የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች የአየር ንብርት ብክለትን ለመቀነስ ፋይዳ ያለው ጥናት መስራት ይጠበቅባቸዋል

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/2005(ዋኢማ) - የአካባቢ ልማት ትምህርቶችን ከጊዜው ጋር በማጣጣም ፋይዳ ያለው ጥናት በመስራት የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች የከባቢ አየር ንብረት ብክለትን ለመቀነስ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት አስታወቁ፡፡

''ቀጣይነት ላለው የአካባቢ ልማት '' በሚል መርህ ከምስራቅ፣ ከመካከለኛውና ከደቡብ አፍሪካ አገራት የተወከሉ 26 ዩኒቨርስቲዎች የሚሳተፉበት ዓውደ ጥናት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተጀምሯል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አድማሱ ጸጋዬ በዓውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በአፍሪካ እየደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ የአካባቢ ልማት ችግር ለመቅረፍ ዩኒቨርስቲዎች በአካባቢ ልማት ላይ የሚሰጡትን ትምህርት በማሻሻል ብዙ ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ ይኖርባቸዋል፡፡

በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ጥናት ምርምሮች እንዲካሄዱ በማድረግ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት በመስራት ለውጥ ያመጡ ስራዎች እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከቅድመ ምረቃ እስከ ዶክትሬት ደረጃ ለአካባቢ ልማት ጠቃሚ የሆኑ የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት የኢንዱስትሪ መስፋፋት በአካባቢ ልማት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ዩኒቨርስቲው አበረታች ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው ሮድ ዩኒቨርስቲ የተወከሉት ፕሮፌሰር ሄላሎትዝ ሲስትካ በበኩላቸው የአካባቢ ልማት ትምህርት ዘርፈ ብዙ ስለሆነ የአፍሪካ ዩንቨርስቲዎች ይህን በመረዳት አዳዲስ የትምህርት ክፍሎችን በመጨመርና ለውጥ አምጪ ጥናትና ምርምር ማካሄድ ይኖርባቸዋል።

መንግስታትም የአየር ፀባይ መለዋወጥ ኢኮኖሚያቸው ላይ ከባድ ተፅኖ እንደሚያደርግ በመረዳት ዩኒቨርስቲዎች ለሚሰሩት ስራ የሚሰጡትን ድጋፍ ማሳደግ ይኖርባቸውል ብለዋል፡፡

ከምስራቅ፣ ከመካከለኛውና ከደቡብ አፍሪካ አገራት የተወከሉ 26 ዩኒቨርስቲዎች የሚሳተፉበት ዓውደ ጥናት ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ተሳታፊዎቹ በአካባቢ ልማት የተሰሩ ጥናቶችና ተሞክሮዎች አቅርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው ኢዜአ ዘግቧል።