ኢንቨስትመንት ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን ስኬት!

  • PDF

ዮርዳኖስ ሞላ

ኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስመንት አማራጮች ያላት አገር ነች። የትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ ማዕድንና ቱሪዝም ዘፎች ለኢንቨስትመንት አማራጮች ሆነው ይገኛሉ። መንግሥት ቀደም ሲል በመንግሥት ተይዘው የነበሩ ተቋማትን ወደ ግል ማዞር የሚያስችል እቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል። በርካታ በመንግሥት ሥር የሚገኙ ተቋማትን ወደ ግል ለማዞር በተያዘው እቅድ መሠረት በያዝነው የበጀት ዓመት 20 የሚሆኑ የልማት ድርጅቶች ወደ ግል እንደሚዛወሩ ነው።

በተያዘው የበጀት ዓመት እነዚህን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በጨረታ አወዳድሮ ለመሸጥ ታቅዷል። ባለፈው የበጀት ዓመትም የተለያዩ የመንግሥት የልማት ድርጀቶችን ወደ ግል በ6 ነጥብ 2 ቢሊዬን ብር መዛወራቸው ይታወቃል።  በመንግሥት ይዞታ የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዞሩ ተግባር ለኢንቨስትመንት  መስፋፋትና መጠናከር አጋዥ እንደሆነም እሙን ነው።

በአገራችን ካሉት የኢንቨስትመንት አማራጨች አንዱ የትምህርት ዘርፍ ነው። ይህ ዘርፍ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ቀልብ የሳበ ትልቅ የኢንቨስትመንት አማራጭ ሆኗል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በርካታ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ የሣይንስና ቴክኖሎጂ  ዩኒቨርሰቲዎችና ተቋማት፣ የጤና ሥልጠና ተቋማትና ኮሌጆች ተስፋፍተዋል። ይህ የአንቨስትመንት ዘርፍ አሁንም ገና ያልተነካ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም።

ኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ልማት ኢንቨስትመንት ያላት አቅምም ቀላል እንዳልሆነ አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በአገሪቱ መገኘታቸው በጥናት ከተረጋገጡ ማዕድናት መካከል ወርቅ፣ ታንታለም፣ ፖታሽ፣ ፕላቲኒየምና የመሳሰሉት ይገኙበታል።  ከዚህም በተጨማሪ ከ45 ሺሕ በላይ ሜጋ ዋት ማምረት የሚችል የውሀ ሀብት እንዳላት ይታወቃል። በዚህ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ ኢንቨስተሮች ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ለማወቅ አያዳግትም።

ከዚህም በተጨማሪ በግንባታው ረገድ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዳላት ይታወቃል። በመንገድ፣ በመኖሪያ ቤቶችና በንግድ ተቋማት ግንባታዎች ሰፊ ኢንቨስትመንትን የሚጠይቁ በመሆናቸው ይህም አንድ አማራጭ ሆኖ ያገለግላል።

የቱሪዝም ዘርፍም ሌላው የኢንቨስትመንት አማራጭ ነው።  በዚህ ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ከዘርፉ በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ ይሆናሉ። አገሪቱ በዚህ ረገድ ከፍተኛ የሆነ ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች ያሏት በመሆኑ ዘርፉ ለኢንቨስትመንት አመቺ ዘርፍ እንደሆነ ነው።

የማኑፋክቸርንግ ዘርፉ ሌላው የኢንቨስትመንት አማራጭ እንደሆነ ይታወቃል።  ከሦስት ዓመታት በፊት የተጠና አንድ መረጃ  እንደሚያሳየው ይህ ዘርፍ እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ መሠረት አምስት በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱ ምርት የሚሸፍን ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢንዱስትሪው አስተዋጽኦ ደግሞ 37 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል። ይህ ዘርፍ የምግብ ፋብሪካዎችን፣  የጨርቃጨርቅና አልባሣት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን፣ ወረቀት፣ ብረታብረት እና የእንጨት ሥራ ፋብሪካዎችን ያጠቃልላል። ይህ ዘርፍ ለኢንቨስትመንት ትልቅ አማራጭ እንደሆነም ይታወቃል።

ግብርና ሌላው መጠነ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ነው። ይህ ዘርፍ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሠረት ነው። በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ተጠቃሚነታቸው አያጠያይቅም። እስከ 86 በመቶ የሚደርሰው ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት የግብርና ምርት እንደሆነ ይታወቃል።  የእህል ምርትና የእንስሳት እርባታ ላይ በርካታ ሊሰሩ የሚችሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዳሉ ነው።
አገራችን በእንስሳት እርባታ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ትገኛለች። ይሁን እንጂ ከዘርፉ የሚገኘው ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ የታሰበው ያህል አይደለም። ይህንን ዘርፍ መንግሥት አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩንም ሆነ አርሶ አደሩ በዘመናዊ መልክ እንስሳት የማርባት ልምድ ለማስረጽ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ነድፎ እየሰራበት ያለ ቢሆንም ባለሃብቶችንም በዘርፉ ቢሰማሩ ቀላል የማይባል ጥቅም ሊያገኙ እንደሚችሉ እሙን ነው።  እንግዲህ ከላይ የተገለጹትና ሌሎች በዚህ ጽሀፍ ያልተነሱ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮችና የተፈጥሮ ፀጋዎች  ባለቤት በሆነችው ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሳይስፋፋ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። 

ኢትዮጵያ ለልማት ሊውሉ የሚችሉ ሰፋፊ መሬቶች አሏት። ከዚህም በተጨማሪ ተስማሚ አየር ካላቸው የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ነች። ይሁን እንጂ ይህንን የተፈጥሮ ፀጋ ወደ እለታዊ ጥቅም ለመቀየር የሚደረግ ምንም ዓይነት ጥረት አልነበረም።

ባለፉት ሥርዓታት የአገረቱን የልማት አቅጣጫዎችን በመለየት ከድህነት ለማላቀቅ የሚሰራ መንግሥት ባለመኖሩ ምክንያት ሕዝቧ ድህነት ለወለደው የሥራ አጥነት ችግር ሲዳረግ ቆይቷል። አገሪቱም የሁከትና የግጭት መናኸሪያ ሆና ለበርካታ ዓመታት ዘልቃለች።

ኢትዮጵያ ያሏትን ፀጋዎች መጠቀም የሚያስችላት አሠራር የዘረጋ መንግሥት ስላልነበረ ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ አልቻለችም። በየጊዜው ይፈራረቁ የነበሩት መንግሥታት ለሕዝቡ ብልጽግና የሚያስቡበት ጊዜ ባለመኖሩም የተነሳ  ለዘመናት በድህነት መማቀቅ እጣ ፈንታቸው ሆኖ ዘልቋል።

በአገራችን አሁን እየታየ ያለው የልማት፣ የሠላምና የዴሞክራሲ ለውጥ ለማምጣት በርካታ ኢትዮጵያውያን ተሰውተዋል። በእነሱ መስዋዕትነት የተገኘው አሁን ያለንበት የልማት ዘመንም ቀደም ሲል የነበሩት የተወሳሰቡ ችግሮችን በመቋቋም በፈጣን ሁኔታ ማደግ የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የተጀመሩ አዳዲስ የኢንቨስትመንት አጀንዳዎች በርካታ ናቸው። ቀደም ሲል በግለሰብ ደረጃም ሆነ በመንግሥት ያልተሰራባቸውና ከሥርዓቱ መቀየርና ለኢንቨስትመንት አመቺ ሁኔታ መፈጠር ጋር ተያይዞ ከመጡት አዳዲስ የኢንቨስትመንት አቅጣጫዎች አንዱ የአበባ ልማት ነው።

የአበባ ልማት በአገራችን  የተለመደ አልነበረም። እንደ ኬኒያ የመሳሰሉ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሣሣይ መልክዓ ምድር ያላቸው አገራት የአበባ ልማት ከጀመሩ በርካታ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ይሁን እንጂ የጎረቤት አገራትን ተሞክሮ ወስዶ ይህንን ልማት ለማስፋፋት ጥረት አልተደረገም ነበር።

አገሪቱ ለሆርቲካልቸር ተስማሚ አየር ቢኖራትም ልማቱ የተጀመረው ከስድስት ዓመታት በፊት ነበር። የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት በሰፊው ማምረትና ለውጭ ገበያ ማቅረብ የተጀመረው ከቅርብ ዓመታት በፊት ነበር።

በአገሪቱ የሆርቲካልቸር ልማት ቢስፋፋ ለምጣኔ ሀብቱ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግሥት ዘርፉን ለማጠናከር በርካታ እርምጃዎች  በመውሰድ ላይ ይገኛል። መንግሥት የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በዚህ የልማት ዘርፍ እንዲሳተፉ ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ምክንያት የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ  ምርት ፈጣን እድገት እያስመዘገበ መምጣት ችሏል። 

የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ግን በተቀናጀ መልኩ ባይሆንም በተበታተነ መልኩ  ቀደም ሲልም በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደነበር ይታወቃል። አትክልትና ፍራፍሬን በመላ አገሪቱ የማስፋፋትና አርሶ አደሩ በዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ የማድረግ ሁኔታ ግን አልነበረም። በተበታተነ መልኩ የነበረው ልማትም ውጤታማ አልነበረም።  ከዚህ ጎን ለጎን  የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሃብቶች በሰፊው እንዲሰማሩ የተደረገው ከቅርብ ጊዜ በኋላ ነበር። 

የአበባ ምርት ግን በአገራችን አይሰራበትም ነበር። አበባ አንድ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እንደሆነም ግንዛቤ አልተፈጠረም። በሌሎች የልማት ዘርፎች የሚታዩ ችግሮች በሆርቲካልቸርም መኖራቸው እሙን ነው። ከእነዚህም አንዱ የተቀናጀ ልማት አቅጣጫ በአገሪቱ አለመኖሩ ነው።

ሌላው ችግር ደግሞ በአገሪቱ የነበረው ጦረኛ መንግሥት የእርስ በርስ ግጭቶችን በማባባስና ከጎረቤት አገራት ጋርም አስፈላጊ ያልሆኑ ግጭቶችን በመጫር ሕዝቡ ተረጋግቶ ስለ ልማት የሚያስብበት ጊዜ ማሳጣት ነው።

የነበረው መንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ወደ ግጭትና ጦርነት ስለነበር ሕዝብ ስለኑሮውና ስለእድገቱ የሚያስብበት ጊዜና እረፍት ነስቶት አላገኘም ነበር።

ሃብትን የሚያበረታታ ባለሃብቶችን የሚያጠናክር የአሠራር ሥርዓት በአገሪቱ ባለመኖሩ ምክንያት በተለያየ የልማት ዘርፍ እንዳይሰማሩ መሰናክል ሆኖ ኖሯል። በአገሪቱ ሕግ አንድ ባለሃብት ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ካፒታል ያለውን የሥራ እንቅስቃሴ ወይም ንግድ መምራት እንደማይችል  ተደንግጎም ቆይቷል። ከዚያ በላይ ሃብት አካበተ ተብሎ የሚጠረጠር ባለሃብት ሀብቱ ይወረስሳል።

ከዚያም ባሻገር በአገሪቱ ሠላምና ዴሞክራሲ ባለመኖሩ ሰው ተደብቆና ተሸማቆ ይኖር ስለነበር “ጎመን በጤና” በሚል ፈሊጥ ቀደም ሲል የያዛትን እየተጠቀመ መኖርን የመረጠ ባለሀብት ቁጥር ቀላል አልነበረም። 

የግል ሃብት ክምችት በመታጠሩ ምክንያት በአገሪቱ የተለያዩ የልማት ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ማዋል ይፈልጉ የነበሩ ግለሰቦች ሕልማቸው መክኗል። የባለሃብቶች እንቅስቃሴ መገደብ መንግሥትም ለልማት ይሰጠው የነበረው ዝቅተኛ ግምት ተደማምረው የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እያሽቆለቆለ የሄደበትና የኢትዮጵያ ሕዝብ የእለት ጉርስም ያጣበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። 

የአገር ልጆች ሀብት እንዳያካብቱና የውጭ አገር ባለሀቶች ደግሞ ወደ አገር ገብተው በየተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች እንዳይሰማሩ በሩ የተዘጋ ነበር። በዚህ ምክንያት  ኢንቨስትመንት የሚባል ነገር  ለአገሪቱ ባዳ ሆኖ  ዓመታት አልፈዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች ካላቸው የዓለም አገራት አንዷ ነች። በግብርና፣ በኢነርጂ፣ በማዕድንና በሌሎች በርካታ ዘርፎች የኢንቨስትመንት አማራጮች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ የኢንቨስትመንት  አማራጮች ሥራ ላይ ባለመዋላቸው የተነሳ አገሪቱ ከድህነት ሳትላቀቅ ቆይታለች። የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገራት ባለሃብቶች ሀብታቸውን ሥራ ላይ ለማዋል በሕግ የተከለከሉበትና በአገሪቱ የነበረው ሕግ ኢንቨስትመንትን የማያበረታታ ስለነበር ነው። በዚህ ምክንያት ምንም ዓይነት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በአገሪቱ እንዳልነበረ ግምት ውስጥ የሚገባ አልነበረም።

እንደሚታወቀው ለአንዲት አገር እድገት የግል ባለሃብቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ድርሻ አለው። የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ካልተስፋፋ የአንዲት አገር ኢንቨስትመንት ሊስፋፋ አይችልም። ኢንቨስትመንት ካልተስፋፋ ደግሞ የምጣኔ ሀብት እድገት በተፈለገው መልክ አይኖርም። 

የግሉ የኢኮኖሚ ዘርፍ እንዳይንቀሳቀስ እጅና እግሩ በሰንሰለት በታሰረበት ሁኔታ  ኢንቨስትመንት ያድጋል ተብሎ አይታሰብም። በአገራችን የነበረው ተጨባጭ ሁኔታም ከዚሁ የተለየ አልነበረም። በመሆኑም በአገራችን የነበረው የኢንቨስትመንት ሁኔታ የአገሪቱን እድገት ለመግታት አንድ ከፍተኛ መሰናክል እንደነበር መገመት አያዳግትም። 

በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች ባለበት አገር ምንም ዓይነት ኢንቨስትመንት አለመኖሩ አገሪቱንና ሕዝቡን ምን ያህል እንደሚጎዳው ለማወቅ አያዳግትም። በዚህ ምክንያት የሕዝቡን ችግር እየተባባሰና ኑሮ እየከበደው የሄደበት ሁኔታ ነበር።   የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እየዘቀጠና እየተሽመደመደ በሄደ ቁጥር ወጣቱ ለሥራ አጥነት ችግር ሰለባ ይሆኖል። የሚሰሩ እጆችና የሚያስብ አእምሮ እያለው በማያፈናፍን ፖሊሲ ምክንያት ለችግር ሲዳረግ መኖር ግድ ሆኖበት ዘልቋል። 

በአገራችን ለዘመናት የዘለቀው የድህነት፣ ጉስቁልናና ረሃብ ዋናው ምክንያትም የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት መሽመድመድና መውደቅ ነበር። ለዚህ ደግሞ የማያሰራ ሕግ በአገራችን በመዘርጋቱ ነው፡፡ የነበረው መንግሥት ከልማት ይልቅ ጦር መምዘዝ፣ ከዲፕሎማሲ ይልቅ ኃይልን መጠቀም ይቀናው ስለነበር ችግሩን ሲያባብሰው ኖሯል። 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ  ያለው የኢንቨስትመንት ሁኔታ ሲታይ ግን ቀደም ሲል ከነበረው ጋር ለንጽጽር ሊቀርብ የሚችል አይደለም። ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት 797 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 55024 ፕሮጄክቶች ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡ ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥም  60 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ፕሮጄክቶች የማምረትና አገልግሎት የመስጠት ሥራቸውን ጀምረዋል። በ122 ቢሊዮን ካፒታል የሚንቀሳቀሱ 3090 ፕሮጄክቶች ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በአገራችን አልተስፋፋም ነበር።  የውጭ ባለሃብቶች ካፒታላቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በተለያዩ ዘርፎች  ኢንቨስት የሚያደርጉበት ሁኔታ አልነበረም። ይህ የሆነው በሁለት ምክንያት ነበር። አንደኛው በአገሪቱ የኢንቨስትመንት እድል የተዘጋ ስለነበር ሲሆን ሌላው ደግሞ  በአገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ባለመኖሩ ነው።
በአገሪቱ ያለውን የአንቨስትመንት ሁኔታ አሁን ላይ ሆነን ስናየው  የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከዓመት ዓመት እያደገ መጥቷል። በ360 ቢሊዮን  ብር 60166 ፕሮጄክቶች ተመዝገባዋል፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም 1377 በቀጥታ የማምረትና አገልግሎት የመስጠት ተግባር የገቡ ናቸው፡፡ 710 ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ 
በአገሪቱ  ለኢንቨስተመንት አመቺ ሁኔታ በመፈጠሩ ዜጎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።  ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ውስጥ 258 ሺህ ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ፡፡ በተጨማሪም 652 ሺህ ዜጎች በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል አግኝተዋል።  በአገሪቱ ወደ ሥራ ያልገቡና በግንባታ ሂደት ላይ  ያሉ ፕሮጄክቶች ሲጠናቀቁ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ቋሚና ጊዜያዊ  ሠራተኞች የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይህ የሥራ ዕድል በግል ኢንቨስመንት አማካይነት የሚፈጠር ነው፡፡ በሌሎች የመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ሊፈጠር የሚችለው የሥራ ዕድል ግምት ውስጥ ሲገባ የሥራ አጥነት ችግርን ከመፍታት አንጻር ምን ያህል ጥረት እየተደረገ እንደሆነ መረዳት ቀላል ይሆናል። 
በአገሪቱ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትና የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሃብቶች በአገሪቱ ባሉ በርካታ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማሩ መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል።
አንደኛው አገር ውስጥ ያለውን አሠራር የማስተካከልና የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚኖርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የተለያዩ የማበረታቻ ተግባራትን ቀርጾ መፈጸም ነው። በዚህ መልክ መንግሥት ከወሰዳቸው የተለያዩ የማበረታቻ እርምጃዎች መካከል ባለሀብቶቹ ቁሳቁሶችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ መፍቀድ አንዱ ነው፡፡ ከሁለት እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ የግብር የእፎይታ ጊዜን መስጠት ደግሞ ሌላኛው እርምጃ ነው። ይህ ደግሞ በአገራችን ያለው የኢንቨስትመንት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንዲመጣ አስችሏል፡፡

በዚህ ምክንያት በአገሪቱ ያለው የኢንቨስትመንት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም ሆኑ  የውጭ አገር ባለሃብቶች ቁጥር እያደገ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ከላይ ለማየት የተሞከረው በፌዴራል የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ አስተባባሪነት እየተሰራው ያለውን ነው፡፡ በክልሎች ደረጃ የሚሰሩም በርካታ የኢንቨስትመንት ልማቶች አሉ። በጋምቤላ ሕዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥትና በትግራ ክልል ያለውን  ለአብነት ማየት ይቻላል።

የጋምቤላ ክልል ከታዳጊ ክልሎች አንዱ ነው። ባለፉት ሥርዓታት ትኩረት ካልተሰጣቸው ክልሎች አንዱ ስለነበር በአካባቢው የተስፋፋ ልማት አልነበረም።  ልማት ብሎ ነገርም የለም። የመሠረተ ልማት አውታሮች ባለመስፋፋታቸውና  በወቅቱ የነበሩ መንግሥታት አካባቢውን ለወታደራዊ ማዕከላት ከመጠቀም ያለፈ  ኅብረተሰቡን ሊጠቅም የሚችል የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ባለመገንባታቸው  የተነሳ ባለሀብቶች ወደ አካባቢው ሄደው መዋዕለ ንዋያቸውን ሥራ ላይ ለማዋል  ያልቻሉበት ሁኔታ ነበር። 

በአገራችን ልማታዊ መንግሥት ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በክልሉ አምስት ቢሊዮን የሚጠጋ ብር ካፒታል ላላቸው 800 ለሚሆኑ ባለሃብቶች ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምሩ ከሩብ ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዚያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ታውቋል፡፡

በጋምቤላ ሰፊ የእርሻ መሬት እንዳለ ይታወቃል። በመሆኑም በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሃብቶችን በማበረታታትና አንዳንድ አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ በዘርፉ ያለውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲጠናከር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።  በዚህ ዘርፍ ፈቃድ ለወሰዱ 352 ባለሃብቶች 256 ሺህ ሄክታር መሬት ተሰጥቷል።

በትግራይም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው የአምስት ዓመቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማሳካት በሚያስችል መልኩ እየተካሄደ ነው፡፡ የክልሉን ኢንቨስትመንት  በየዓመቱ በ20 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው። በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መርሀ ግብር መሠረት ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው እንቅሰቃሴ የክልሉ የኢንቨስትመንት ካፒታል ፍሰትና በመስኩ የተሰማሩት ኢንቨስተሮች ቁጥር ከእቅዱ ጋር በተጣጣመ መንገድ ማደግ ችሏል።

ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በተያዘው እቅድ መሠረት  በአሁኑ ወቅት  720 የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጠንተው ለባለሀብቶች ተዘጋጅተዋል። ባለሃብቶቹ ወደ ሥራ በሚገቡበት ወቅት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ከ18 ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ ነው።  በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በሚካሄደው እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ከተማ የፕሮሞሽን አገልግሎት የሚሰጥ ተጨማሪ ቢሮ ተቋቁሞ ተግባሩን እያከናወነ ይገኛል።
አገሪቱ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ ያላት በመሆኑ የውጭ ባለሃብቶችን በሰፊው የመሳብና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ከውጭ አገራት ባለሃብቶች ጋር እየተቀናጁ ልምድና እውቀት መቅሰም በሚያስችል መንገድ ኢንቨስትመንቱ እየተስፋፋ ይገኛል። 
በርካታ የውጭ አገር አቅም ያላቸውን ባለሃብቶች በአገሪቱ ኢንቨስትመንት በተለያዩ አማራጮች እንዲሳተፉ ለማድረግ በየአገራቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሣደሮች በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ።
የንግድ ትርዒቶችንና ባዛሮች እንዲዘጋጁ በማድረግና የፕሮሞሽን ሥራዎችን በማከናወን፤ ከባለሃብቶች ጋር ቀጥተኛ የሆነ ውይይት በማድረግና አገሪቱ ያላትን ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የማስተዋወቅና በአገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ በማስረዳት፤ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ባለሃብቶች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ በመጋበዝና የመሳሰሉን ተግባራት በመፈፀም የውጭ አገር ባለሃብቶችን ወደ አገራችን ለመሳብ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።