የነገዋ ፀሐይ አዲስ ተስፋን ሰንቃ ትመጣለች

  • PDF

ሀብተወልድ ፈቃዱ

ኢትዮጵያ በፌዴራሊዝም ሥርዓት አወቃቀር ከሚተዳደሩ የዓለማችን አገሮች አንዷ ናት፡፡ ይኸው የፌዴራሊዝም ሥርዓት አወቃቀርም ለአገሪቱ ልማት፣ ዕድገት፣ ሠላምና ዴሞክራሲ ላበረከታቸው ድሎች መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ አገራችን በአሁኑ ወቅት ግብርና መር የኢኮኖሚ ሥርዓትን የምትከተል ናት፤ በዚሁ ስትራቴጂ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ብቻ እያሳደገች ሌሎች ዘርፎችን ለአፍታ ያህልም ቢሆን ቸል ብላ ያዘገመችበት ጊዜ አልነበረም፡፡

በዚህም ታዲያ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ በግብርና መርነቱ ቀዳሚ አድርጋ በርካታ ሥራዎችን ከውናለች፤ እየሰራችም ነው፡፡ ከአምስት ዓመቱ የእቅድና ትራንስፎርሜሽን ሰፋፊ እንቅስቃሴዎችና ምርጥ ጅማሮዎች ጋር፡፡ አገሪቱ በከተማም ሆነ በገጠር ለዚህ ከፊታችን ላለውና እየሰራን ከምንገሰግስለት የእቅድና ትራንስፎርሜሽን ስኬት አምጪ አምዶችን በየሥፍራው እያቆመችና እየተከለች ትገኛለች፡፡

ከእነዚህም ታላላቅ የዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር አምሳያ ብርቱ ሥራዎች በግንባር ከሚጠቀሱ ስኬታማ ሂደቶች መካከል በጥቃቅንና አነስተኛ ብድር ተቋማት ሥር አስደናቂ ሥራዎችን እያከናወኑ አጀብ የሚያሰኝ ውጤት ላይ የደረሱ በርካቶች አሉ፡፡
በዘርፉም የሚታዩ የነገ ታላላቅ ፋብሪካዎችን ማለትም በጥቃቅንና አነስተኛ ብድር አቅራቢ ተቋማት ተነሳሽነትን በምናይበት ወቅት ልማታዊው የኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለፈርጀ ብዙ እድገት መሰለፉንና ለአገር ብልፅግና እየታተረ በትጋት የቆመ በሕዝብ ለሕዝብ የተወከለና የተመረጠ መሠረቱም፣ ዓላማውም፣ ግቡም ሕዝባዊና አገራዊ መሆኑን በተደጋጋሚ ያስመሰከረበት አንዱ መንገድ ነው፡፡

በአገሪቱ ታሪክ መንግሥታት ለአገሪቱ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠርም ሆነ ዜጎችን እንዲህ ባለ አቋራጭና አዋጭ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የአመራር ቅልጥፍናና አርቆ አስተዋይነት፣ ወገናዊነትና ሰርቶ የማሰራት ሥራ የተከወነበት ጊዜ የለም፡፡ እጅግ በጣም በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ከባዶ ወይም ከምንም ከሚባል ደረጃ ተነስተው በጥቂት ዓመታት የማይታመን ለውጥ ማምጣቸው ታይቷል፡፡

እነዚህ ዘርፈ ብዙ የወገን የዕድገት መሠረቶችና ማማዎች ማለትም በጥቃቅንና አነስተኛ ብድር ተቋማት በመታገዝና በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሰማራት ከራሳቸው ተጠቃሚነት ባሻገር ለአካባቢያቸው መሠረተ ልማት እድገት ወሣኝ ሚና የተጫወቱና በመጫወት ላይ ያሉ የት የለሌ ወ-ጣቶችን ሲታሰቡ የነገዋን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት እያንዳንዱ ዜጋ በየተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ ጠንክሮ ከሰራ ከራሱ ባለፈ ሌላው ዜጋ የፀረ ድህነት ትግሉን ጎራ እንዲቀላቀልና የዚህ ትግል አጋር አንድ አካል በመሆን በመስራት እድገትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ የሚጋብዙ ባለ ታላቅ ራዕይ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ነው፡፡

ዛሬ…ዛሬ በከተሞች አካባቢ ብንመለከት በማህበራት ተደራጅተው ለምሣሌ ጥርብ ድንጋይ ወይም በኮብልስቶን የውስጥ ለውስጥና የአስፋልት ዳርቻዎች የእግረኛ መንገዶችን በማንጠፍ ሥራ የተሰማሩ በርካታ ዜጎች ማንሳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል እንደዚሁ በማህበራት በመደራጀት በሽመና ሥራ፣ በዳቦና እንጀራ መጋገርና ማቅረብ፣ በተለያዩ ንግድ ዘርፎች በመሰማራት ኅብረተሰባቸውን ከማገልገልና ከመጥቀም አልፈው ለሌሎችም ወገኖቻቸው የሥራ ዕድል በመፍጠር መልካም አርአያነታቸውንና የተምሣሌትነት አሻራቸውን የተከሉ በቁጥር የማይደረስባቸው ዜጎች ወይም ወገኖች እንዳሉ ግልፅ ነው፡፡

መንግሥት በብልህ አመራሩና በእድገት ቀያሽ ፖሊሲው ትኩረት ሰጥቶ ማሰራቱን ቀጥሏል፡፡ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ ወገን ለወገኑ ይተሳሰባል፡፡ ጥቂት ነገር ይዞ ተንቀሳቅሶ ብዙ አድርጎ ብዙ ሰርቶና አምርቶ ተለውጦ የሚታደግበትና የሚገለፀግበት ጊዜ በሥራና በስራ ብቻ አሁን መሆኑን በርካቶች ተገንዝበውታል፡፡

የአምስት ዓመቱ የዕቅድና ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ዛሬ ላይ ሆኖ የነገዎቹን ታላላቅ  ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች በዛሬዎቹ የጥቃቅንና አነስተኛ ብድር ተቋማት አጋዥነት የተተለሙና የተጀመሩ ሥራዎች የሩቆች የሚመስሉትን የወደፊቱን የአገራችንን የብልጽግና ፏፏቴዎች ማየት ይቻላል፡፡

መንግሥት የሥራ መስኮችን በስፋት በመተለምና የሥራ አጦችን ቁጥር ለመቀነስ ብሎም ሥራ አጥነትን ከአገሪቱ ለማጥፋት ባለው ቁርጠኝነት በእነዚህ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በተከፈቱ ፈርጀ ብዙ የሥራ እድሎች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ከራስ መቻል በላይ ሌሎች ወገኖቻቸው ከድህነት አረንቋ ለመላቀቅ ታላቅ የሥነ ልቦና አሊያም የአሸናፊነት መንገድ ቀያሽ ወይም ደግሞ የሥራ ባህል የለውጥ ኃይል በመሆን ብርሃን የፈነጠቁ ሆነዋል፡፡ ይህ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋም የዜጎች ተቀዳሚ ዋስትና ሆኗል፡፡ በማህበር ተደራጅቶ ለሥራ የተነሳሳ የትኛውም ወገን ቢሆን መንግሥት ዕድሉን አመቻችቶለታል፡፡ ይህም በመሆኑ በአገራችን በአሁኑ ጊዜ በተለይ ሴቶችና ወጣቶች የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ ሰርተው የሚያገኙትን በጥቂቱም ቢሆን እየቆጠቡ ካሰቡት ብቻ ሳይሆን ካሰቡት በላይ ደርሰዋል፡፡ ሌሎች በርካቶችም የእነዚህን ፈለግና አርአያ በመከተል እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ዜጎች ሊገነዘቡትም የሚገባ አሊያም መረዳት ያለባቸው ቁም ነገር አለ፡፡


ይኸውም ልማታዊ የሆነው መንግሥት በጣም በርካታ መንገዶችን እያሳያቸው መሆኑን ነው፡፡ ይህም ሲባል የዜጎችን የሥራ ባህል መሻሻልና መቀየርን እንዲሁም ከሥራቸው ፍሬ የሚያገኙትን በመቆጠብ የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ ጥበበኞች በመሆን የነገን ትልቅ ራዕይ እንዲያልሙ ማስቻል ነው፡፡

በዚሀ በኩል ታዲያ መንግሥት ከላይ እስከታችኛው የሥልጣን እርከን ድረስ በመውረድ ተከታታይና በርካታ የግንዛቤ ሥራዎችን መስራቱ ለእንዲህ ያለው የለውጥ ፍሬ አገሪቱንም ሆነ ዜጎቿን አብቅቷቸዋል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገራት የሥራ አጥነት ችግር ብዙ የሚወራባት አገር አይደለችም፡፡

ምክንያቱም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ካላት የጀማሪነት ሀሁ ወይም ደግሞ የአገራቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጠንካራ መሠረት ላይ በአዲስ እየተገነባ ያለ ከመሆኑ አንፃር ሲታይና በቀደመው አምባገነን ሥርዓት ከተተበተበችበት ፈርጀ ብዙ ችግር አኳያ ሲታይ በዚህ አጭር ጊዜ እንዲህ ያለ የዕድገትና የለውጥ ፍሬ ማሳየቷና ማስመዝገቧ በእጅጉ ያስደንቃል፡፡ በእጅጉም ያኮራል፡፡

ይህ የተጀመረው የመሠረተ ልማት ፈርጀ ብዙ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ በእነዚህ አጭር ጊዜያት የታየው ትልቅ ለውጥና ዕድገት በቀጣይነት ከእነዚህ የበለጡና የላቁ ውጤቶችን ለማምጣት ተበራትቶ መሥራት ይገባል፡፡ የእድገትና ትራንስፎሜሽን እቅዱ ከግቡ ሊደርስ የሚችለውም በእያንዳንዱ ዜጋ የነቃና የፀና ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡ የግብርና መር ኢኮኖሚ ስትራቴጂያችን በተቀመጠው የጉዞ መስመር በአጭር ጊዜ ፈጣን የእድገት ራዕያችን ውጤታማ እንዲሆን ዜጎች በመረባረብ ለነገ የማያሳድሩት ሥራ ሳይኖራቸው ብርቱ ጥረት የልብ ወኔያቸውን ቀስቅሰው ሥራን ባለመምረጥና ባለመናቅ የነገን ከችግር የተላቀቀችና የበለፀገች ኢትዮጵያን በማሰብ በሰፊውና በረዥሙ እያቀዱ በትጋት መስራት አማራጭ የሌለው የወቅቱ ጥሪና ፈጣን ምላሽ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በየትኛውም የስራ መስክ ጠንክሮ ለሚሰራና ለሚንቀሳቀስ ሁለንተናዋ ገና ያልተነካ ድንግል ነው፡፡ ስለዚህ ይህች አገራችን የዘወትር የልጆቿን እድገትና ማቆሚያ የሌለው ብልፅግና ለማየት ጓጉታለች፡፡
የዚህ ዘመን ታታሪና ብርቱ ብልህና አርቆ አስተዋይ ባለራዕይ መሪዎቿ ከዚያ ከዘመናት የእድገትና ብልፅግና የምኞት ማማዋ ላይ አውጥተው መዘውሩን አስጨብጠዋታል፡፡ ኢትዮጵያን ውድቀቷን የሚመኙላት እቅዳቸው መክኖባቸዋል፡፡ ዛሬ የተጀመሩ ወጥኖች ሁሉ በአጭር ጊዜ ፍሬያቸውን ይሰጣሉ፡፡

የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለዜጎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዳራው እጅግ አርኪ ነው፡፡ ለወደፊትም እነዚህ የዕድገት ዋስትናዎችና መሠረቶች በትውልዶች ቅብብሎሽ ሚናቸውን አጉልተውና አጠንክረው ይዘው የመጓዝ ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በጋራ ርብርብ ሌት ከቀን ሰርተው ራሳቸውንና አገራቸውን ለማሳደግ በሁሉም መስክ ጠንክረው ሁሌም በአዲስ መንፈስ አለባቸው፡፡ የነገዋ ፀሐይ አዲስ ተስፋን ሰንቃ ትመጣለች፡፡ በእርግጥም ነገ የምትወጣዋ አዲስ ፀሐይ አዲስ እድገትን ይዛ መምጣቷ እሙን ነውና፡፡ በዚህ መንፈስና ስሜት ሁላችንም በርትተን እንስራ፡፡