አገርንና ሕዝብን ለማሳደግ

  • PDF

አዲሱ ለማ
ለአንድ አገር የትልቅ ብልፅግና መሠረቱና ሚስጥሩ ልማትና ምርታማነት ነው፡፡ በጊዜው ጥቂትም ብትሆን ምርታቸውን የሰበሰቡና ያከበሩ ጐች ያሏቸው አገሮች ዛሬ ላይ አንቱታን በማግኘት ከበሬታን ተችረዋል፡፡ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ምርት የላትም ማለት አልነበረም፡፡

አሁን አገራችን የደረሰችበና እየሰራች ያለው ሥራ ቀደም ባሉት ጊዜያት ተከናውኖ ቢሆን ኖሮ አገራችን ዛሬ ላይ የት በደረሰች ነበር፡፡ አሁን ሁሉም ዜጋ ይህንን ቁጭት ወኔና እልህ ሰንቆ የልማት መሣሪያውንና የልማት ኃይሉን ወደ ልማቱ ዓውደ ግንባር ከመለሰ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ወትሮም ቢሆን ብልህ አስተዋይና ሩቅ አሣቢ መሪ ካገኘ ለዓይን የሚከብደውን ተራራ ሜዳ ማድረግ መቻል የሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ በብልሁ፣ በቆራጡና በባለራዕይ መሪው አቶ መለስ ዜናዊ ራዕይ ሰናቂነት የተጀመረው የልማትና የምርታማነት ጉዞ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ውጤትና ለውጥ ማምጣቱን አይተናል፡፡

የባለራዕዩ መሪ ታዲያ የሰሩት ምርቱንና ልማቱን አሊያም ፍሬና ውጤቱን በመቁጠር መኩራራት ብቻ ሳይሆን ለልማቱም ይሁን ለምርታማነቱ መሠረት የሆነውን አልሚውንና አምራቹን ታች ድረስ በመውረድ የማበረታቻ ሽልማት ብቻ ሣይሆን የአርቆ አስተዋይነት አመለካከት ለውጥ ግንዛቤን ሸለሙት፡፡

ከዚያ ወዲያ በአርሶ አደሩ አካባቢ ብቻ ሣይሆን መላው አገሪቱ ዜጐች በተሰማሩባቸው የሥራና የሙያ መስኮች ሁሉ አልሚና አምራች ሆነው ከራሳቸው በፊት ልማታቸውና ምርታቸው እንዲታይ እንዲናገርና እንዲመሰክር ያስቻለ ወኔ አስታጠቁ፡፡

የዘመቻው ማነጣጠሪያ ድህነት ብቻ መሆኑን አስገነዘቡት፡፡ ሴት ወንድ አይልም፤ ዘመቻው ጊዜ አይገድበውም፤ ሁሌ ልማት ሁሌ ምርት አረንጓዴው ሰብል በስተግራ እየለማ ፍሬ የያዘው ግራጫ ሰብል በስተቀኝ ይታጨዳል፤ ይወቃል፡፡ ይሰበሰባል፡፡ ልማትና ምርት በአንድ ዓውድ ይታያል፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ ታጥቀው ሲገሰግሱለት የነበረው ዓላማ ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገ ወዲያም ማብቂያ ቀርቶ ማረፊያ በሌለው መልኩና ተነሳሽነት ሊቀጥል የአገሪቱን ዜጐች ሁሉ ላፍታም ሌላ ጉዳይ ሌላ መነጋገሪያ አጀንዳ እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል፡፡

ዜጐች ሠላምታቸው ሥራ ማረፊያቸው ሥራ ሆኗል፡፡ በዚህ በተነሱለትና በያዙት ዓላማ ሥር ተጠልለው በልማትና በምርትማነት አጀንዳቸው ላይ ተማምለዋል፡፡ እጅ ለጅ ተያይዘው አገርን ሊያለሙና ከእጥፍም እጥፍ በላይ ለማልማትና ለማምረት ቃል ገብተዋል፡፡

ለቀጣይ ተረካቢ ትውልድ የደኸየችና ችግር ያቆራመዳትን ኢትዮጵያን ሣይሆን በሀብት የበለፀገች፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሰለጠነች፣ በሁሉም ተመራጭ የሆነች አገርን ለማውረስና ለማስተላለፍ የወሰኑና የተነሱ ዜጐችን ይዛለች፡፡

ኢትዮጵያ ልማትን እንዴትና መቼ ማልማት እንዳለባትና ምርትና ምርታማነትን ለማጐልበት እንዴት ማቀድና መሥራት እንዳለባት አውቃለች፡፡ አሁን ዜጐች ለጉልበታቸው፣ ለጊዜያቸውና ለእውቀታቸው የሚሰስቱበት ያ የአመለካከት ተሰብሯል፡፡ ጊዜው የልማትና የምርታማነት የዕድገትና የብልፅግና የሥራና የሠራተኞች ሆኗል፡፡ ብሩህ አዕምሮና ጠንካራ መንፈስ፣ ሰርቶ የማይደክም ጉልበት እየታየ ያለበት፣ የስንፍናና መሠል ማሰሪያዎች፣ የጥላቻና የሥራ አጥነት አጀንዳዎች፣ የተዘጉበት እንዲያውም ከነአካቴው የተቀበሩበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ የዜጐች አመለካከት ተቀይሯል፡፡ የማልማትና የመበልፀግ ውልን አስረዋል፤ ቃል ኪዳን ገብተዋል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በርትቶ ለሰራበት በተለይ በግብርናው መስክ በዓመት ሁለትና ከዚያም ጊዜ በላይ ለማምረት የሚያስችል ምቹ የአየር ንብረት፣ ለም አፈርና የተስተካከለ መልክዓ ምድር እንደሁም የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውኃ በተፈጥሮ የተቸረች ውብ አገር ናት፡፡

ለእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ ዘርፍ ለመስኖ እርሻ አገልግሎት የሚውሉ እንደነ አዋሽ፣ ኦሞ፣ ገናሌና አባይን የመሳሰሉ በተፈጥሮ ምርጥ አቀማመጥና ለማልማት በተመቻቹ መልክዓ ምድሮቻችን እየተዘናፈሉ ለዘመናት ያለ ጥቅም ሲፈሱ የኖሩ ፈሳሽ ወርቆቻችንን በቃችሁ እስከ ዛሬ ያለምንም የአገር ጥቅም በከንቱ ያባከናችሁት ጊዜ ቢያስቆጨንም አሁን ግን ይበቃናል፡፡ ተሰብስባችሁ የአገራችሁን ሕዝብ የአገራችሁን መሬት አስጊጡ አስውቡ ብሎ ሳይወዱ በግድ በእናታቸው እምብርት ላይ ሊያስተኛቸው ቆርጦ ለማልማትና ለማምረት ተነስቷል፡፡

በመሆኑም ከላይ ከዘረዘርናቸው በርካታ የአገራችን ወንዞች መካከል ጥቂቶቹ ቢሆኑም ሌሎቹም እንደዚሁ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ልማት እና ምርት ሥራ እጃቸውን የሰጡበት ዘመን ነው፡፡ የአዋሽ ወንዝ ለከፍተኛ የመስኖ ሥራ የሸንኮራ ልማት ጠብታ ውኃ ሳይሰስትና ሳያባክን የመተኃራንና የወንጂን የሸንኮራ ተክል አጠጥቶና መግቦ ብቻ ሣይሆን ወደ ቀድሞ መግቢያና ማረፊያው ማጀቱ የአቤ ሐይቅ መቃረቢያው ላይ በአፋር ክልል አካባቢ ግዙፍ የመስኖ አገልግሎት ለሸንኮራ ልማትና ለስኳር ምርት አገልግሎት ውሏል፡፡

ይህ እንግዲህ ቀድሞ የአዋሽ ወንዝ በቅንጫቢ ከሚያለማውና በከንቱ እየሞላ ከሚያጠፋው ሁሉ እጅንና መንገደኛ እግሩን አጥፊ የሆነውን የክረምት ትዕቢቱን ለአገሩ ልማትና ምርት ዕድገት የበኩሉን ሊሰራ ከምን ጊዜውም በበለጠና በተሻለ በላቀ መልኩ መዘጋጀቱ ሲታሰብ አገራችንን የልማትና የምርታማነት አውድማ ሊያሰኛት ተቃርቧል፡፡

ወትሮም ቢሆን ኢትዮጵያ ያላትና የተሰጣት ስሟ ብቻ አልጠቀማትም፡፡ በስሟ የሰራችበትና የሰራችው ጥቂቱም ቢሆን ጠቅሟታል፡፡ ይህም ሲባል   የውኃ ጋን አለያም የባለ ብዙ ውኃ ሀብት ባለቤት መሆኗን የተገለፀበት ጊዜና ስሟ በጊዜው ስላልሰራችበት የበርካታ ውኃዎች ሁሉ ምንጭ የሆነችዋ ኢትዮጵያ ከአናቶቿ ውኃ እያመነጨች በውኃ እየተጥለቀለችና እየታጠበች እየተጠማችና እየተራበች ያሳለፈችው ጊዜ እነ ፊንጫ ተከዜ ባሮ ዋቢ ሸበሌ ገናሌና ፈፅሞ አይደፈሬው አባይም እጅ እግራቸውን ሰብስበው አገራዊነታቸውን በአገር ልጅ ለአገር ልጅ ብለው ከፊሎቹ ለኃይል ልማትና ምርት ከፊሎቹ ለመስኖ ልማትና ምርት ሌሎች ከፊሎቹ ደግሞ ለኃይል ልማትና ምርት ከዋሉ በኋላም ለመስኖ ልማት ሊውሉ አንገታቸው አቀርቅረው አገራቸውን እና ሕዝባቸውን ታዝዘዋል፤ ተይዘዋል፡፡

ለሎቹም ደግሞ ከዚህ ባለፈ ለዓሣ ኃብት ምርት ለመዋል ተዘጋጅተዋል፡፡ ይህ ሁሉ የልማት የምርትና ምርታማነት ጉዞ የተደረሰበት እንዲያው በተዓምር አሊያም በምኞት ወይም ደግሞ በቅዥት በከንቱ የልብ ወለድ ሕልም አይደለም፡፡ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው የዕድገትና የብልፅግናን ራዕይ በሰነቁ ለዓመታት እንቅፋቶችን ለማፅዳት በበረሀ ደማቸውን ባፈሰሱና ክቡር ህይወታቸውን በገበሩ ውድ የኢትዮትጽያ ልጆች የተቀየሰ ክቡር እቅድ መሆኑን በውልና በወግ መገንዘብ ያሻል፡፡

ይህ ሁሉ የልማት እና የምርታማነት ሥራ ከዕቅድ ወደ ተግባር ተሸጋግሮ ውጤት ማምጣትና ውጤቱ በይፋ መታየት የጀመረበት ወቅት ላይ መደረሱን ራሱን ቅድሚያ ግንዛቤ መያዝ በራሱ መረጀ ነው፡፡ ዳርና ሩቅ ሆኖ ማውራት አሊያም የሆነ ያልሆነውን የሀሳብ ትረካ ማቀነባበር በጣም ቀላል ይሆናል፡፡ የአንድ ዶማ አካፋና ማረሻ እጀታ ይዞ ወገንብን አጐንብሶ ለመሥራት መትጋት ግን እጅግ ልዩ ጀግንነትን ወኔንና ተስፋን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡

እናም አገራችን በባለራዕዩ መሪዋ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሳልና አርቆ አሳቢነት በተዘረጋው እቅድ ለዚህ መብቃቷን ልብ ማለትና ማወቅ ያሻል፡፡ ልማት ልብንና ሁለንተናዊ ብቃትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ጉልበትና ገንዘብ እንኳን ቢኖር ብልሃትና ብልህነት ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ መሪዎች ብልጥ፣ ፈጣን፣ አርቆ አሣቢና አዋቂዎች መሆንን ብቻም ሣይሆን የሕዝብን ሀብትነት በውል መገንዘብና ሕዝባቸውን ለልማትና ለምርታማነት ሥራ በሞራልም በጉልበትም እንዲነቃቃ የማድረግ ተግባር ይጠበቅባቸዋል፡፡ እናም በዚህ ረገድ በተለይ ወንዞቻችንን ለኃይል ልማት ለማዋል በተደረገው ፈጣን ርብርቦሽ ባለራዕዩ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ታሪክ የማይረሳና በየትኛውም ትውልድ ቅብብሎሽ ላፍታም የማይደበዝዝ ታሪክ ጽፈው አልፈዋል፡፡ ከኋላቸውም ሚሊዮኖችን በራዕያቸው ለራዕያቸው ስኬቶች አሰልፈዋል፡፡ ለተከዜና ለግልገል ጊቤ የኃይል አቅርቦት ልማት ምን ያህል መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ምርቱ ደግሞ በየጊዜው የከተሞችን የፈረቃ የመብራት አገልግሎት ተቀጠቃሚነት በማስቀረት ታይቷል፡፡

ከሁሉም በላይ አዳዲሶቹን የወረዳና የቀበሌ ከተሞች የሀያ አራት ሰዓት የመብራት ኃይል ተጠቃሚ ማድረጉ በመስኩ የታየው የልማቱና የምርቱ ውጤት መሆኑንም መገንዘብ ጥልቅ ምርምር ማድረግ አሊያም ደግሞ ለማንም ዜጋ ነብይነት ወይም ሣይንቲስት መሆን አያስፈልገውም፡፡ በአገሩ መሪዎች ራዕይና እቅድ፣ በአገሩ ሕዝቦች የጋራ ትስስር፣ በአገሩ ምድር የተከናወኑ ሥራዎችን ያውቃልና ነው፡፡

ባለራዕዩ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ካቀዱትና ካበሰሩት ታላላቅ የልማት ሥራዎች በወቅታዊነት የሚጠቀሰው የታላቁ የህዳሴው ግድብ ወይም ደግሞ 6ዐዐዐ /  ስድስት ሺህ/ ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት የሚያመርተው ግድብ ይገኝበታል፡፡

ይህ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቅርብም በሩቅም ያለ ሁሉ አሻራውን ያሳረፈበት፣ ልዩ ታሪካዊና ታላቅ ሀብት ግንባታ እቅድ ተላሚና አብሣሪ እኚህ ታላቅ የሕዝብ ልጅና መሪ ያቀጣጠሉት የልማት ራዕይ በእያንዳንዱ ዜጋ ልቦናና ሁለንተና ሰርፆ እነሆ ትናንትና፣ ዛሬ፣ ነገ፣ ከነገ ወዲያና እስከ መጨረሻው አደራቸውን አሊያም የኑዛዜ ቃላቸውን ከግብ ለማድረስ የተነሣው ኢትዮጵያዊ በገንዘቡ፣ በጊዜው፣ በእውቀቱ፣ በጉልበቱ ለታላቁ ዘመቻ ክተት አዋጅ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተገንብቶ ሲያልቅ ምርቱ ከአገር አልፎ በአህጉሩ ለሚገኙ የጐረቤት አገራት የኃይል አቅርቦት ለመስጠት እንዲያስችል ሆኖ የተቀረጸ የልማት መሠረት ሂደት መሆኑ ሲታሰብ ሌት ከቀን ቢሰሩ ምናለበት እያሰኘ ሌላ እልህና ወኔን ያስታጥቃል፡፡

ልማትና ምርታማነት ተመጋጋቢ ናቸው ወይም ደግሞ ልማት ካለ ምርትና ምርታማነት አለ ማለት ነው፡፡ ልማት የሚገለፀው በእርሻው ወይም በግብርናው መስክ ብቻ አይደለም፡፡

የግብርናውን መስክ ነጥለን ብናይ የአገራችን አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለማሣደግ በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ተጠቃሚ ከመሆናቸውም ባሻገር ከኋላ ቀር የአስተራረስ ድካም በመላቀቅና ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴዎችን በየደረጀው ተግባራዊ በማድረግ እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡

ይህ የልማትና የምርታማነት የግብርና አሊያም የእርሻው ዘርፍ ብዙ ጥረትንና ጥንቃቄን እንዲሁም ክትትልን ይፈልጋል፡፡ ከማሣ ዝግጅት እስከ ዘር መዝራት ከአረም እስከ አጨዳና ከክምር እስከ ውቅያ ድረስ ምርትን ሰብስቦ በጐተራ  አከማችቶ እስከማስገባት ድረስ ዘላቂ ርብርቦሽን የሚጠይቅ የጠንካራና ታታሪ ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ ነው፡፡

የግብርናው ዘርፍ የበጋና የክረምት ወቅቶችን በውስጡ ስለሚያልፍ ለምሣሌ በክረምቱ ወይም በዝናብ ወቅት በአረም ምክንያት ምርት እንዳይቀንስ ክረምቱንም እየተጋፉ መስራት ግዴታ ያለበት ነው፡፡ በበጋው አለያም ፀሃይ በሚበዛበት አጋጣሚም ቢሆን የፀረ ሰብል ነፍሳቶች ሊከሰቱ ስለሚችሉ እንደዚያው ከወቅቱ ጋር ወቅታዊ መከላከልን መንተራስና በንቃት መስራትን ይጠይቃል፡፡

ይህ ሁሉ ደረጃ ታልፎ የሰብል መሰብሰቢያ አጋጣሚም ላይ ቢሆን ማለትም በአጨዳና በውቂያ ወቅት ድንገተኛ የግሪሣ ወፍን የመሣሠሉ የምርትና ምርታማነት አውዳሚ ክስተት ሊያጋጥም ስለሚችል ክትትሉ በዘርፉ ፋታ የለሽ ሥራን ይጠብቃል፡፡

በሌላም በኩል በአንዳንድ የአርሶ አደር አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀና ያልተከተለ ድንገተኛ ዝናብ ሊከሰትና የምርት መጐዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ምርትን ምርታማ ሊያሰኙ ከሚችሉ ገፅታዎች ደግሞ የምርት ጥራትና ብዛት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ስለዚህ ልማታዊው አርሶ አደር ከማሣ ዝግጅት ጀምሮ ባሉት ሂደቶች በተለይ በሰብል መሰብሰቢያ ወቅቶች ምርትን ለመጠበቅና የደረሱ ሰብሎችንም ወቅታዊ የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የአየር ንብረት ትንበያን በመመርኮዝ ለደረሱ ሰብሎች አሰባሰብ መረባረብ የግለሰብ ብቻ ሣይሆን የኅብረተሰብ ተሣትፎን ይፈልጋል፡፡

ሌላው በምርትና በምርታማነት ዘርፍ የግብርና ምርምር ማዕከላት በየጊዜው አዳዲስና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ፀሃይን ወይም የቆላማ አየር ንብረትን ሊቋቋሙ የሚችሉ ወይም በውኃ አጠር አካባቢያዎች ችግርን ተቋቁመው ቶሎ የደሚደርሱ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮችና ለአልሚዎች በማዳረስና ስለምርትና ምርታማነቱ ግንዛቤን መፍጠር ጐን ለጐን በስፋት መሰራት አለበት፡፡

ይህ እንግዲህ በግብርናው በእርሻው ዘርፍ ያለውን ነው፡፡ በሌሎችም የልማት ዘርፎች ቢሆን ጥረቱ ቢበልጥ እንጂ ከዚህኛው ዘርፍ የሚተናነስ አይደለም፡፡ ሳይለፉበትና ሳይደክምበት ልማት ውጤታማ መሆን አይችልምና ነው፡፡ በጥሩ ሁኔታ ያለሙት የልማት መስክ ምርትና ምርታማነቱ በእጅጉ ይጨምራል፡፡ በፋብሪካዎችና በኢንዱስትሪ መስክም ቢሆን ይኸው ነው፡፡ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚሉውሉ ቁሣቁሶችን ለመሥራት የሚውለው ጥሬ እቃ ጥራት ጥንካሬና ብዛት ለምርትና ምርታማነት ግብዓትነት የሚውሉ ሌሎች ነገሮችን አካትቶ መቅረብ ይገባል፡፡ 

በልማትና ምርታማነት ዙሪያ በተለይ በከፍተኛ ተነሳሽነት የተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ ምርት ላይ ሲደርስ ብክነት እንዳይኖር ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ከላይ ከዘረዘርናቸወ ጥቂት የልማት የምርትና ምርታማነት ማሣያዎች በግብርናውም ሆነ በውኃ ኃብት ልማት በፋብሪካውም ይሁን በኢንዱስትሪው መስክ ለምሣሌ ከግብርናው ዘርፍ ብንነሣ በምርት መሰብሰብ ጊዜ አንዲት ፍሬ በከንቱ መባከን የለበትም፡፡ ከዚሁ ከግብርናው ዘርፍ ሳንወጣ አንዲት ጠብታ የዝናብም ይሁን የመስኖ ውኃ ያለልማት መባከን የለበትም፡፡ እንዲሁም አንዲት ቁንጣሪ አፈር በጐርፍና በአውሎ ንፋስ መጠረግ የለበትም፡፡ ይህ ሁሉ የምርትና ምርታማነት ብክነትን ስለሚያስከትል ነው፡፡ ስለአፈርና ውኃ ብክነት ሲነሳም ታላቁ የአባይ ወንዛችን ያላንዳች ታዛቢና ከልካይ የስንትና ስንት ትውልዶችን የዘመናት እድሜውን የአገራችንን አፈርና ውኃ እያጋዘ ለባዕዳን መበልፀጊያ ሆኖ ኖሯል፡፡

ዛሬ ላይ ግን ያ ብክነት እንዳይቀጥል እያንዳንዱ ዜጋ ጠጠር ጥሎ ሃይ ሊለው ተሰናድቷል፡፡ የውኃ ኃብት ዘርፍም ቢሆን በዚህ ዘመን ከነዳጅ ባልተናነሰ ሁኔታ ዓላማችንን ማነጋገር ከያዘ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በእርግጥ ውኃ ህይወት ነው፡፡ ያለውኃ ምንም መስራት አይቻልም፡፡ ውኃ ህይወት ነው፡፡ በተለይ ለአገራት ዕድገት ዋና መጋቢ አንቀሳቃሽ ሞተርና ኃይል ነው፡፡ ከውኃ የሚገኘው የኤክትሪክ ኃይል ከብክለት የፀዳ ነው፡፡ ይህም ሲባል ከኒውክሌየር ኃይል ከሚገኘው የኤሌክትሪክና መሰል የኃይል ማመንጫ በእጅጉ ይለያል፡፡

የውኃ ሀብትነት ከዚህም በላይ ይዘልቅና ሌሎች ልማቶችን ሲያለማ ይስተዋላል፡፡ ከእነዚህም ለዓሳ ምርትና ውኃ ላይ መዝናኛ ብሎም ለቱሪዝም ሀብትነት ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታውን እያጐላ ይሄዳል፡፡ ይህ እንግዲህ በአገራት የጉዞ ታሪክ ተዝቆ የማያልቅ ምርትን የመጣል ማለት ነው፡፡

በተጓዳኝ ትርጉሙም የምርት ወይም የሀብት ብክነት የለም ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ መልኩ ከተሰራበት እናም አሁን ያለው ቀጣዩ አገር ተረካቢ ትውልድ የአገርን ሀብት ከጥቂቱ ጀምሮ እስከ ብዙው፣ ከትንሹ እስከ ትልቁ በየፈርጁ ተንከባክቦና ጠብቆ ያለብክነትና ያለ መንጠባጠብ አገሩንና ሕዝቡን ሊያሳድግበትና ሊያበለጽግበት ይገባል፡፡

አሁን…አሁን በውጭ ኢንቨስተሮችም ይሁን በአገር ዜጐች እየተቋቋሙና እየለሙ ያሉ ታላላቅ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ይታያሉ፡፡ ታዲያም እነዚሀ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ለሚያመርቷቸው ማንኛውም ዓይነት ምርት ግብዓት የሚሆናቸውን ጥሬ ዕቃ ከአገር ውስጥ ተጠቅመው ለአገር መስራታቸውን ትልቁ የግዛቤያቸው መሠረት አድርገው መሆን አለበት፡፡

ከአገር ተመርተው ወደ ውጪ የሚላኩዋቸው ምርቶቻቸው የአገርን ስም ይዘው ስለሚሄዱ ጥራትንና ልዩነትን መፍጠር ግባቸው ማድረግን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ጥራት ያላቸው ምርቶች ከምንም በላይ ማስታወቂያዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም እያንዳንዱ ዜጋ ከሚያለማው ልማትና ከሚያመርተው ምርት ፊትና ኋላ አገሩን ወገኑን እያሰበ መሆን አለበት፡፡