ሕዝብ የሚመርጠውን እንጂ ውዝግብ ፈጣሪ ፓርቲን አይሻም

  • PDF

አዲስ ቶልቻ (ህዳር 2005)

ሪፖርተር ጋዜጣ በረቡዕ ሕዳር 5/2005 እትሙ የፖለቲካ አምዱ ስር “የተንከባለሉ ጥያቄዎችን የቀሰቀሰው ምርጫ” በሚል ርዕስ በየማነ ናግሽ የቀረበ ፅሁፍ አስነብቦናል፡፡
ፅሁፉ በመጪው ሚያዝያ ወር የአዲስ አበባ ምክር ቤትና የአካባቢ ምክር ቤቶች ምርጫ እንደሚካሄድ አስታውሶ፣ እንደዚህ አይነቱ ምርጫ ዋናውን የመንግስት ስልጣን ለማሸነፍ ፉክክር የሚደረግበት ባይሆንም፤ በዋናው ምርጫ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ወሳኝ ሁኔታዎችን የመፍጠር አቅም ስላለው እንዲሁ ችላ የሚባል አይደለም” በማለት ይጀምራል፡፡
በማያያዝም “ተቃዋሚዎች ከዚህ ቀደም ጀምሮ ሲንከባለል የመጣው ምርጫው የሚከናወንበት ያልተስተካከለ መንገድ ሳይሻሻል አንሳተፍም በሚል ፔቴሽን ማሰባሰባቸውንና የስድስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው መድረክን ጨምሮ ከ40 በላይ የሆኑት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም ይዘዋል፡፡” ይላል፡፡
ፅሁፉ በዚህ አላበቃም “ጥያቄያቸው ከምርጫ ቦርድና ከገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር ሊያነታርካቸው ጀምሯል” ይላል፡፡ በዚሁ መነሻነት ፀሃፊው የማነ “ለጥያቄው የሚሰጠው ምላሽም ምርጫው ከወዲሁ ምን እንደሚመስል የሚወሰን ይመስላል” ብለው የግል  አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከፌደራል ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉት ምክር ቤቶች ምርጫ በየአምስት አመቱ የሚካሄድ መሆኑ በሕግ የተወሰነ ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም ላይ 4ኛው የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ተካሂዷል፡፡ በዚህ ምርጫ በፌደራልና በክልል ደረጃ እስከ 2007 ዓ.ም የሚመሩ ገዢ ፓርቲዎች በአብላጫ ድምፅ ተመርጠው ስልጣን ተረክበዋል፡፡
የአካባቢ - የቀበሌ ወረዳና ዞን ም/ቤቶች ምርጫ እንዲሁም የቀድሞው ቅንጅት ምርጫ 97ን ተከትሎ በሕዝብ ድምፅ የተሰጠውን አዲስ አበባን የማስተዳደር ኃላፊነት አሻፈረኝ በማለቱ ጊዜው የተዛባው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ ዘንድሮ በሚያዚያ ወር ይካሄዳል፡፡
የማነ በፅሁፋቸው እንደጠቀሱት ይህ በሚያዝያ ወር የሚካሄደው ምርጫ  በ2002 ዓ.ም ምርጫ አሸንፈው የመሰረቱትን የመንግስት ስልጣን አይነካም፡፡ በቀበሌ፣ በወረዳና በዞን ደረጃ የሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ ይህን ባይነካም እንደቀላል የሚታይ ምርጫ አይደለም፡፡
እንደቀላል እንዳይታይ የሚያደርገው ፀሃፊ የማነ እንዳሉት በቀዳሚነት በዋናው ምርጫ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን የመፍጠር አቅም ስላለው ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ህዝቡን በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በቀጥታ የሚሳተፍበትን ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ነው፡፡
በዚህ ምርጫ በቀበሌ፣ ወረዳና ዞን ደረጃ የሚመረጡትን በሚሊዮን  የሚቆጠሩ ተወካዮችን የተመለከተ ሕዝብ በራሱ ጉዳይ ላይ ምን ያህል በቀጥታ የሚሳተፍበትን ሁኔታ እንደሚፈጥርለት በትክክል ይረዳል፡፡ ምርጫው ትልቅና ትኩረት የሚሻ የሚሆነው በዋነኝነት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እርግጥ በዚህ ምርጫ ላይ የሚያሸንፍ ፓርቲ መጪውን ምርጫ ያሸንፋል የሚል ከፍተኛ ግምት እንዲሰጠው ሊያደርግ የሚችልበት ሁኔታ አለ፡፡
ፀሃፊ የማነ ወደዋና ጉዳያቸው ሲገቡ መጪው ምርጫ ላይ የስድስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ የሆነውን መድረክ ጨምሮ 40 ፓርቲዎች ከምርጫው በፊት መመለስ አለበት ያሉዋቸውን ጥያቄዎች ማንሳታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እዚህ ላይ አቶ የማነ አካሄዳቸው የአንድ ወገንን ጉዳይ አግዝፎ የማሳየት ዝንባሌ ያላቸው መሆኑን የሚያመለክት አንድ ነገር ታዝቤያለሁ፡፡ ይህም መድረክ  ቅድመ ምርጫ ጥያቄ ያቀረቡት ፓርቲዎች ራሱን ጨምሮ ሰላሳ አራት መሆናቸውን እየተናገረ፣ የማነ ግን ከዚህ በተለየ  የፓርቲዎቹን ቁጥር ለማሳደግ ስድስት ጨምረው አርባ ማድረሳቸው ነው፡፡
የማነ መድረክ የስድስት ፓርቲዎች ጥምረት ነኝ ብሎ እንደ አንድ ፓርቲ መመዝገቡንና በምርጫ ላይ እንደ አንድ ፓርቲ በአንድ የምርጫ ምልክት የሚወዳደር መሆኑን ዘንግተውት ነው የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ ይህን ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት በምርጫው ላይ ቅሬታ አለን የሚሉት ፓርቲዎች እንዲበዙላቸውና ነገሩ ያለወጉ እንዲጋጋል በማሰብ ይመስላል፡፡
እርግጥ የመድረክ ተጣማጅ ፓርቲዎች ፍፁም የተለያየና ተቃራኒ ፖሊሲ ያላቸው በመሆናቸው ጥምረታቸው በምን ላይ እንደተመሰረተ ብዙዎችን ግራ ያጋባ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ፀሃፊ የማነም የስድስቱ ፓርቲዎች በመድረክ ስር መጣመር የማይዋጥ ሆኖባቸው ዘርዝረዋቸው ሊሆን እንደሚችል ግን እገምታለሁ፡፡ ሆኖም የተሰበሰበው ፔቲሽን ላይ  ሰላሳ አራት ፊርማ ብቻ መስፈሩን  ሊያስታውሱ ይገባል፡፡
እንዲህ ስል “ሰላሳ አራቱ ፓርቲዎች ቁጥራቸው ትንሽ ነው” እያልኩ እንዳልሆነ እንዲታወቅ እሻለሁ፡፡ ሰባ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሉበት አገር ሰላሳ አራቱ 45 በመቶ ገደማውን እንደሚወክሉ እገነዘባለሁ፡፡
እነዚሀ መድረክ መራሽ 45 በመቶ ያህል የሚሸፍኑት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያነሱት ጥያቄ ከምርጫ ቦርድና ከገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር ሊያነታርኳቸው መጀመራቸውን የማነ ነግረውናል፡፡ ለዚህ ጠያቄ የሚሰጠው ምላሽም ምርጫው ከወዲሁ ምን እንደሚመስል ይወስናል ብለዋል፡፡
ይህ የየማነ ሃሳብም ጉዳዩን ያለ አቅሙ አቅም በመስጠት አቧራ ማስነሳት ያለመ ይመስላል፡፡  ምርጫ የሕዝብ የስልጣን ባለቤትነትና ምንጭነት የሚረጋገጥበት መሰረታዊ የፖለቲካ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ እጅግ በጣም ትልቅ ጉዳይ ደግሞ በዘፈቀደ ሳይሆን በሕግና ስርዓት የሚመራ ነው፡፡ ሃገራችን ኢትዮጵያም ይህን የምታስተናግድበት ሕግ፣ ደንብና ስርአት አላት፡፡  ሕጎቹና ደንቦቹ በዴሞክራሲ መርህ ላይ የተመሰረቱ፣ በየወቅቱ በምርጫ ሂደት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ታሳቢ በማድረግ የዳበሩ፣ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘቡ ናቸው፡፡
ምርጫውን የሚያስፈፅመው አካልም ምርጫውን የሚመራው በዚህ የሕግ ማዕቀፍ ተገድቦ ነው፡፡ ስለዚህ ያነሱት ጥያቄ ምርጫው ላይ በመሳተፍ ረገድ ከሌሎች ታቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እኩል መብት ካለው ኢህአዴግ ጋርም ሆነ ምርጫን ለማካሄድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለልተኝነቱ ተረጋግጦ ከተሰየመው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር አተካሮ ውስጥ የሚከት አንዳችም ነገር የለውም፡፡
እስካሁንም ጥያቄውን አነሳን የሚሉት ወገኖች ከሚያሰሙት ጩኸት ውጭ ከማንም ጋር የተፈጠረ ንትርክ አልሰማንም፡፡ ለወደፊትም የመነታረኪያ አጀንዳ መሆን የሚያስችለው አንዳችም እድል የለም፡፡
እንዲህ ስል “ጥያቄዎቹ ተገቢና ምላሽ የሚፈልጉ አይደሉም” እያልኩ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ምላሽ የሚያገኙት በጫጫታ፣ በንትርክ፣ በፍጥጫ፣ ረብሻ አስነሳለሁ ብሎ በማስፈራራት፣ … ሳይሆን፣ ለዚሁ ጉዳይ በተቀመጠ ሕግና ስርዓት ብቻ ነው፡፡ ጥያቄዎቹን ሊያስተናግድ የሚችል ሕግ፣ ደንብና የአሰራር ስርዓት ደግሞ አለ፡፡
ፀሃፊው የት የሰሙትን ንትርክ እንደሆነ ባይታወቅም “ኢህአዴግንና ምርጫ ቦርድን ሊያነታርክ ጀምሯል” ያሉት በመድረክ መራሹ ቡድን የቀረበውን ጉዳይ በተመለከተ፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እየጠበበ መምጣቱንና የምርጫ ውድድር ሜዳው የተስተካከለ ያለመሆኑን፣ ከዚህ በፊት የተደረጉ ምርጫዎች በአፈፃፀም ችግሮች የተተበተቡ መሆናቸውንና ችግሮቹ  አሁንም እንዳሉ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡
እነዚህ መድረክ መራሾቹ ፓርቲዎች ያነሱዋቸው ችግሮች “አሉ ወይም የሉም” የሚል ድምዳሜ መስጠት አልፈልግም፡፡ ዋናው ጉዳይ የችግሮቹ መኖር ወይም አለመኖር አይደለም፡፡ በመቶ አመታት የሚቆጠር የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል ባላቸውም አገራት ቢሆን ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ እናም ዋናው ጉዳይ “የችግሮቹ መኖር በማስረጃ ተረጋግጦ ሲቀርብ የሚፈቱበት ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአት አለ ወይስ የለም?” የሚለው ነው፡፡ በእኛ አገር ደግሞ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚፈቱበት ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ተዘርገቷል፡፡
በእኛ ሃገር እነዚህ ችግሮች ለአጋጣሚ አልተተውም፡፡ ችግሮቹ ሲያጋጥሙ ችግሩ ደረሰብኝ ያሚለው ወገን “ባወጣ ያውጣህ” ተብሎ አይተውም፡፡ በምርጫ ሕጉ በተለይም የጉዳዩ ቀዳሚ ባለቤቶች የሆኑ  የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች (ከመድረክ በስተቀር) ለሁለት ወራት ያህል እያንዳንዱን አንቀፅ አድቅቀው ተወያይተው ተስማምተው የተፈራረሙበት፣ በኋላም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ አድርጎ ያፀደቀው የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ ላይ መፍትሄ የሚያገኙበት አግባብ ተመቻችቷል፡፡
ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ችግሮች ሲያጋጥሙት በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፎ በሕግ በተደነገገው መሰረት፣ ለምርጫ ቦርድ በማቅረብ ይህም ካልተሳካ በፍርድ ቤት እንዲታይ በማድረግ መፍትሄ ማግኘት የሚቻልበት ሕጋዊ መብት አለ፡፡ አሁን መድረክ ከምርጫው በፊት ልወያይባቸው በሚል ያቀረባቸው አብዛኞቹ ጉዳዮች ደግሞ መድረክ አልፈልግም ብሎ የተወው የምርጫ ስነምግባር ደንብ ላይ የሰፈሩ ናቸው፡፡
ከመድረክ መራሹ ሰላሳ አራት የፖሊቲካ ፓርቲዎች መሃከል ሰላሳ ሶስቱ የምርጫ ስነምግባር ደንቡ ላይ ተስማምተው የፈረሙ በመሆናቸው “ደንቡ ተጥሷል” ብለው ሲገምቱ፣ ጉዳዩን ለፖሊቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቅርበው ውይይት እንዲደረግበትና ስጋቱ እንዲወገድ የማድረግ መብት አላቸው፡፡
እርግጥ መድረክ “የምርጫ ስነምግባር ደንቡ አያስፈልገኝም” የሚል አቋም ይዞ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ባለመሆኑ ይህን ማድረግ የሚያስችለውን መንገድ ስለዘጋ ሊቸገር ይችል ይሆናል፡፡ የምክር ቤቱ አባል ሳይሆን የቀረው ግን በመንግስት፣ በገዢው ፓርቲ ወይም በሌሎች ፓርቲዎች ተገፍቶ ሳይሆን፣ ከስነምግባር ደንቡ ውጪ መንቀሳቀስ ያዋጣኛል በሚል የራሱ ውሳኔ መሆኑ መታወስ ይኖርበታል፡፡ ይህም ቢሆን ግን በማንኛውም ግዜ ደንቡ ላይ ፈርሞ የም/ቤቱ አባል መሆን ስለሚችል ዕድሉን የመጠቀም መብቱ አሁንም በእጁ ነው፡፡
የማነ በፅሁፋቸው “የቀደመው የአካባቢ ምርጫ …” በሚል ንኡስ ርዕስ ስር ፀሃፊው ምርጫ 97ንና 2002ን አስታውሰዋል፡፡  ካነሱት ጉዳይ ውስጥ ምላሽ ይሻል ያልኩትን ልጥቀስ፡፡ ይህም “ ኢህአዴግ እንደመንግስት ስልጣኑን በወቅቱ ምርጫ (1997) ለመነጠቅ ተቃርቦ የነበረ ሲሆን፣ ተቺዎች እንደሚሉት በምርጫው ማግስት የፀደቁት የፕሬስ አዋጅና፣ የሲቪል ማህበራት አዋጅ አጠያያቂና አነጋጋሪ ነበር” የሚለው ነው፡፡ ፀሃፊው ይህን ያነሱት ኢህአዴግ ምርጫ 2002ን ለማሸነፍ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ወስዷል ለማለት ነው፡፡
“ምርጫ 97 ላይ ኢህአዴግ እንደመንግስት ስልጣኑን ለመነጠቅ ተቃርቦ ነበር”  የሚለው ጉዳይ ከእውነትነት ይልቅ ስሜታዊነቱ ያይላል፡፡ እርግጥ ነው በ1997 ምርጫ ከዚያ ቀደም በ1987 እና 1992 ከተደረጉት ምርጫዎች ጋር ሲነፃፀር ተቃዋሚዎች በክልልና በፌደራል ም/ቤት ውስጥ ከፍተኛ መቀመጫ አግኝተዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ማስተዳደር የሚያስችል ድምፅ አግኝተዋል፡፡ ይህ ግን ኢህአዴግ ገዢ ፓርቲ መሆን የሚያስችለውን አብላጫ ድምፅ አላሳጣውም፡፡
ሆኖም ቅንጅት ከፍተኛ ድምፅ ባገኘባቸው ስፍራዎች ያሉ ድምፅ ሰጪዎቹን ውክልና ዋጋ እንዳለው ቆጥሮ መቀበል አልፈለገም፡፡  ድምፅ ሰጪዎቹ በአመፅ ስልጣን ለመንጠቅ የሚያስቸሉ ኃይል እንዲሆኑለት ዓልሞ የመንግስት ስልጣን ለመንጠቅ ሁከት ቀስቅሷል፡፡ የማነ ኢህአዴግ ስልጣኑን ለመነጠቅ ተቃርቦ ነበር ያሉት ይህን ይሆን? ይህም ቢሆን ግን በጥቂት ከተሞች ጎዳና ላይ ከተቀሰቀሰ ሁከትነት ያለፈ ስልጣንን በሕገወጥ መንገድ ለመመንተፍ የሚያስችል አቅም ያለው ስላልነበር ኢህአዴግ ስልጣኑን ሊቀማ ተቃርቦ ነበር አያስብልም፡፡
ይህ የከተማ ሁከት ከኢህአዴግ ይልቅ ሁከቱን የጠነሰሱትንና የመሩትን ወገኖች ብቻ ነው የጎዳው፡፡ ተቃዋሚዎችን በቀጣዩ ምርጫ ላይ ለአስከፊ ሽንፈት የዳረጋቸው በ97 ምርጫ ላይ ሕዝብ የሰጣቸውን የሥልጣን ውክልና አሻፈረኝ ማለታቸው እንዲሁም ሕገወጥ ድርጊት ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ፀሐፊው እንዳሉት የፕሬስ አዋጅ - የመረጃ ነፃነትና የመገናኛ ብዙሃን  አዋጅ እንዲሁም የሲቪክ ማህበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅ ተቃዋሚዎች በ2002 ምርጫ ላይ እንዲሸነፉ አንዳችም አስተዋዕኦ አልነበረውም፡፡ የፕሬስ አዋጁ ረቂቅ መዘጋጀት የጀመረው ከምርጫ 97 በፊት ነበር፡፡ የማነ በወቅቱ በተለይ ጋዜጠኛ ከነበሩ ይህንን ያውቃሉ፡፡ ይህን የማያውቅ አንድም ኢትዮጰያዊ ጋዜጠኛ የለም፡፡
ከምርጫ 97 በፊት ቢያንስ ለሁለት ዓመታት የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤቶች በፕሬስ አዋጁ ረቂቅ ላይ እንዲወያዩ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ባለድርሻ አካላት፤ አሳታሚዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ሌሎችም  አገሪቱ ላይ ከፀደቁ ሕጎች ሁሉ በተለየ ሁኔታ በተደጋጋሚ ተወያይተውበታል፡፡ ይህ የተደረገው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት መገለጫ የሆነው የፕሬስ ነፃነትን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ማንኛውም ዜጋ ያለምንም ችግር መረጃ ማግኘትና ማሰራጨት መጠቀም የሚያስችለው ድንቅ ስርዓት ተዘርግቷል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ባለፈው አመት የፕሬስ ቀን በተከበረበት ስነስርአት ላይ ረቂቅ የፕሬስ አዋጁ ላይ በግንባር ቀደምትነት ሲሳተፉ የነበሩትና የማነ ፅሁፋቸውን ያቀረቡበት ሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ (አሁን የአሳታሚ ድርጅቱ ስራ አስኪያጅ) የሆኑት አቶ አማረ አረጋዊ ምስክርነታቸውን ሰጥተውበታል፡፡
ረቂቅ አዋጁን ባለድርሻ አካላት በሙሉ በውይይት እንዲያዳብሩት ማድረግ ያስፈለገው በተለይ የዴሞክራሲ ዋነኛ መሰረት የሆነው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና መረጃ የማግኘት መብትን የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሃሳብን በነፃነት ለመግለፅ ቀዳሚ የዴሞክራሲ እሴት ትልቅ ዋጋ በመስጠቱ ነው፡፡
ይህ መሆኑ የፕሬስ አዋጁን መንግስት ወይም ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ በራሱ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ሌሎችን ለማፈን ከላይ ወደታች ያላወረደው መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ዴሞክራሲን ማጎልበት፣ ሕዝቡና የፖለቲካ ፓረቲዎች የዴሞክራሲው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ላይ ያተኮረ መሆኑንም ያመለክታል፡፡  በመሆኑም አዋጁ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ሃሳብን በመግለፅና በመቀበል ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲጠቀሙ ከማድረግ በቀር አንዳችም መሰናክል አልፈጠረባቸውም፡፡
ወደ የበጎ አድራጎትና ሲቪክ ማህበራት አዋጅ እንመለስ፡፡ ይህ አዋጅ በሲቪክ ማህበራት መቋቋምና መንቀሳቀስ ላይ አንዳችም ገደብ አላኖረም። አዋጁ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት እንዲቋቋሙና እንዲንቀሳቀሱ ይፈቅዳል።
አዋጁ ላይ ቀደም ሲል ከነበረው የተለየ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው ከ10 በመቶ በላይ የገንዘብ ምንጫቸው ከውጭ የሆኑ ድርጅቶችና ማህበራት በውጭ ድርጅትነት እንዲመዘገቡ የሚደነግግ መሆኑ ነው። ከዚሁ ጋር አያይዞ የውጭ ድርጅቶችና ማህበራት በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባት አይችሉም የሚል ድንጋጌ አስቀምጧል። ልብ በሉ ኢትዮጵያዊ ማህበራት ግን ያለአንዳች ገደብ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የመንቀሳቀስ መብት ያላቸው መሆኑ በአዋጁ ተረጋግጧል፡፡
ይህ የሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳይ የማንም የውጭ ወገን ጉዳይ ሳይሆን የዜጎችና የዜጎች ብቻ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ማንኛውም ገንዘብ ያለው የውጭ አካል በዚህ የዜጎችና የዜጎች ብቻ  በሆነው ፖለቲካዊ ጉዳይ ውስጥ በ"እኔ አውቅልሃለሁ" ጣልቃ የመግባት መብት ሊኖረው አይገባም። ከዚህ በተረፈ ከላይ እንደተጠቀሰው በኢትዮጵያውያን ዜጎች የተቋቋሙ ድርጅቶችና ማህበራት ግን ያለምንም ገደብ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ ሙሉ መብት ያላቸው መሆኑን ህጉ አረጋግጧል።
“አዋጁ አፋኝ ነው” የሚል አቋም ያላችው፣ የውጭ ማህበራትና ድርጅቶች በኢትዮጵያ ጉዳይ ውስጥ ገብተው ማቡካት የሚችሉበት ዕድል ካገኙ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ባላገናዘበ ሁኔታ ለእነርሱ አድረን ወይም አጎብድደን ስልጣን ልናገኝበት የምንችልበትን ሁኔታ ያመቻቹልናል የሚል እምነት ያላቸው ወገኖች ናቸው፡፡የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከዜጎች ፍቃድ አውጥተው በፈለጉት መንገድ መጠምዘዝና ጥቅማቸውን የማስጠበቅ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢነት ራዕይ ያላቸው የውጭ ኃይሎችም አዋጁ አልተመቻቸውም፡፡ አዋጁን በተደጋጋሚ የሚተቹት እነዚህ ወገኖች ናቸው፡፡
የውጭ ድርጅቶችና ማህበራት፣ የዜጎች ጉዳይ ብቻ ከሆነው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውጭ ባሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ግን ያለምንም ገደብ የመሳተፍ መብት ያላቸው መሆኑ አዋጁ ያስረዳል። ይህ አዋጅ ከወጣ በኋላ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት እንዲቋቋሙና እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ፡፡  አዋጁ ከወጣ ወዲህ ቀደም ሲል አዲስ ተደራጅተው ህጋዊ እውቅና ያገኙ ማህበራት ቁጥር መጨመር ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ችሏል።
ከአዋጁ በፊት በአመት ይመዘገቡ የነበሩት የውጭና የአገር ውስጥ ማህበራትና ድርጅቶች 80 ያህል ሲሆኑ፣ ከአዋጁ በኋላ ባሉት አመታት ይህ አሃዝ ወደ 300 አድጓል።በ2002 በተካሄደው አራተኛ ዙር ምርጫ ላይ ከ12 ሚሊዩን በላይ ኢትዮጰያዊያንን የሚወክሉ ከ10 በላይ ሲቪክ ማህበራት ከማንኛውም ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢ በተለየ ሁኔታ በመላ አገሪቱ በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ በመገኘት ምርጫውን መታዘባቸውን ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል።
እንግዲህ ይህ አዋጅ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ተቃዋሚዎች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳደረውና ሊያሳድር የሚችለው በምን አኳኋን ይሆን? ያም ሆነ ይህ መድረክና አስከተልኩዋቸው ያላቸው ፓርቲዎች ሰሞኑን ከመጪው አካባቢያዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ያነሱትና ፀሃፊ የማነ ሊያራግቡት የፈለጉት ጉዳይ መሰረተ ቢስና ምንም ያህል ቢራገብ የማይነድ ሙት ጉዳይ መሆኑ ነው።
በመሆኑም መድረክም ሆኑ አብረውት እንደሆኑ የተገለፁት ፓርቲዎች በዚህ ምርጫ ላይ ዕጩዎችን መወከል የሚችሉ ከሆነና ለህዝብ የሚያቀርቡት ግልፅ አማራጭ ካላቸው መወዳደር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምርጫው ላይ መሳተፋቸው ለቀጣይ የፓርቲያቸው ጥንካሬና ሕልውናም አስፈላጊ ነው።  ከምርጫ ውጭ መሆን ራሳቸውን ከህዝብ ዕውቅና የሚሰውር መቀመቅ ውስጥ ቸንክሮ ዘለቄታዊ ህልውናቸውን ከማጥፋት ያለፈ ምንም ዓይነት ፋይዳ አያስገኝላቸውም፡፡ ለምርጫው ዕጩዎችን ማቅረብ የማይችሉ እና/ወይም ለህዝብ የሚያቀርቡት የነጠረ ፖሊሲ የለንም የሚል አምነት ካላቸው ደግሞ ለቀጣይ ምርጫዎች የሚያበቃቸውን የቤት ስራቸውን እየሰሩ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ከሁለት ግዜ በላይ ምርጫ ላይ አለመሳተፍ ግን ሕጋዊ እውቅናቸውን የሚያስነጥቅ መሆኑን ሳይዘነጉ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ የሚሻው ምርጫን አስታኮ ውዝግብ የሚፈጥረበትን ሳይሆን የተጀመረውን ፈጣን ልማት የሚያስቀጥልና ድህነትን ለመቅረፍ የተሻለ አማራጭ ይዞ ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ውድድር ራሱን ያዘጋጀ ፓርቲ ነጥሮ እንዲወጣ ነው፡፡ ለዚህም ጠንካራ አቋም ይዞ ምርጫ ማካሄድ የመረጠበት ደረጃ ላይ መድረሱን ማስተዋል አዋቂነት ነው።