እንችላለን፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ካላቸው ስልጣን ቆርሰው ለፌዴራል መንግስቱ በመስጠት የሀገሪቱ አስተዳደር በመረጧቸው ተወካዮች አማካኝነት እንዲንቀሳቀስ ፈቅደው ተስማምተዋል፡፡ ለዚህ አንዱና ዋነኛው ማስረጃ ህገ-መንግስቱ በመግቢያው ላይ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች …”  በሚል ሐረግ መጀመሩ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሌላኛው ልዩ ባህሪ ህብረ - ብሔራዊ መሆኑ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የየትኛውም ዓይነት ፌዴራሊዝም ዋነኛ ዓላማ በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በልዩነታቸው ውስጥ ያለውን አንድነት አቻችሎ በጋራ እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ እናም በውስጧ ከ80 በላይ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የያዘችው ሀገራችን ከፌዴራሊዝም ውጭ ሌላ ምርጫ ሊኖራት አይችልም፡፡
ስለሆነም እነዚህ ህዝቦች በልዩነታቸው ውስጥ ያላቸውን አንድነት ለማጠናከር እንዲሁም ተፈቃቅደውና ተከባብረው በመኖር የጋራ ቤታቸው የሆነችውን ሀገራችንን ለማልማት ቃል ኪዳን ገብተዋል፡፡ እነዚህ ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ እየተጠቀሙና እየተዳኙ ብሎም ባህላቸውን እያሳደጉ ከፌዴራሉ አንድነት የሚገኘውን የጋራ ጥቅም በመቋደስ የአብሮነት ጉዟቸውን ምቹ አድርገዋል፤ ውጤታማም ሆነዋል፡፡
በአንቀጽ 39 ስር የተደነገገውና የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል መብትም የሀገራችንን ፌዴራሊዝምን ልዩ ገጽታ የሚያላብሰው የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ ይህ አንቀጽ በአንዳንድ ወገኖች የተሳሳተ ዕይታ ሀገራችንን የሚበታትን ተደርጎ ይቀርባል፡፡ እውነታው ግን የአንቀጹ መኖር ሀገራችንን ከብተና ያዳናት መሆኑ ነው፡፡ ይህን ሃቅ ለመረዳት በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ አንቀጽ ስር ሦስት ዓበይት ጉዳዮች መኖራቸውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ እነርሱም፡-
1.    የመብቱ ባለቤት ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መሆናቸው፣
2.    የራስን ዕድል የመወሰን መብት ህገ - መንግስታዊ ዋስትና ማግኘቱ እና
3.    አንድ ብሔር ብሔረሰብ ተገንጥሎ የራሱን መንግስት ለመመስረት እንዲችል መፈቀዱ ናቸው፡፡
እነዚህ ለየት ያሉ የፌዴራል ስርዓታችን ባህሪያት በህዝቦች ይሁንታ ላይ የተመሰረተው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ብቻውን በቂ ያለመሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
ስለሆነም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድና በአንድነት መኖር የሚያስችላቸውን ዴሞክራሲያዊ የአንድነት ዕድልንም አብሮ ይሰጣል፡፡ ታዲያ ይህን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመፍጠር ህዝቦች የእኩልነት መብታቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም በአንቀጹ አማካኝነት የእኩልነት መብት ማረጋገጫ የሆኑት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች ወዘተ ተከብረዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ በፖለቲካዊ አስተዳደር በኩል እኩል የመሳተፍ መብት ያገኙ ሲሆን፤ በልማት ስራው ላይም እኩል ዕድል እዲያገኙና በውጤታቸው መሰረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡
ታዲያ እነዚህን መብቶች ሁሉ ያረጋገጠ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በምን ምክንያት ሊገነጠሉ ይችላሉ? የመብቶቹ ባለቤት በመሆኑም ጥቅሞቹን እያጣጣመ የፌዴራል ስርዓቱን ያጠናክራሉ እንጂ በምን ዓይነት የሂሳብ ቀመር ሊበታተኑ ይችላሉ? በመሆኑም አንዳንድ ወገኖች በአንቀጽ 39 ላይ ያላቸው የስጋት ምንጭ ቀዳሚዎቹን አሃዳዊ ስርዓቶች ከመናፈቅ የመጣ አሊያም ህገ -መንግስቱን ቀድዶ ለመጣል ከመፈለግ የመነጨ ከመሆኑ በስተቀር እስካሁን ድረስ ያለው ተጨባጭ እውነታ የመበታተን ስጋትን የሚያመላክት አይደለም፡፡
ይህ የሀገራችን ተጨባጭ ሃቅም በመስኩ ምሁራን የተረጋገጠ ነው፡፡ የፌዴራሊዝም ምሁሩ ጆርጅ አንድርሰን እንደሚናገሩት፤ ምንም እንኳን የመገንጠል ጥያቄ ሊኖር የሚችለው በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ ነው ተብሎ ቢታሰብም እስካሁን ድረስ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያመላክተው አብዛኛዎቹ አሃዳዊ መንግስታት መበታተናቸውን ነው፡፡ እግርጥም “አራምባና ቆቦ” ስጋት ይሏል እንዲህ ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ፤ በፌዴራሊዝም ስርዓታችን ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኘው አንቀጽ 39 የአንድነታችን ዋስትና እንጂ የመለያየታችን ስጋት ሊሆን አይችልም፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙና ይህ አንቀጽ የሌላቸው ሀገራት በብጥብጥና በሁከት እየታመሱ ያሉትም በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን ማምጣት ባለመቻላቸው መሆኑን ካሉበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር መመልከታችንም የዚሁ ውጤት ነው፡፡
በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት፤ በግጭት ውስጥ እየታመሱ ያሉት እነዚያ ሀገራት ይህ አንቀጽ ቢኖራቸው ኖሮ እስካሁን ድረስ የተከሰተው ሰብዓዊና ማቴሪያላዊ ቀውስ ባልተፈጠረ ነበር፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ያለምንም ገደብ ያረጋገጠ ቢሆንም ዓላማው በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን በሀገሪቱ ላይ ለማምጣት እንደሆነ መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡
የምንከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት አባሎቹ የሚናቆሩበትና የሚባሉበት ሳይሆን አብረው በፈቃዳቸው በጋራ የሚያድጉበት ስርዓት መሆኑ ሌላው ልዩ ባህሪው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ ተባብረውና ተጋግዘው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ተደርጎ የተቀረጸው የፌዴራሉ ስርዓት በህገ - መንግስቱ ላይ በግልጽ መንጸባረቁ የጥንካሬው መገለጫ ነው፡፡
የህገ - መንግስቱን መግቢያ ቆንጥረን ብንወስድ እንኳን “…ጥቅማችንን፣ መብታችንንና ነጻነታችንን በጋራና በተደጋጋፊ ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን…” የሚለው ሃሳብ የፌዴራላዊ ስርዓቱ መገለጫ ህብረ - ብሔራዊነት ብቻ ሳይሆን መተጋገዝም ጭምር መሆኑን አመላካች ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም “መንግስት በዕድገት ኋላ ለቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልዩ ድጋፍ ማድረግ አለበት” የሚለው የህገ - መንግስቱ አንቀጽ 89 (4) የዚህ የመተጋገዝ ፌዴራሊዝም መገለጫ ተደርግ የሚወሰድ መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል፡፡
በጥቅሉ በእነዚህ አንኳር ልዩ ባህሪያት አማካኝነት በተፈጠረው የሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ምላሾቹም ዘላቂ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን እውን የሚያደርጉ ከመሆናቸውም በላይ፤ በርካታ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች፣ ባህሎችና ታሪኮች ያሏቸው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፌዴራሊዝም ስር በመሆን ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸው እንዲጎለብት አስችለዋቸዋል፡፡
ለዚህም ነው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በህንድ በተካሄደው 4ኛው የዓለም የፌዴራሊዝም ጉባዔ ላይ ፤ “…ፌዴራሊዝም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ያለንን ልዩነት እንድናቻችል ያደረገን መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ …ይህም ሀገራችን ካላት የተለየ ባህሪ አንጻር በፌዴራል ስርዓቱ ውጤት ማምጣት ችለናል…” በማለት የገለጹት፡፡
መቼም ውድ አንባቢዎቼ በዚህ ክፍል አንድ ጽሑፌ ስለ ፌዴራሊዝም አጠቃላይ ግንዛቤ፣ የፌዴራል ስርዓቱን ለማምጣት የተከናወኑ ነባራዊ ሁነቶች፣ ኢትዮጵያ ለምን ፌዴራሊዝም እንደመረጠች እንዲሁም የሀገራችንን ፌዴራል ስርዓት ለየት የሚያደርገውን ባህሪያት ለማሳየት መሞከሬን ተገንዝባችኋል ብዬ አምናለሁ፡፡
በክፍል ሁለት ጽሑፌ ደግሞ ‘ለመሆኑ የሀገራችን ፌዴራል ስርዓት እንከን አልባ ነበርን? ፌዴራላችንስ ምን ውጤት አስገኘልን?’ የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ላስነብባችሁ እሞክራለሁ፡፡