በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት በኢትዮጵያ!

  • PDF

ሲኢድ መሐመድ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጡ የልማት ተቋማትና የኢንቨስትመንት ዘርፎች በርካታ ናቸው። መንግሥት አገሪቱን ለዘመናት ተቆራኝቷት ከነበረ ድህነት ለማላቀቅና በእድገት ጎዳና ለማስኬድ በሚያደርገው ጥረት የአገሪቱን ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲቻል የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ እቅድ በመንደፍ እየሰራ ይገኛል።

በተለይ የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በሚደረገው ትግል መሠረት ይጥላል ተብሎ ይገመታል።

በዚህ እቅድ ከሰፈሩት አዳዲስ የኢንቨስትመንትና የልማት  ፕሮግራሞች መካከል የሆርቲካልቸር ኢንዱስትሪ ይገኝበታል።

ኢንዱስትሪው ምንም እንኳን እንደ ኬኒያ በመሳሰሉ ጎረቤት አገራት የረዥም ጊዜ ተሞክሮ ቢኖርም በአገራችን ግን ተመሣሣይ የአየር ጠባይና ሰፊ የእርሻ መሬት እያለ በዘርፉ  የሚገኘውን ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልነበረም። ዘርፉ የተጠናከረ ሥራ የጀመረው ከጥቂት  ዓመታት በፊት ነበር።

በአገራችን እየተስፋፋ ከመጣው የኢንቨስትመን ዘርፍ አንዱ የሆነው የሆርቲካልቸር ልማት በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በቦሌ አየር መንገድ ምክንያት ለውጭ ገበያ የሚጓጓዙ የሆርቲካልቸር ልማት ስብስብ በአራቱም አቅጣጫዎች እየተስፋፋ ይገኛል።

የአዲስ አበባ አየር ማረፊያን መሠረት አድርጎ እየተስፋፋ የመጣው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ  ምርት ልማት በመቀሌና ባህር ዳር የአውሮፕላን ማረፊያዎች ዙሪያም ለማስፋፋት ሥራዎች መጀመራቸውና እየተጠናከረ እንደሚሄድ መረጃዎች ያሳያሉ።

በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ እንደተመለከተው በአዲስ አበባ አካባቢ ላለው ቅድሚያ በመስጠት ለልማት ዝግጁ የሆነ መሬት ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ አስፈላጊ  በመሆኑ ይህንን ለመፈጸም እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።

ይህንን ከማስፋፋት ጎን ለጎን በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመሳብ የሆርቲካልቸር ልማቱን የበለጠ በማስፋፋት አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። 

የአባባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት ከማስፋፋቱ ጎን ለጎን  ጥራቱን ለመጠበቅ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሆነ ይታወቃል። በርካታ አገራት ለከፍተኛ ውድቀትና የምጣኔ ሀብት ዝቅጠት የሚዳረጉት በምርት ጥራት አለመኖር  ምክንያት ነው። የምርት ጥራትን መሠረት ያደረገ የገበያ ትስስር ካልተፈጠረ በስተቀር ውጤታ መሆን አይቻልም።

በዓለም ገበያ ተወዳድሮ ተመራጭ ለመሆን የምርትን ጥራት መጠበቅ አማራጭ የለውም። በጥራት መደራደር አይቻልም።

የደንበኞችን ቀልብ ስቦ ለረዥም ጊዜ በደንበኛነት ማቆየት የሚቻለው በጥራት ከሆነ ብቻ ነው። ለዚህም ነው ከምርቱ እያደገ መምጣት ጋር ተያይዞ ጥራቱም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሊሟላ ይገባል።

ከስድስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የሆርቲካልቸር ልማት በፍጥነት እያደገ መምጣቱን ከሆርቲካልቸር ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያሳያል። ባለፉት ሁለት

የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የመጀመሪያ ዓመታት በዘርፉ የነበረውን አፈጻጸም ማየት ይቻላል። አፈጻጸሙ በተያዘው እቅድ እንደነበርም መረጃው ያሳያል።

ሦስተኛ ዓመት ከአበባ፣ አትክልትና ፍሬፍሬ ልማት ዘርፍ ከ569 ሚሊዬን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዷል።

በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ሦስተኛ ዓመት ከአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት የሚገኘውን ገቢ ወደ 569 ሚሊዬን ዶላር ለማድረስ አምስት የልማት ማዕከል ኮሪደሮችን በመምረጥ ወደ ሥራ ተገብቷል። 

በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ተጨማሪ ከ30 ሺህ እስከ 40 ሺህ የሚደርስ መሬትን በሆልቲካልቸር ለማልማት ታቅዷል። ልማቱን ከአርሶ አደሮች ጋር በትብብርና በመሬት ባንክ ባለ መሬት እንደሚለማ ለማወቅ ተችሏል።

በሆልቲካልቸር ልማት ዘርፍ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በሰፊው እንዲሳተፉ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረገ ነው። በተለይ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ በተለያዩ አገራት ያሉ የኢትዮጵያ አምባሣደሮች ያላሳለሰ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

የውጭ አገር ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጭተው መዋእለ ንዋያቸውን ሥራ ላይ እንዲያውሉ የአገሪቱን የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የውጭ አገር ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ምርቶችም በተለያዩ የውጭ አገራት ገበያ እንዲያገኙ በማድረጉ ረገድም ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።


የዘርፉን ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚኖራቸው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ ይህንኑ ለማስፋፋት እየተሰራ ይገኛል።

በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሆርልቲካልቸር ልማት ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ሲጀመር 1100 ሄክታር መሬት ብቻ ነበር የለማው። የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለሥላሴ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት 11 ሺህ 110 ሄክታር መሬት ለዚሁ ልማት ውሏል። 

ይህ ዘርፍ የአገሪቱን ገቢ በማሳደግ ረገድ የሚያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በአገሪቱ እየተስፋፉ ከሚገኙ የአበባ ልማት ዘርፉ 100 ሚሊዬን ዶላር ተገኝቷል። 

በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ልማቱ በተቀናጀ መልኩ ከመጀመሩ በፊት  የነበረው ሁኔታ ሲታይ ዝቅተኛ ነበር።  ከዚሁ ምርት 17 ሚሊዬን ዶላር ብቻ ይገኝ እንደነበርም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ከአበባው ዘርፍ የሚገኘው ገቢ በእጥፍ በማደጉ 200 ሚሊዬን ዶላር ደርሷል። ይህ ገቢ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ የሚኖረው ሚና ቀላል እንዳልሆነ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፉ በኩልም ወደ 60 ሚሊዬን ዶላር ከፍ ብሏል ብለዋል።

በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን  መጨረሻ 11 ሺህ ሄክታር ላይ ያለውን የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻ ልማት ወደ 30 ሺህ ሄክታር ለማድረስ መታቀዱንም መረጃው ያሳያል። 1 ሺህ 500  ሄክታር ያለውን የአበባ እርሻም ወደ ሦስት ሺህ ሄክታር ከፍ በማድረግ አጠቃላይ ገቢውን ወደ 1 ነጥብ 48 ቢሊዬን ዶላር ለማሳደግ መታቀዱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታትም ከሆርቲካልቸር ልማት 490 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። በአበባ፤ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ከአምስት አመት በፊት ለ10 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሮ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ አምስት መቶ ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። 

በአገራችን  የአበባ ልማት የተጀመረው በቅርብ ጊዜ ቢሆንም  እያስመዘገበ ያለው ፈጣን እድገት ግን ቀደም ብለው ከተጀመሩ ዘርፎች ባልተናነሰ መልክ እያደገ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። 

በተለይ ደግሞ በአፍሪካ አህጉር ይህንን የልማት ዘርፍ ቀደም ብለው ከጀመሩ አገራት ጋር  ሲነጻጸር  የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት ይቻላል።

ለአብነት ያህል የኬኒያን ተሞክሮ ብናይ  የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት ከሻይ ቅጣልና ከቱሪዝም ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝላት የልማት ዘርፍ እንደሆነም ይታወቃል።

የአገሪቱ የሆርቲካልቸር ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ 31 በመቶ እያደገ መጥቷል። 130 ሺህ ቶን በየዓመቱ በማምረት  ለተለያዩ የአውሮፓ አገራተ ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ ምርቷን መላክ የጀመረች ሲሆን ኒዘርላንድ 71 በመቶ እንግሊዝ ደግሞ 20 በመቶ የሚሆነውን ምርቷን ይረከቧታል።

ኬኒያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የአበባ ምርት በየዓመቱ 3 ነጥብ 6 እንደሚያድግ መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህ የኬኒያ የረዥም ጊዜ ተሞክሮ በቅርብ ጊዜ በአገራችን ከተጀመረው ጋር ሲነጻጸር አገራችን ከጥቂት ዓመታት በኋላ የሆርቲካልቸር ምርቷን በማሳደግና ጥራቱን በመጠበቅ በውጭ ገበያ ከፍተኛ ተፎካካሪ መሆን እንደምትችል መገመት አያዳግትም።

በአፍሪካ የሆርቲካልቸር ልማት ተስፋፍቶባታል የምትባለው ሌላ አገር ኡጋንዳ ነች። በኡጋንዳ  20 የሚሆኑ የአበባ እርሻዎች ይገኛሉ። እነዚህ የአበባ እርሻዎች 200 ሄክታር መሬትን ይሸፍናል።

ኡጋንዳ በዓመት 6003 ሜትሪክ ቶን አበባን ለውጭ ገበያ ታቀርባለች። በዚህ ዘርፍ የተፈጠረው የሥራ ዕድል  6000 ያህል መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።   አገሪቱ  ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ዘርፉን ለማስፋፋት በነደፈችው እቅድ መሠረት ተጨማሪ 300 ሄክታር መሬት በማልማት ላይ ትገኛለች። 

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራትም ሆነ ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳዳሪ የሆነ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬን በማምረት በዓለም ገበያ ቀዳሚውን ሥፍራ ለመያዝ በሚያስችላት መንገድ መጓዝ ይኖርባታል። የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የመጨረሻ ሦስት ዓመታት ሲጠናቀቁ በዘርፉ ያለው ምርት በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል ተብሎ ይገመታል። በዚህ ዘመን ከ 30 እስከ 40 ሺህ ሄክታር መሬት በሆርቲካልቸር ይለማል።    

በየዓመቱ ለውጥና እድገት እያስመዘገበ የመጣው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት በተጠናከረ መልክ የተጀመረው ከአምስት ዓመት በፊት ነበር። በ2000 ዓ.ም የነበረው አፈጻጸም ከ2004 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር የእድገቱ መጠን ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

የአበባ ልማት ዘርፍ ከአምስት ዓመታት በፊት ያስገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ  በእጥፍ አድጎ 220 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል። በአትክልትና ፍራፍሬ ረገድም በተመሳሳይ ጊዜ ከ17 ሚሊዮን ወደ 60 ሚሊዮን ዶላር ማደግ ችሏል። 

እንደ ኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለሥላሴ ተክኤ ገለጻ ዘርፉ የሥራ አጥነት ችግርን በመቅረፍ በኩልም ቀላል የማይባል

አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። ከአምስት ዓመት በፊት ከ10 ሺህ የማይበልጥ የሥራ እድል ፈጥሮ የነበረ መሆኑን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠሩ ከ80 በመቶ በላይ እድገት ማሳየቱን መገንዘብ ይቻላል። 

የሆርቲካልቸር ልማት በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንደተቀመጠው በእቅዱ ዘመን ማጠቃለያ  1 ነጥብ 48 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማስገኘት ነው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት 490 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማድረግ ተችሏል። ይህ አፈጻጸም የእቅዱን 75 በመቶ እንደሚሸፍን ለማወቅ አያዳግትም።  በያዝነው የበጀት ዓመት ደግሞ  ገቢውን ወደ 569 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማድረስ እየተሰራ ነው።

የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን በተገቢው መልክ እንደሚፈጸምም እምነት ተይዟል። 

በአገሪቱ አምስት የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ማዕከላት አሉ። እነዚህን ማዕከላት በማጠናከርና የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሃብቶችን በዘርፉ እንዲሰማሩ በማድረግ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም በተገቢው መንገድ ማግኘት ትችል ዘንድ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ነው።

አንደኛ የሆርቲካልቸር ልማት ማዕከል ተብሎ የሚጠራው የአዲስ አበባና የኦቶሚያ ዙሪያ የልማት ኮሊደር ነው። ይህ ኮሊደር ከአዲስ አበባ በአራቱም አቅጣጫዎች እሰከ 180 ኪሎ ሜትር የሚያካለል ነው።

ይህ የልማት ማዕከል የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያን መሠረት አድርጎ የሚለማ ልማት ነው። በባህር ለሚጓጓዘው ደግሞ ዝዋይን እንደማዕከል ይጠቀማል።

በዚህ የልማት ማዕከል የሚለማ 10 ሺህ ሄክታር መሬት በባንክ የተያዘ ነው። ከአርሶ አደሩ ጋር በማቀናጀት የሚሰራ ደግሞ ሌላ 40 ሺህ ሄክታር መሬት በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። 

ሁለተኛው የልማት ማዕከል ደግሞ የሃዋሳና አርባ ምንጭ አካባቢ የልማት ማዕከል ነው። በዚህ የልማት ማዕከል ከአራት ሺህ ሄክታር በላይ በመሬት ባንክ የተቀመጠ ነው። ከአርሶ አደሮች ጋር በመተባበር ለመስራት የታቀደው ደግሞ ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ

የአዋሽ፣ ድሬዳዋ፣ ሀረርና ሶማሌ  የልማት ማዕከል ደግሞ የድሬዳዋ ኢንተርናሽናል የአየር ማረፊያን ማዕከል አድርጎ የሚለማው ሦስተኛው የሆርቲካልቸር የልማት ማዕከል ነው። 20 ሺህ ሄክታር መሬት በባንክ የተዘጋጀ ሲሆን ሌላ 30 ሺህ ሄክታር ደግሞ ከአርሶ አደሩ ጋር በማስተሳሰር የሚለማ መሆኑን መረጃው ያሳያል።

ሌላው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ማዕከል ደግሞ የባህርዳርና የአባይ ተፋሰስ ማዕከል በመባል የሚታወቀው አራተኛው የልማት ማዕከል ነው። ይህ የልማት ማዕከል በባህዳር አካባቢ ያሉ የሆርቲካልቸር ልማቶችንና በአባይ ተፋሰስ የሚኖሩትን ያጠቃልላል።

ይህ የልማት ማዕከልም መሠረት ያደረገው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ እንደሆነ መረጃው ያሳያል።  ለዚህ አካባቢ ልማት 10 ሺህ ሄክታር መሬት በባንክ የተያዘ ሲሆን ሌላ 50  ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ ከአርሶ አደሩ ጋር በትስስር የሚሰራ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። 


አምስተኛው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ደግሞ የመቀሌ፣ ራያና አላማጣ የልማት ማዕከል በሚል ይታወቃል። ይህ የልማት ማዕከል የመቀሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያን መሠረት አድርጎ እየለማ ያለ መሆኑን መረጃው ያሳያል።

በዚህ የልማት ማዕከል ለልማት የሚውል 10 ሺህ ሄክታር መሬት በባንክ ተይዟል። ሌላ 40 ሺህ የሚሆነው ደግሞ ከአርሶ አደሮች ጋር በትስስር የሚለማ ይሆናል።

በአምስቱም የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የልማት ማዕከላት ከአርሶ አደሮች ጋር በትስስር የሚለሙ እርሻዎች አርሶ አደሩን በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ይሆናሉ።

በሁሉም ማዕከላት ከ180 ሺህ ሄክታር በላይ የሆርቲካልቸር ልማት የሚለማው በአርሶ አደሩ የእርሻ ማሳ ላይ ይሆናል። በዚህ መልክ አርሶ አደሩ የምግብ ሰብሎችን ከማምረትና እንስሳትን ከማርባት ጎን ለጎን ጥሩ ገቢ የሚያስገኙ ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚነቱን እያሳደገ ይሄዳል። 

በዚህ መልክ በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መጨረሻ ተጨማሪ ከ30 እስከ 40 ሺህ ሄክታር መሬትን ለማልማት የታቀደው።  ይህንን ልማት ተግባራዊ ለማድረግ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሃብቶች እንዲሰማሩ ይደረጋል።

ቀደም ሲል እንደነበረው ለመጣው ሁሉ መሬትን መስጠት ብቻ ሳይሆን በትክክል አቅም ላላቸውና የገበያ ትስስር ሊፈጥሩና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለአርሶ አደሩ ሊያወርሱ ለሚችሉ በቂ ሃብትና ሪሶርስ ያላቸው ባለሃብቶች በልማቱ እንዲሳተፉ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረገ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። 

በተለይ ባለሃብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ እንዲቻል በአንድ ማዕከል ብቻ እንዲስተናገዱ የማድረጉ ሥራ እየተከናወነ ነው። የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ ይህንን ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛል። ከኤጀንሲው  የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው የአገራችን ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በቅንጅት እንዲሰሩና ከውጮቹ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ  ነው።

በአንድ በኩል አርሶ አደሩ በሆርቲካልቸር ልማት በሰፊው ተሰማርቶ የገቢውን አማራጭ እንዲያሰፋ ሰፊ ተሞክሮ እንዲወስድና ከባለሃብቶች ጋር እየተቀናጀ እያመረተ ተጠቃሚነቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ እንዲሄድ ማድረግ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን በዘርፉ የሚሰማሩ ልማታዊ ባለሃብቶች ከተለያየ የዓለማችን አህጉሮችና አገራት የሚመጡ በዘርፉ ብዙ ልምድ ያካባቱ ባለሃብቶች ጋር በቅንጅት በመስራት ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ማሳደግ እንዲችሉና አገሪቱም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም በላቀ ደረጃ ማግኘት እንድትችል ለማገዝ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። 

አገሪቱ የተቀናጀ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማትን ተግባራዊ በማድረግ  ለዚሁ ምርት በቂ ገበያ  በማፈላለግ ውጤታማ ስራን ለመስራት የገበያ ጥናቶችን በማካሄድ ወሣኝ መዳረሻ የተባሉት ተለይተዋል። 

ከእነዚህ የገበያ መዳረሻዎች አንዱ የራሺያ ፌዴሬሽን የገበያ መዳረሻ  ነው። በዚህ የገበያ መዳረሻ መስኮ፣ ሴንቲፒተርስ በልድና ሳይቤሪያ ይገኙበታል። በእነዚህ አካባቢዎች 145 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይኖራል።

የሕዝቡ የመግዛት አቅምም አስተማማኝ ነው። ለዚህ የገበያ መዳረሻ የአበባ፣ ምርት ብቻ ሳይሆን አትክልትና ፍራፍሬዎችንም የማቅረብ አቅጣጫ ተይዟል። 

ሁለተኛው የገበያ መዳረሻ ማዕከል ተደርጎ የተለየው አሜሪካ ነው። በተለይ ምሥራቅ ኮሪደር በሚባሉት አካባቢዎች የአገራችን የሆርቲካልቸር ምርት ተፈላጊነት እያደገ መጥቷል።

በዚህ የገበያ መዳረሻ የሚያስፈልገውን የሆርቲካልቸር መጠንና ጥራት በመለየትና አመራረታችንን በደንበኞቻችን መሠረት በማስተካከል የአገራችንን ምርት በአሜሪካን አገር ሕዝብ ተፈላጊ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ነው ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ የሚያሳየው። 

ሌላው ትልቅ  የሆርቲካልቸር ምርቶቻችን መዳረሻ  ሆኖ የተለየውና ቀደም ብሎም ሲሰራበት የነበረው የገበያ ማዕከል የጃፓን ገበያ ነው። የጃፓን ሕዝብ ለአበባ ልዩ ፍቅር እንዳለው ይታወቃል።

በዚህ ረገድ ያለው ባህል ጠንካራ በመሆኑ ይህንን ህዝብ የአበባ ምርታችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል መሰረት አለ።

ቀደም ሲል በትንሹ ሲላክ የነበረው ምርት የፈላጊው ቁጥር እያደገ በመምጣቱ ከአገራችን የሚላከው የሆርቲካልቸር ምርት መጠንም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ሕዝቡ አትክልትና ፍራፍሬ የመጠቀም ባህሉ ጠንካራ በመሆኑ ከአበባው ጎን ለጎን አትክልትና ፍራፍሬ በመላክ ላይ ነው። በዚህ መልክ በአሁኑ ወቅት በዓመት እስከ 20 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚሆን ገቢ ከዚሁ አገር ይገኛል።

እነዚህ የገበያ መዳረሻ ማዕከላት ሕዝቦች ቀደም ሲልም የኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ምርቶች ይደርሷቸው እንደነበር አንዳንድ መረጃዎች ያሳያሉ።

ምርቶቹ የሚደርሷቸው ከኒዘርላንድ ስለነበር ምርቶቹ የኢትዮጵያ ብራንድ ባለመያዛቸው ከኢትዮጵያ ለመሆናቸው ተጠቃሚዎች የሚያውቁት ነገር አልነበረም። 

ይህንን የመስበርና የኢትዮጵያ ምርቶች በአገሪቱ ብራንድ በተለያዩ የገበያ መዳረሻዎች እንዲታወቁ የማድረግ ሥራም ጎን ለጎን እየተሰራ ይገኛል። አገሪቱ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የአምስት ዓመቱን የእድገትና ትራንስፎርማኝን እቅድ  በስኬት ለማጠናቀቅ ለምታደርገው ሁለንተናዊ ጥረት የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬም ድርሻው የጎላ ይሆናል። 

የአበባ ልማት አዲስ የመሆኑና በአካባቢው ዓለም አቀፍ መጓጓዣ የሚያስፈልግ በመሆኑ ከአትክልትና ፍራፍሬ ጋር በንጽጽር ሲታይ እድገቱ በዝግታ እንደሚሆን እሙን ነው።

አትክልትና ፍራፍሬ ግን አንድም ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በተጨማሪም ለአገር ውስጥ ፍጆታ ለማዋል ስለሚቻል እድገቱ በጣም ከፍተኛ እንደሚሆን ይገመታል። በዚህ መልክ አገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማግኘት ትችላለች የሚል እምነት ተጥሏል።