ድህነትን ታግሎ ለመጣል!

  • PDF

ታከለ ዓለሙ

ኢትዮጵያ የታላቁና የገናናው የአባይ ወንዝ መፍለቂያ ማህፀን ነች፡፡ አባይ በሱዳኖችም በግብፆችም “አባታችን” ተብሎ የሚወደስ ወንዝ ነው፡፡ የአባይ አምላክ ብለውም ከጥንት ዘመን ጀመሮ ያመልካሉ፡፡ ገምሻራው አባይ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ወንዞችን አስገብሮ ሲያበቃ በታላቅ ግርማ ሞገስ ነው የኢትዮጵያን ምድር ለቆ ሱዳን ከሱዳን ግብፅ የሚገባው፡፡  ሱዳንም ግብፅም በአባይ ውኃ በመጠቀም በጃንሆይ ዘመን ግድብ ሰርተዋል፡፡

ወደ ኋላ ለመመለስ ከሱዳኖች ጋር ብዙ ጊዜ ጦርነት ገጥመናል፡፡ ከደርቡሾች ጋር ተዋግተናል፡፡ ከመተማ ጎንደር ከተማ ድረስ ዘልቀው አቃጥለው አውድመው የተመለሱበትም ታሪክ አለ፡፡ አፄ ዮሀንስ ለኢትዮጵያ አገራቸው አንገታቸውን የተቀሉት መተማ ላይ ከሱዳኖች ጋር በተደረገው  ጦርነት ነው፡፡

ቴዎድሮስም ከአጎታቸው ከዳጃዝማች ክንፉ ጋር በነበሩበት ወቅት አብረው ዘምተው ከደርቡሾች ጋር ተዋግተዋል፡፡ ግብፆችም የአባይን ውኃ ከምንጩ ለመቆጣጠር በነበራቸው ፍላጎት ከኢትዮጵያ ጋር መዋጋታቸውን የታሪክ ዋቢ ያስረዳናል፡፡ የሁለቱም የጋራ ቅኝ ገዥ እንግሊዝ የነበረች በመሆኗ፤ ግብፆችና ሱዳኖች ለረዥም ጊዜ ከነበራቸው ቅርበትና ቁርኝት ሌላ በትልቁ የኢትዮጵያው የአባይ ወንዝ (ፈለገ ዮርዳኖስ) ጉዳይ በጋራ እንዲቆሙ፣ እንዲመክሩና እንዲዘክሩ ሲያደርጋቸው ኖሯል፡፡

በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ አንድ ቀን አቅም አግኝታ የአባይን ወንዝ ልትገድብ ትችላለች፤ ኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብት ካደገችና ከጎለበተች ይህን ከማድረግ የሚያግዳት አለመኖሩን ያምናሉ፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ እንደ አገር ተረጋግታ፣ ሠላሟን አጣጥማ፣ በምጣኔ ሀብት እንድታድግና እንድትበለፅግ አይፈልጉም፡፡ ለዚህም እጅግ በጣም ብዙ የቤት ሥራ ለኢትዮጵያ እየሰጧት በጦርነት፣ በግጭትና  በውጥረት እንድትኖር አስገድደዋታል፡፡

የዐረብ ናሽናሊስቱና የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበረው ኮሎኔል ጀማል አብደል ናስር ከዚህ ሥጋቱ በመነሳት ነው ኤርትራን ዐረባዊት ናት በሚል ጀብሀ የተባለውን እስላማዊ ፓርቲ በኤርትራ ተወላጅ ሙስሊሞች አማካይነት በማቋቋም፤ ሙሉ የገንዘብ፣ የድርጅትና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ያደረግ የነበረው፡፡ ተዋጊዎችም አሰልጥነዋል፡፡

የመጀመሪያው የጀብሀ መሪ እድሪስ አዋቴ ሌሎችም የሰለጠኑት በግብፅ ወታደራዊና የደህንንት ባለሙያዎች ነው፡፡ ሱዳንም በዚያን ወቅት የበኩሏን ድጋፍና ሙሉ ትብብር አድርጋለች፡፡ ሱዳን ውስጥ ጦር ሰፈር ሰጥታለች፡፡ የድርጅታቸው ቢሮ  ካርቱም፤ ሱዳን ካይሮ፤ ግብፅ ነበር፡፡ በዚህም አላበቁም  በምሥራቅ ኢትዮጵያን በጦርነት ወጥሮ ለመያዝ ሙሉ ድጋፍ ለሶማሊያ መንግሥት ይሰጡ ነበር፡፡ የሶማሊያ የመጨረሻ ፕሬዚዳንት የነበረው ጄኔራል ዚያድ ባሬ እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ የግብፅ መንግሥት በገንዘብም፣ በጦር መሣሪያም፣ በሥልጠናም ሙሉ ድጋፍ አድርጎለታል፡፡

ጃንሆይ ከሥልጣን ሲወርዱ በኢትዮጵያ አለመረጋጋት አለ፤ መሣሪያና ሠራዊቷ ትንሽ ነው በሚል ይህን አጋጣሚ መጠቀም አለብን ብሎ ዚያድባሬ ግዙፍ የእግረኛ ክፍለ ጦሮችን፣ ታንከኛ፣ መድፈኛ፣ እንዲሁም የአየር ኃይል ተዋጊ ጄቶቹን አሰልፎ ኢትዮጵያን ወግቷል፡፡ 700 ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያን ግዛት ጥሰው ገብቷል፡፡ የኦጋዴንና የሐረርን ብዙ አውራጃዎች ተቆጣጥሯል፡፡ ጅጅጋ፣ ደገሀቡር፣ ፊቅ፤ ካራማራ፤ ፈዲስ ሌሎችንም ይዟል፡፡

ግብፆች የአባይን ወንዝ መነሻ ለመቆጣጠር እንደተመኙት ሶማሌዎችም የአዋሽ ወንዝ መፍለቂያ ድረስ የእኛ ነው እስከ ማለት ደርሰው ነበር፡፡ ተዓምረኛዋ ኢትዮጵያ በወቅቱ በአጠቃላይ አራት ክፍለ ጦርና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ክፍሎች ነበሯት፤ ምርጥ የተባለውና ኤፍ-አምስት ተዋጊ ጄት የታጠቀ አየር ኃይልና ብቁ የተባሉ አብራሪዎች ነበሯት፡፡ ሶማሊያም ሚግ ሃያ ሦስት ተዋጊ  ጄት ታጥቃለች፡፡

ጃንሆይ ሥልጣን ከመልቀቃቸው በፊት ከአሜሪካን የጦር መሣሪያ  ግዥ ፈፅመዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ግን አልገባም፡፡ ደርግ እንዲሰጠው አሜሪካንን ቢጠይቅ ተከለከለ፡፡ ስለዚህም ፊቱን ወደ ራሺያ አዙሮ በዱቤ ግዥ በርካታ የጦር መሣሪያና ተዋጊ ጄት ገዛ፡፡ የመኖች ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ለመሰለፍ ሙያተኞች ላኩ፡፡ ኩባ ተዋጊ ሠራዊት ላከች፡፡ በአጭር ጊዜ 300 ሺህ ሚሊሺያ ሠራዊት ከመላው ኢትዮጵያ ተውጣጥቶ በሦስት ወር ሥልጠና ብቻ ወራሪውን የሶማሊያ ሠራዊት በሁሉም ግንባር እየተዋጋ ከኢትዮጵያ መሬት ጠራርጎ አስወጣው፡፡

ከሶማሊያ መንግሥት ጀርባ ግብፅ፣ ሱዳንና አንዳንድ የዐረብ አገሮችም ነበሩ፡፡ የሶማሊያ መንግሥት የመሬት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ከጀርባ ያሉት ግብፅን የመሰሉ ኃይሎች በዚህ መልኩ ፀረ - ኢትዮጵያ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ የሚረዱበት ዋነኛው ምክንያት ኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት አግኝታ የአባይን ውኃ እንዳትጠቀምበት ወይንም ለኃይል ማመንጫ ለመገደብ እንዳትችል ነው፡፡

የግብፅ መንግሥት ሶማሊያ መንግሥት አልባ ሆና በኖረችበት ዓመታትም የተለያዩትን አንጃዎች ሲረዳ ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጉዳይ አደራዳሪ  በሆነችበት መድረክ ሁሉ ተስማምተው አያውቁም፡፡ ስምምነቱን አፍርሰው አሥመራ የገቡት የጄኔራል ፋራህ አይዲድ ልጅ ሁሴን አይዲድም ሆነ፣ ዳሂር አዌይስ ሙሉ  እርዳታ የሚያገኙት ከግብፅ ነው፡፡  አሁንም ከኢትዮጵያ  ኦጋዴንን እገነጥላለሁ ብሎ የሚዋጋው “የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር” የሚረዳው በግብፅ ነው፡፡ ቀድሞ ለእነ መሐመድ ጃራ እንቅስቃሴ፤  ኦነግንም ጭምሮ ግብጽ እርዳታና እገዛ ታደርጋለች፡፡

የአሥመራው መንግሥትም በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን ለመውጋት በሚያደርገው ትግል ኦነግን፤ ኦብነግን፤ የሶማሊያ አንጃዎችን፤ በትጥቅ፣ በሥልጠና፤ መጠጊያ በመስጠት፤ ሶማሊያ ድረስ ወታደራዊ አስልጣኞችና የደህንነት ባለሙያዎችን በመላክ ከምፅዋና አሰብ በመርከብ እንዲሁም በአውሮፕላንም የጦር መሣሪያ በመጫን አርጌሣና ባይደዋ በማራገፍ ሲረዳ ቆይቷል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አጣሪ ቡድን ሶማሊያ ተገኝቶ ባደረገው ምርመራና ማጣራት በተገኘው ተጨባጭ ማስረጃ ለአሽባሪዎች እንደሚረዳ በመረጋገጡ   እቀባ የተጣለበትም ለዚህ ነው፡፡

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በባድመ ምክያት ጦርነት ከፍቶ ሲዋጋ ለሻዕቢያ ሠራዎት የጦር መሣሪያ ፈንጂና ቦምብ ይሰጠው የነበረው ከግብፅ ነው፡፡ ለዚህም የተማረኩት መሣሪያዎቻቸው ማን እንዳመረታቸው በግልጽ ስለሚታይ ክርክር ውስጥ አያስገባም፡፡

በሌላ ወገን ሱዳን በማንኛውም ጊዜ የግብጽ ተባባሪ በመሆን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንቅፋትና መሰናክል ሲፈጥሩ፤ የተለያዩ ቡድኖችን መሣሪያ እያስታጠቁ ግጭትና ጦርነት እንዲነሳ ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡

ይህን የተገነዘበው ደርግ በሶማሊያ በኩል የምዕራብ ሶማሊያ ነፃ  አውጪ ንቅናቄን፣ በሱዳን በኩል በኮሎኔል ጆን ጋራንግ ይመራ የነበረውን የደቡብ ሱዳን ነፃነት ንቅናቄን አሁን ነፃ የወጡትን በሥልጠናና በትጥቅ እያገዘ ኢትዮጵያ ላይ የጫሩት እሣት ተመልሶ በእነሱ ላይ እንዲነድ አድርጓል፡፡

ጃንሆይ ጠንቅቀው እያወቁ የሱዳንና የግብፅን ጉዳይ በከፍተኛ ዲፕሎማሲ ይዘውት ኖረዋል፡፡ ደርግ ከሻዕቢያ ጀርባ ሱዳንና ግብፅ መኖራቸውን በሚገባ ያውቃል፡፡ ቢሆንም በጦርነት ሲጋፈጥ አልፏል፡፡

ኢትዮጵያን የማስተዳደር ኃላፊነት የተረከበው ኢሕአዴግ ግር የተሰኘው በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ነበር፡፡ ቢሆንም ሁሉንም ጉዳይ ጠንቅቆ መረዳትና መገንዘብ ቻለ፡፡ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ መንገድንም ዋነኛው አጀንዳው አድርጎ መረጠ፡፡

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚመራው መንግሥት የጎረቤት አገሮች ሠላም ለኢትዮጵያ ሠላምም ወሣኝ ነው፤ በምጣኔ ሀብት ትስስርና በመደጋገፍ፤ ለጋራ እድገትና ሠላም በትብብር መስራት ጠቃሚ ነው በሚለው መርህ መሠረት ተንቀሳቅሷል፡፡

ኢህአዴግ በሶማሊያ በኩል የነበረውን ብዥታ አጥርቷል፡፡ ሶማሊያ የዓለም አቀፍ አሸባሪዎች መናኸሪያ መሆኗ ከማንም በላይ የኢትዮጵያን አገራዊ ጥቅምና ደህንነት የሚፈታተን ታላቅ አደጋ በመሆኑ፤ የአገሪቱን ድንበር አልፎ በመግባት በዓለም አቀፍ የጅሀድ ተዋጊዎች አማካይነት ጦር ሠፈር አቋቁሞ ሲንቀሳቀስ የነበረውን አክራሪና አሸባሪ ቡድን በወሰደው የማጥቃት እርምጃ ደምስሷል፡፡ ይህን ቡድን ማን እንደሚረዳው ይታወቃል፡፡ እንዲህም ሆኖ ከአገሪቱ ጋር አተካራ መግጠም አልተፈለገም፡፡

አልሻባብ የተባለው የአልቃይዳ ክንፍ የሆነው እክራሪ እስላማዊ ቡድን፤ መንግሥት አልባ በሆነችው ሶማሊያ በመንሰራፋቱ፤ ከኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ባለው ቅርበት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እየዘለቀም ተደጋጋሚ ጥቃት ለማድረስ በመሞከሩ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ከማስከበር አልፎ ሶማሊያ መሬት በመግባት አልሸባብን በሚገባ ቀጥቶታል፡፡

ለዚህ ነው አልሻባብ በአቶ መለስ ዜናዊ ሞት ተደስቶ መግለጫ ያወጣው፡፡ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ አበቃላትም ያለው፡፡ ኢትዮጵያ በድንበሯም ሆነ ከድንበሯ አልፋ ጠላቶቿን ስትዋጋ ከእነዚህ ኃይሎች ጀርባ ሻዕቢያና አንዳንድ የዐረብ አገራት እንዳሉ ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡

አልኢትሀድ፣ ኦነግ፣ አብነግ፣ አልሻባብ፤ በኢትዮጵያ ላይ በተለያየ ጊዜ ጦርነት ሲከፍቱ የገንዘብ፣ የመሣሪያና የሥልጠና ድጋፍ፣ የመረጃ ልውውጥ ጭምር ከእነማን እንደሚያገኙ ኢትዮጵያ ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ምድር ተሰልፋ ከጀርባ በሌላ ኃይል እየታገዙ የውክልና ጦርነት (proxy war) የከፈቱባትን ኃይሎች የተዋጋችው አንዳንድ ተቃዋሚዎች እንደሚዘባርቁት ለአሜሪካን ጥቅም መከበር ሲባል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ለራሷ ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ስትል ብቻ ነው የተዋጋችው፡፡ ተገቢም፤ ትክክለኛም እርምጃ ነው፡፡

ሶማሊያ የኢትዮጵያ ጎረቤትና ረዥም ድንበር የምትጋራ አገር እንጂ የአሜሪካን ጎረቤት አይደለችም፡፡ በሶማሊያ እየተንሰራፋ የሚመጣው የአሸባሪነትና የአክራሪነት አደጋ በቅርብ የሚያጠቃው ኢትዮጵያን ነው፡፡ ስለዚህ ነበር መሰለፍና መዋጋት የነበረብን፡፡ ዛሬም ነገም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ የሚነሱትን ጠላቶች ያለምህረት ትዋጋለች፡፡

ዛሬ ከሱዳንም ሆነ ከግብጽ ጋር ወንድማዊና የተለሳለሰ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አለን፡፡ በንግድና ኢንቨስትመንት በሌሎችም መስኮች ትብብር አለን፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የአካባቢው ተደማጭና በሁሉም መስክ ተፅዕኖ አሳዳሪ ኃያል አገር ለመሆን የበቃችው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካይነት ባገኘችው የገዘፈ ተቀባይነት፤ ባስመዘገበችው ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት፤ በመከላከያ ተቋሟ ዘመናዊነትና ብቁነቷ፤ እንዲሁም በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ማስከበር ግዳጅ በአንደኛ ደረጃ ተመራጭ መሆኗ ነው፡፡፡

ከዚህም በላይ ያለምንም የውጭ መንግሥታት ድጋፍና እርዳታ የአባይን ወንዝ በራሴ ገንዘብ እገድባለሁ፤ ለልማት አውለዋለሁ፤ በአፍሪካ ትልቁ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ይሆናል ብለው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሥራው እንዲጀመር የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡

አባይን የመሰለ ወንዝ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የገዛ ሀብቷን ሳትጠቀምበት ቀርታ በተደጋጋሚ ዘመናት በድርቅና በረሀብ ስትመታ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ ለውጭ እርዳታና ልመና ሲጋለጡ፤ ክብራቸው ሲዋረድ ኖሯል፡፡

ይህን አሳፋሪና አንገት አስደፊ ታሪክ የሚለውጥ ጀግና መሪና ጀግና ትውልድ ተፈጥሮ አባይን ገድቦ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማደስ ታጥቆ ሊነሳ ትላልቆቹም ትናንሾቹም መንግሥታት በጫጫታ ተተራመሱ፡፡ ግድቡ እንዳይሰራ፤ እንዲቆም፤ እንዲዘገይ፤ የሚል ስፊ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ ተከፈተ፡፡ ኢትዮጵያ በድህነቷ ዝንተ ዓለም ትቀጥል፤ እኛም በጌትነት እስከ ወዲያኛው እንዝለቅ እንደማለት ይቆጠራል ጩኸታቸው፡፡

በምንም መልኩ ለኢትዮጵያ እንደማይተኙም ይታወቃል፡፡ ተላላኪ፤ ቅጥረኛ፤ አሻጥረኛ፤ ከመግዛትና ከማሰማራት፤ እስከ ወታደራዊ እርምጃ ድረስ፤ እቅድ ፕላን እንደሚያወጡ ዝግጅት እንደሚያደርጉ ኢትዮጵያ ታውቃለች፡፡ ጦርነትን አትናፍቅም፡፡ ሁሌም ንቁ ሆና  ግን ትጠብቃለች !!


አሁንም ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ  ለሶማሊያም፣ ለሱዳንም፣ ለግብፅም ወዳጅ ነች፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁን የሕዳሴ ግድብ (የአባይን) ወንዝ በተመለከተ ለአገሯ ጥቅም ለማዋል የወሰደችው የግንባታ እርምጃ የማንኛውም የተፋሰሱን አገሮች በተለይም የሱዳንንም ሆነ የግብፅን የውኃ ድርሻ አይቀንስም፡፡ ውኃው ተገቢውን የኃይል ማመንጨት ተግባር አከናውኖ ተመልሶም ወደ መስመሩ በመግባት ፍሰቱን ወደ የአገራቱ ይቀጥላል፡፡ ይኼንንም እውነት እንዲረዱ የተቋቋመው የጋራ ጥምር ኮሚቴ በሠላም እየሰራ መግባባት ላይ እየተደረሰ ነው፡፡

በዓለም በርዝመት ረዥሙ የሆነው የአባይ ወንዝ መፍለቂያ የሆነችው ኢትዮጵያ የራሷም ሕዝብ፣ የጎረቤት አገር ሕዝቦችም ውኃ እንዲጠሙ፤ እንዲራቡም፤ አትፈቅድም፡፡ እንዲያውም እያላት እንደሌላት ሆና ረዥም ዘመን በረሀብና ችግር ያሳለፈችው ኢትዮጵያ ነች፡፡ ተፈጥሮ ያደለንን ፀጋ በጋራ መጠቀም እንችላለን፡፡

መቼም ኢትዮጵያን በመብትሽ መጠቀም አትችይም የሚላት ማንም የለም፡፡ እንግሊዞች  ከአውሮፓ በቅኝ ገዥነት መጥተው የአባይን ውኃ ለሁለቱ ቅኝ ግዛቶቻቸው ሱዳንና ግብፅ በኮታ ያከፋፈሉበት ታሪክ ዛሬ ላይ አይሰራም፡፡ ዛሬ ለሱዳንም ለግብፅም የሚበጃው ከኢትዮጵያ ጋር ተከባብሮና ተደማምጦ በጋራ እየመከሩ መስራት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬ ታላቅ ጦርነት የገጠመችው ድህነትን ታግሎ ለመጣል ነው፡፡ የተፈጥሮ ሀብቷን ለመጠቀም ነው፡፡ ከድርቅና ረሀብ ለመላቀቅና ራሷን ለመቻል ነው፡፡