በምሥራቃዊ ኮንጐ ውጊያ ተቀሰቀሰ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2005 (ዋኢማ) - በኮንጐ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊከ ምሥራቃዊ ክፍል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል (ማኑክ) በሚደገፈው የመንግሥቱ ጦር ኃይልና «ኤም-23» በሚል ስም በሚታወቀው የአፈንጋጭ ወታደሮች (አማፅያን) ቡድን መካከል ውጊያ መቀስቀሱን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ።

ውጊያው በመካሔድ ላይ የሚገኘው ጐማ ከተባለች የአካባቢው ዋና ከተማ በስተሰሜን በቅርብ ርቀት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።

ኤም-23 በሚል ስም የሚታወቀውና ከመንግሥቱ ጦር ሠራዊት አፈንግጠው በወጡ ወታደሮች የተደራጀው የአማፅያን ቡድን በአካባቢው ሁከት መፍጠር የጀመረው ካለፈው ሚያዝያ አንስቶ ሲሆን፤ በተፈጠረው ሁከት ምክንያት 500,000 ሕዝብ መፈናቀሉን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዑጋንዳና ርዋንዳ ለእዚህ አፈንጋጭ የአማፅያን ቡድን ድጋፍ እንደሚሰጡ በማመልከት ነቀፋ መሰንዘሩም በበቢሲ ዘገባ ተመልክቷል።

ርዋንዳና ዑጋንዳ ግን የተመድን ውንጀላ ማስተባበላቸው ተገልጿል።

ሰሞኑን እንደገና የተቀሰቀሰው ውጊያ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር የኮንጐ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መንግሥት በጦር ሄሊኮፕተሮችና በከባድ መሣሪያዎች የታገዘ ተጨማሪ ኃይል ወደ አካባቢ መላክ የጀመረ ሲሆን፤ ማኑክም በአካባቢው የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ማጠናከሩ ተገልጿል።

የኮንጐ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ ጐማ ከተማ ውስጥ በሰጠው መግለጫ ሰሞኑን በተቀሰቀሰው ውጊያ ሂደት 44 የአፈንጋጭ ቡድኑ አባላት መገደላቸውን አመልክቷል።
እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ የማኑክ ቃል አቀባይ እንዳመለከተው ደግሞ የመንግሥቱ ጦር ማቤንጋ የተባለችውን ከተማ ከተቆጣጠረ በኋላ የአማፅያን ቡድኑ ማዕከል የሆነችውን ኪዋንዳ የተባለች ከተማ ለመያዝ ተንቀሳቅሷል።