ዘመናዊ የዱር እንስሳት ፓርክ በአዲስ አበባ እየተገነባ ነው

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2005፣ (ዋልታ)- በስድስት ኪሎ አንበሳ ግቢ ላሉ አንበሶች እና በተለያዩ የአገራችን መልክአ ምድር ላይ ለሚገኙ የዱር እንሰሳት መኖሪያ የሚሆን ዘመናዊ ፓርክ  በአዲስ አበባ እየተገነባ ነው ።

አዲስ ዙ ፓርክ ለከተማዋ ነዋሪዎች ደረጃውን የጠበቀ የመዝናኛ ስፍራና የእንስሳት የጥናትና የምርምር ማእከል ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን የአዲስ ዙ ፓርክ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት አስባባሪ አቶ ፈለቀ ይመር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ለፓርኩ የሚሆን 26 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል ያሉት አቶ ፈለቀ ፥ ቅድሚያም በ11.3 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው የአንበሶቹ የመኖሪያ እና የመመገቢያ ስፍራ ግንባታ እየተካሄደ ሲሆን ፥ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ እንዲጠናቀቅ እቅድ መያዙንም ነው የገለፁት።

ከዚህ ጋር ተያይዞ አንበሶቹ እየተንቀሳቀሱ የሚኖሩ በመሆናቸው ፥ በጎብኝዎች  ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ጥንቃቄ የሚያሻው ግንባታ ነው እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

እስከ አሁንም አራት ሜትር ጥልቀት ያለው የመሰረት ግንባታና ፥ እንዲሁም ስምንት ሜትር ወደ ላይ በኮንክሪት የመገንባት ስራና ሌሎች ስራዎች ተጋምሰዋል።

እንደ ፋና ዘገባ አስተዳደሩ ባጠናው ጥናት መሰረት ፓርኩ በአንድ ጊዜ የሚከወን ሳይሆን በሚቀጥሉት አስራ አምስት አመታት 475 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ በአራት ምእራፍ የሚከናወን መሆኑን ታውቋል።