3ተኛው የመላው አፍሪካ ህጻናት መድረክ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀመረ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2005 (ዋኢማ) - በአፍሪካ ባለፈው አስር ዓመት የተመዘገበው ፈጣን የምጣኔ ሃብት እድገት መንግስታት ለህጻናት የሚሰጡት ትኩረት እንዲጠናከር ማድረጉን የአፍሪካ ህብረት ገለጸ፡፡

በአህጉሪቱ ህጻናት የመሰረታዊ ጤና እና የትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረገው ጥረትና ውጤቱ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡

3ተኛው የመላው አፍሪካ ህጻናት መድረክ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡ ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ጉባኤ “ተጠያቂነት ለህጻናት በሚደረግ መዋዕለ ንዋይ ላይ” በሚል መሪ ቃል ነው የተጀመረው፡፡

በጉባኤው እንደተገለጸው በአህጉሪቱ ህጻናት የጤናና የትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረገው ጥረት ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡

በተለይም ለችግር የተጋለጡና አካል ጉዳተኛ ህጻናትን ተጠቃሚ በማድረግ መሻሻሎች ተመዘግበዋል ነው የተባለው፡፡

ባለፈው አስር ዓመታት በአፍሪካ የተመዘገበው ፈጣን የምጣኔ ሃብት እድገት መንግስታት ለህጻናት የሚሰጡት ትኩረት እንዲዳብር አስተዋጽኦ ማበርከቱም ተገልጿል፡፡

በዚህም ከአምስት አመት በታች የህጻናት ሞት ቀንሷል፣ የንጹህ መጠጥና የአካባቢ ንጽህና አቅርቦት ተሻሽሏል፣ በትምህርት ቤቶች የስርዓተ ጾታ እኩልነት እየተረጋገጠ መጥቷል፣ የኤች አይ ቪ /ኤድስ መድሃኒት ህክምናና ሌሎች አገልግሎች አቅርቦት ተጠናክረዋል፡፡

በጉባኤው የኢትዮጵያ ህጻናትን ተወካዮች ጉባኤው ከተገኙት ውጤቶች ጎን ለጎን የመንግስታትን ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ለማስገንዘብ ያግዛል ብለዋል፡፡

ከተገኙ ውጤቶችን ጎን ለጎን ያሉ የአፈጻጻም ችግሮችን ለመቅረፍና የአፍሪካ ህጻናት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማስቀጠል የአፍሪካ ህብረት ቁርጠኛ መሆኑን የህብረቱ የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር ዶክተር ሙስጠፋ ካሉኩ ተናግረዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ የህጻናት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ይበልጥ ለማጠናከር በሁሉም ደረጃ የተላለፉ ውሳኔዎችን ተፈጻሚ ለማድረግ ርብርብ አስፈላጊ መሆኑንም በጉባኤው ተጠቁሟል፡፡

በጉባኤው ሀገራት የህጻናት መብት ለማስከበር ያከናወኗቸው ተግባራትና ያጋጠሟቸው ፈተናዎች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል፡፡