ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለኢንዱስትሪው መሠረት ነው

  • PDF

አንተነህ ተሰማ

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መሠረት የግብርናው ዘርፍ እንደሆነ ይታወቃል። ግብርናው ምጣኔ ሀብቱን ሊመራ  በቂ ምክንያት እንዳለው የተሰወረ አይደለም። አገሪቱ ያላት ሰፊ ሃብት መሬትና የሰው ጉልበት ነው።

ሰፊ ለእርሻ ልማትና ሌሎች ግንባታዎች ሊውል የሚችል የመሬት ሃብት አላት። ይህንን መሬት በዘመናዊ መንገድ ለማልማትና የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ የሚችል የሰው ኃይልም አላት። በዚህ ምክንያት  የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት መሠረት ሊሆን የሚችለውና ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተነድፎ ሥራ ላይ የዋለው ከዚህ መነሻ ነው። 

በርካቶች ለምን ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ግንባታ ፖሊሲ አይኖረንም ብለው የተከራከሩበት ወቅት እንዳለ የሚታወስ ነው። ዳሩ ግን የአንዲት አገር እድገት በመጨረሻው ጠርዝ በኢንዱስትሪ የሚወሰን ቢሆንም በቂ ካፒታል በሌላት አገር ለኢንዱስትሪው እድገት መሠረት ለመጣል ግብርናው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ማወቅ አያዳግትም። 

ኢትዮጵያ በግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት እየተመራች ትገኛለች። የግብርና ልማቱን ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር በማስተሳሰር በዘላቂነት ኢንዱስትሪውን በአስተማማኝ መንገድ ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል። የኢንዱስትሪ መሠረት የመጣሉ አጀንዳ በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይ በግልጽ ሰፍሯል። 

በእቅዱ መሠረት  ግብርና መር የሆነውን የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት መሠረት በአገሪቱ ያለውን የኢንዱስትሪ ልማት በማሳደግና በሂደት  የምጣኔ ሀብቱ መሠረት እንዲሆን ለማድረግ አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።

በዚህ መልክ እየተስፋፋ የመጣው የኢንዱስትሪ ልማት የተለያዩ ዘርፎችን ያጠቃልላል። ዘርፉ ኮንስትራክሽን፣ የኃይል ምንጭ፣ ማዕድንና የመሳሰሉትን የሚያጠቃል ቢሆንም በዚህ ጽሁፍ የተዳሰሰው ግን የማኑፋክቸርንግ ዘርፉ ነው።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣው የመካከለኛና ከፍተኛ የማኑፋክቸርንግ እንዱስትሪ በእንዱስትሪ ሚኒስቴር ድጋፍና ክትትል እየተደረገለት ከጊዜ ወደ ጊዜ የእድገት መጠኑ እየጨመረ መምጣት ችሏል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ   የካፒታል ወጪ የጠየቁና  ከፍተኛ የማምረት አቅም ያላቸው እንዱስትሪዎች ተቋቁመው ወደ ማምረት ተግባር ተሸጋግረዋል። በርካታ ሌሎች እንዱስትሪዎችም በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ። የእንዱስትሪው ዘርፍ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ከእንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያሳያል።

በቀጣይ የሚኖረው የምጣኔ ሀብት የእድገት አቅጣጫ የሚመሰረተው በኢንዱስትሪው ይሆን ዘንድ ከወዲሁ አስተማማኝ መሠረት ለመጣል አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራበት ይገኛል። 

መንግሥት አገሪቱ ከተዘፈቀችበት የድህነት ማጥ ለማውጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ ራዕይ ሰንቆ በመስራት ላይ ይገኛል።

አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ በመንደፍና በአገባቡ በመተግበር ላለፉት ዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት የሚያበረታታ የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ ተችሏል።

እስካሁን በተለያየ ጊዜና ደረጃ ከተተገበሩት የልማት ስትራቴጂዎች መካከል ከ1995 - 1997 ዓ.ም የተተገበረው የዘላቂ ልማት የድህነት ቅነሳ ፕሮግራም አንዱ ነበር። በዚህ ጊዜ አገሪቱ የተሻለ የምጣኔ ሀብት እድገት እያስመዘገበች የመጣችበት ሁኔታ መፍጠር ተችሏል።

በዚያን አጋጣሚ የተፈጠረውን መልካም ሁኔታ መሠረት በማድረግ ከ1998 – 2002 ዓ.ም የልማት እቅድ ተዘጋጅቶ በመተግበሩ አገሪቱ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት የምጣኔ ሀብት እድገትዋን በሁለት አኃዝ ማሳደግ  አስችሏታል።

ይህንን ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገትን መሠረት በማድረግ የአገሪቱን ለውጥ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ለማድረግ የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተነድፎ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል።

በእቅዱ በግልጽ እንደተቀመጠው በአምስት ዓመታት ጊዜ በማኑፋክቸሪንግ  ከ446 ነጥብ 5 ሚሊዮን እስከ 2 ነጥብ 63 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚያስችል ግብ ተጥሎ ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በእድገትና ትራንስፎርማሽን ዘመን መጨረሻ ላይ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እስከ 23 እጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ  አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ አግሮ እንዱስትሪ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የጨርቃጨርቅና አልባሣት፣ ኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶችን የሚያጠቃልለው ይህ ዘርፍ ባለፉት ሁለት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድ አፈጻጸም የመጀመሪያ ዓመታት የነበረው አፈጻጻም  ሲታይ እጀግ አበረታች እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።  

ይህንን  ለውጥ ለመገንዘብ ያስችለን ዘንድ ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየውን አፈጻጸም በአኃዝ አስደግፎ ማየት ጠቃሚ ይሆናል።

በ2003 ዓ.ም የነበረው የወጪ ንግድ አፈጻጸም የጨርቃጨርቅና አልባሣትና የቆዳና የቆዳ ውጤቶች  62 ነጥብ 22 እና  104 ነጥብ 34 ነበር። በተመሣሣይ መልኩ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶችና የፋርማሲቲካልና የኬሚካል ውጤቶች  34 ነጥብ 45 እና  6 ነጥብ 91 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቶ ነበር።

እላይ ከተገለፀው አኃዛዊ መረጃ ለመገንዘብ እንደሚቻለው በእድገትና ትራንስፎርማሽን እቅድ የአፈጻጸም ዘመን በመጀመሪያ ዓመት ከማኑፋክቸርንግ ዘርፍ የወጪ ንግድ አፈጻጸም የተገኘው አጠቃላይ ገቢ  207 ነጥብ 92 ሚሊዮን የአሜካን ዶላር ነበር።

በተመሣሣይ መልኩ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ሁለተኛ ዓመት አፈጻጸምም በተጠበቀው መልክ የተኬደበት ሁኔታ እንደነበር ለመገንዘብ ይቻላል።

ጨርቃጨርቅና አልባሣት 84 ነጥብ 63፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች 112 ነጥብ 6፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች 51 ነጥብ 75 እና  የፋርማሲቲካልና የኬሚካል ውጤቶች 7 ነጥብ 1 ነበር። በ2004 ዓ.ም በማኑፋክቸርንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ 255 ነጥብ 45 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት ተችሏል።

እላይ በተሰጠው መረጃ መሠረት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተገኘው አጠቃላይ የወጪ ንግድ 462 ነጥብ 37 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከማኑፋክቸሪን ዘርፍ መገኘቱን መረዳት ይቻላል። 

በ2004 ዓ.ም የነበረው አፈጻጸም ከ2003 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ47 ነጥብ 53 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብልጫ ያሳያል። ይህ የሚያመለክተው በየዓመቱ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እያደገ መምጣቱን ነው። 

የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ከመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር ለማስተሳሰር የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራት ከቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በማስተሳሰር በመደበኛ የትምህርት ፕሮግራምና በአጫጭር ሥልጠናዎች የዘርፉን አቅም ለመገንባት በሚያስችል መልኩ እንዲቃኙ ተደርጓል።  

በአገራችን የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆችም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት በማገዝ ላይ ይገኛል።

ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች የሚያደርጉት ድጋፍ እንዳለ ሆኖ የማኑፋክቸሪንገ ዘርፍን የበለጠ ለመደገፍ የሚያስችል በክህሎት የታነፀ አምራች ኃይል ለማፍራት በተለያዩ ፋብሪካዎች ተቀጥረው እየሰሩ ለሚገኙ ባለሙያዎች አጫጭር የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን በመስጠት የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። 

መንግሥት ከዚህም አልፎ የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች የተቀላጠፈ የፋይናንስ፣ የጉምሩክና የሎጅስቲክ አገልግሎቶች ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛል። 

እንደ መለዋወጫዎች፣ አክሰሰሪዎችና ኮምፒውተሮች የመሳሰሉ መሣሪያዎች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ የማድረግና ከውጭ በሚመጡት ላይም የጥራት ፍተሻ አገልግሎት ድጋፍ በመስጠት እያገዘ ይገኛል።  ከዚህም በተጨማሪ  የገበያና የምርት ግብይት ትስስር፣ የገበያ ማፈላለግ ማስተዋወቅና ማስተሳሰር እገዛዎች  እየተደረገ ነው።

መንግሥት ዘርፉን ለማገዝ ቀላል የማይባል እርምጃዎችን በየደረጃው ወስዷል። የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ጥራት በማረጋገጥ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ ያላሳለሰ ጥረት አድርጓል።

በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የተለያዩ ማበረታቻዎችንም አድርጓል። የጉምሩክና የቀረጥ ማበረታቻ አዋጅ ወጥቶ ሥራ ላይ እንዲውል ከማድረጉም በተጨማሪ ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ ኤጀንሲ ተቋቁሞ የሥራ አመራር ሥርዓትን ለማስረጽ በመስራት ላይ ይገኛል።

ካይዘን  የለውጥና የማሻሻል ፍልስፍና ነው። በጃፓን አገር ምርትንና ምርታማነትን ለማሻሻል በተደረገው ጥረት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የቻለ አሠራር ነው። ይህንን አሠራር በአገራችን ተግባራዊ ለማድረግ በተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ለመገንዘብ ይቻላል።

ዘርፉን ለማገዝ ከተወሰዱ ሌሎች እርምጃዎች መካከል የኢንዱስትሪ ዞንን የመከለል ተግባር ይገኝበታል። በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ዞን በሚመለከት የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ የማልማቱ ተግባር በክንውን ላይ ይገኛል።

ኢንዱስትሪው በቀጣይ 13 ዓመታት ሊመራበት የሚችል ስትራቴጂ የጥናት ሰነድ በመዘጋጀት ላይ መሆኑ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛነትን ያሳያል።

የማኑፋክቸርንግ ዘርፉ ተግዳራቶች በርካታ ናቸው። በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ የአቅም ውስኑነት የምርት ጥራት የተጠበቀውን ያህል አለመሆኑ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የምርት ማነስ፣ ዘለቄታዊ የገበያ ትስስር መፍጠር አለመቻልና የተገኘው የገበያ እድልም ቢሆን  እስከ መጨረሻው አሟጦ አለመጠቀም ይገኙበታል።

ሌላው ተግዳሮት ደግሞ የቅንጅታዊ አሠራር መላላት ነው። በተለይ ደግሞ በመንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ለወጪ ንግድ ሥራው የሚሰጡት የአገልግሎት ቅልጥፍና፣ ጥረትና ውጤታማነት ማነስ እንዳለበት መገመት ይቻላል።

ከዚህ ረገድ አምራቾች ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ በሚያስችል ደረጃ አለመገኘት ሌላው ችግር ነው። ከዚሁ ተለይቶ ሊታይ የማይችለው ሌላው ችግር ደግሞ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በማይወጡ ባለሀብቶች ላይ ተገቢው የእርምትና ማስተካከያ እርምጃ ወቅቱን ጠብቆ  አለመወሰድ ነው።

እነዚህ ተግዳራቶች ከውስጣዊ አሠራር ጋር ተያይዘው የሚመጡ ከውጫዊው ዓለም አንጻር ሊፈጠሩ የሚችሉ የዘርፉ መሰናክሎች እንዳሉ መገነዘብ የግድ ይላል። ከእነዚህ መካከል የዓለም ምጣኔ ሀብት አለመረጋጋት አንዱ ነው።

ከዚህና ከሌሎች ምክንያቶች በመነጨ መልኩ የውጭ ገበያ መቀዛቀዝና የገዥዎች መቀነስ የዘርፉን ምርታማነት በመቀነስ ረገድ ቀላል የማይባል አሉታዊ ጫና እንደነበረው መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህንን የተረዳው የኢትዮጵያ መንግሥት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከመንግሥት ጋር በመተባበር ለዘርፉ እንቅፋት የሆኑትን ተግዳራቶችን ለመፍታት ምርታቸውን ማሳደግ ይችሉ ዘንድ የተለያዩ የምክክር መድረኮች ተካሂደዋል።

አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት ዘመናቸው ከዘርፉ ባለሀብቶች ጋር ውይይቶችን በማድረግ ዘርፉ ላይ ተጋርጠው የነበሩ  ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ ችለዋል። በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱም ሆነ በዘርፉ ለወደፊቱ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች የችግሩ  የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ያላሳለሰ ጥረት አድርገዋል።

አገሪቱ የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በማሳካት መካከለኛ ገቢ ካላቸው  የዓለማችን አገራት ተርታ ለማሰለፍ ለምታደርገው ጥረት የማኑፋክቸርንግ እንዱስትሪ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በዘርፉ እየተካሄደ ያለው የአቅም ግንባታ፣ የክትትልና የድጋፍ ሥራዎች አፈጻጸም ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻሻል ዘርፉ ምርታማነቱን እያረጋገጠ መምጣት ችሏል።

በየደረጃው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት በመፍታትና የዘርፉ ባለሀብቶች በችግሮቹ አፈታት ሙሉ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ዕድል በማመቻቸት ዘርፉን በላቀ ደረጃ ውጤታማ ለማድረግ ያላሳለሰ ጥረት እየተደረገ  ይገኛል።

መንግሥት እስካሁን በዘርፉ ያለውን እንቅስቃሴ በመገምገም በቀጣይ የበለጠ ምርታማ ለማድረግ በምን መልክ መሰራት እንዳለበት ለይቷል።

በዚህ መሠረት የመጀመሪያው ዐቢይ ጉዳይ ለፋብሪካዎች የሚያስፈልጉ የማሽነሪዎች የተለያዩ ክፍሎች በአገር ውስጥ ለማምረት ባለፉት ሁለት ዓመታት አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል።

አገሪቱ በማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ልማት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ዘርፍ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ወጪዋን መቀነስ የሚያስችል አሠራር እየተከተለች ትገኛለች።

በመሆኑም ከውጭ አገር የሚገዙ ማንኛውም ቁሳቁስ የማምረት አቅጣጫ በመከተል ለማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያስፈልጉትን ጥሬ እቃዎች አገር በቀል የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ዘርፋን በቀጣይ ማሻሻል ትኩረት ማግኘት ያለበት ሌላው ዐቢይ ጉዳይ ደግሞ ክትትልና ቁጥጥር ነው። አገራችን ሁለት ዓይነት ባለሀብቶች ያሉባት አገር እንደሆነች በተለያየ አጋጣሚ ተገልጿል።

ቀደም ሲል የነበረው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለው ችግር እንደነበረው አያጠራጥርም። 

በአንድ በኩል በአገሪቱ ልማት ላይ እሴት የሚጨምሩ የኢንዱስትሪ ልማት አውታሮችን የሚያስፋፋና ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድልን የሚፈጥሩ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ልማታዊ ባለሀብቶች አሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ኪራይን በመሰበሰብና በአቋራጭ ሀብትን በማካበት ተግባር ላይ የተሰማሩ ኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶች አሉ።

ይህ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ብቻ ሳይሆን የውጭ አገር ባለሀብቶችንም ይመለከታል። ከተለያዩ አገራት በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያችንን አፍስሰን እንጠቀማለን፤ አገሪቱንም ተጠቃሚ እናደርጋለን በሚል ልባስ የሚመጡና ከመጡ በኋላ ግን በኪራይ ሰብሳቢነት የሚሰማሩ ባለሀብቶች አይታጡም፤ በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችም ከዚህ የፀዱ እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል።

ኪራይ ሰብሳቢነትን በአጭር፣ በመካከለኛ በረዥም የማኑፋክቸሪንግ እቅዶቻችን መሳካት ላይ እንቅፋት እንዳይሆን በተገቢው መንገድ በመለየትና በኢንቨስተር ስም አየር በአየር ለመክበር

የሚመጡ ባለሀብት ነን ባዮችን ከልማታዊ ባለሀብት በማጥራት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ያሻል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ልማታዊ ባለሀብቶች በሥልጠናና በመሳሰሉት በማገዝና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በዘርፉ በሰፊው እንዲሳተፉ ለማድረግ እየተሰራበት ያለውን አቅጣጫ አጠናክሮ መቀጠል የግድ ይላል።

አገሪቱ የምትከተለው የውጪ ንግድ ስትራቴጂ ኤክስፖርት መር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ስትራቴጂ በአንድ በኩል ከተለያዩ የውጭ አገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየገዛች የምታስገባቸውን የተለያዩ ምርቶች  በአገር ውስጥ ምርቶች የመተካት አቅጣጫ መከተል ነው።

በዚህ መልክ በማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ልማት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ዘርፍ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ወጪዋን መቀነስ የሚያስችላትን አሠራር ማስፋት ነው።

በመሆኑም ከውጭ አገር የሚገዙ ማንኛውም ቁሳቁሶችን የማምረት አቅሟን በማሳደግ ለማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያስፈልጉትን ጥሬ ዕቃዎች አገር በቀል የማድረግ ሥራ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ለውጭ ገበያ ሊቀርቡ የሚችሉ የተለያዩ ምርቶችን የማምረት  ተግባር ነው። በአገሪቱ ያለውን የግብርና  ልማት ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር በማቀናጀትና እርስ በርሱ ተመጋጋቢ እንዲሆን በማድረግ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማቱን በማጠናከር ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርትን  ደረጃውንና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ማሳደግ ነው። በዚህ መልክ ወደ ውጭ የሚላከውን የምርት መጠን በማስፋትና በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ማሳደግ ነው።

በዚህ ሁኔታ እስካሁን ድረስ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። በመሆኑም ለዘርፍ ቀጣይ እድገትና መሻሻል ትኩረት ማግኘት የሚገባውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል። አገሪቱ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሏት ይታወቃል። ይህንን ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ መጠቀም የሚችሉ ባለሀብቶችን ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገራት መሳብ የግድ ይላል።

በተለይ ከተለያዩ የውጭ አገራት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በዘርፉ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶችን ቁጥር ለማሳደግ ለመስራት የተቀየሱ አቅጣጫዎችን በአግባቡ መፈፀም ያሻል።

በዚህ ረገድ የተጀመረውን እንቅስቃሴ መንግሥት አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል። በተለይ የአገሪቱን መልካም ገጽታ በማስተዋወቅ በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናከሮ ሊቀጥል ይገባል። 

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ በተለያዩ የውጭ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንጺላዎች  በሚኖሩባቸው አገራት የሚገኙ ባለሀብቶችን በመሳብ ረገድ እስካሁን ድረስ እያደረጉ ያለውን የፕሮሞሽን ሥራ የበለጠ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል።

እስካሁን ድረስ ባለው ተሞክሮ አምባሣደሮቹ በሚሰሩባቸው አገራት የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያሳዩ ሲምፖዚየሞችን፣ ኮንፈረንሶችን፣ የንግድ ትርኢቶችን ማዘጋጀት አንዱ ተግባር ነበር።

በዚህ መልክ በርካታ የውጭ አገር ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ሥራ ላይ ያዋሉበትና ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል የፈጠሩበት ሁኔታ አለ።

ከዚህ ጎን ለጎን የተለያዩ አገራት ባለሀብቶች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ነው። ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በርካታ የውጭ ባለ ሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በአገረቱ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲያዩ በመደረጉ ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እያደገ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በዚህ መልክ በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ባለሀብቶችን ወደ ኢትዮጵያ መሳብ ቢቻልም ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል የግድ ይላል። በዚህ መልክ ከውጭ አገራት ወደ

ኢትዮጵያ  የሚመጡ ባለሀብቶችን ቁጥር በማሳደግ በዘርፉ የሚኖረውን ምርታማነት በከፍተኛ መጠን ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡

የውጭ ባለሀብቶችን ከመሳብ ጎን ለጎን የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ለማድረግ እስካሁን ድረስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አጠናክሮ በመቀጠልና ይሰጡ የነበሩ ድጋፎችን በማስፋት ቁጥራቸውን ማሳደግ እንደ አንድ አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራበት ነው።

ይህንን የበለጠ በማጠናከር የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ በማመቻቸት የዘርፉን ምርታማነት ማሳድ ያስችላል።

በተለይ ደግሞ የአገሪቱ ባለሀብቶች ያለባቸውን የቴክኖሎጂና የእውቀት ክፍተት ለመሙላት በሚያስችል መልኩ በመንቀሳቀስ በዘላቂነት የአገሪቱን የማኑፋክቸሪንገ ዘርፍ ልማት በመሪነት እንዲይዙት ለማድረግ ያስችላል።

በአገሪቱ የተጀመሩትን የኢንዱስትሪ ዞኖችን በማጠናከር የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን የበለጠ ማሳደግ የሚቻልበትን አቅጣጫ ይዞ ይገኛል። ከአሁን ቀደም የተጀመሩትን ዞኖች በማጠናከርና ሌሎች አዳዲስ የኢንዱስትሪ ዞኖችን በማዘጋጀት ዘርፉን ማጠናከር የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

ዘርፉን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል በግብዓትና ምርት ትስስርና በገበያ ፍለጋ፣ በሎጂስቲክ አቅርቦትና በፋይናንስና ብድር አቅርቦት፣ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተደረገለት ይገኛል፡፡

እነዚህንና ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎችን በማድረግ ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግና በቀጣይ ሦስት ዓመታት የኢንዱስትሪው ዘርፍ የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መሠረት ለመሆን የሚያስችለውን መሠረት እንዲይዝ ማድረግ የግድ ይላል፡፡

እስካሁን በዘርፉ ያለውን ተሞክሮ በማስፋት ቀልጣፋ አገልግሎትን እውን በማድረግ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ዳር ለማድረስ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብት  ትርጉም ያለው ድጋፍ ማድረግ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ማድረስ ይቻላል፡፡

ለኢንዱስትሪ ልማት ምሰሶ የማኑፋክቸሪን ኢንዱስትሪው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አነስተኛ፣ መካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች በሚስፋፉበት ወቅት አጠቃላይ የአገሪቱ እድገት ይፋጠናል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ በአንድ ወገን አገሪቱ የምትፈልጋቸውን ምርቶች በማምረትና በማቅረብ በሌላ በኩል ደግሞ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል የሚኖረው ፋይዳ በእጅጉ የጎላ ነው፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት ሥራ እያጠናከሩ ጎን ለጎን ደግሞ በኢንዱስትሪዎቹ ሊደርስ የሚችለውን  የዓለም ዓቀፍ  ጫና መገንዘብ ሌላው አስፈላጊ ነገር መሆኑን በርካቶች ይስማማሉ፡፡

ሁሉም አገራት የምርት ጥራታቸውን በማሻሻል በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ይጥራሉ። በዚህ የዓለም ምርቶች ቀርበው በሚወዳደሩበት ገበያ ገብቶ ተፈላጊ ሆኖ መገኘት  ራሱን የቻለ  ከፍተኛ ጥረት የሚያስፈልገው ነው።

የአገሪቱ የማኑፋክቸሪንግ ምርት ጥራትና ደረጃ ይህንን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ነው መስፋፋትና ማደግ ያለበት።

ከዓለም ዙሪያ ተመርተው ለገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች ጋር ተወዳድሮ ማለፍ የሚችልበት ሁኔታ መፍጠር ስንችል የአገራችን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት አስተማማኝ መሠረት  ላይ መገንባቱን መገመት ይቻላል።

በአንድ በኩል ለውጭ ገበያ የሚመረተው ምርት የጥራት ደረጃው የጠበቀና ተወዳዳሪ እንዲሆን በማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚሆን የማኑፋክቸሪንግ ምርትን በማስፋት አገሪቱ ከዚህ ዘርፍ ማግኘት የሚኖርባትን ጥቅም ማግኘት እንድትችል ለማድረግ የተጀመረውን የተጠናከረ ዘመቻ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል።

በዘርፉ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች፣ መንግሥትና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ዘርፍ ማደግ የሚያደርጉት ጥረት በማቀናጀት ዳር ለማድረስ የሚደረገው ጥረት  አልጋ በአልጋ ባይሆንም በመንግሥት፣ በባለሀብቶችና በሕዝብ የተቀነጀ ጥረት እውን ይሆናል።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ለአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ልማቱ መሠረት ነው። የዚህ ዘርፍ መስፋፋትና ውጤታማ መሆን አገሪቱ የምጣኔ ሀብት መሠረትዋን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለመቀየር የሚያስችል መሠረት ለመጣል ወሣኝ ነው። በመሆኑም ይህንን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ርብርብ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል።