ድርጅት መልዕክቶችን በትክክል ለማድረስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገለጸ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2005 (ዋኢማ) - የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ደህንነት በማሻሻል የሚጠፉ፣ በስህተት የሚላኩ፣ የሚበላሹ፣ የሚጎድሉና የማይመዘገቡ መልዕክቶችን በመቀነስ በሩብ ዓመቱ በሰራው ስራ የእቅዱን መቶ በመቶ ማከናወኑ ተገለጸ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሳይንስ፣ መገናኛና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የድርጅቱን የ2005 ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ገምግሞ በሰጠው አስተያየት በድርጅቱ የእደላ ፍጥነትን ለማሻሻል እየተሰሩ ባሉ ስራዎች የአገልግሎት ፍጥነትን ለማሻሻል የተያዙት ግቦች በአብዛኛው ተፈፅመዋል፡፡

በቴክኖሎጂ የተደረፈ የመረጃ አጠቃቀም መኖር፣ በዓለም አቀፍ የፖስታ ሕብረት የተቀመጠውን የኦ.ኤም.ኤስ የፍጥነት መለኪያዎችና ዓለም አቀፍ የጥቅል ፍጥነት መመዘኛዎችን ለማሟላት መስራቱ እንዲሁም የአሰራር ችግር ያለባቸውን የስራ ክፍሎች ማጥራቱ የድርጅቱ ጥንካሬዎች መሆናቸውን ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ በሩብ ዓመቱ ለመተግበር ከታቀዱት ተግባራት ዝቅተኛ አፈፃፀም የታየባቸው የስራ ሂደት አገልግሎት ፍጥነትን ማሟላት አብዛኛዎቹ ከ30 በመቶ በታች መሆናቸው፣ የገቢ አሰባሰቡ ዝቅተኛ መሆን፣ የክዋኔ ኦዲት አለመደረጉ፣ በቅብብሎሽ መልዕት የሚያገኙ ፖስታ ቤቶች መቀነሳቸው ደካማ ጎኖች እንደነበሩ ቋሚ ኮሚቴው ጠቅሷል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ እንዲሁም ዝቅተኛ የበጀት አጠቃቀም መኖሩና ሴክተር ዘለል ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷቸው አለመሰራታቸውን ቋሚ ኮሚቴው ጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ ፖስታ አገለግሎት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግደይ ገብረ ዮሐንስ በሩብ ዓመቱ አፈፃፀም ላይ ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጡት ግብረ መልሶች ተገቢ መሆናቸውን ጠቁመው ቀጣይ ስራዎቻቸውን ለመስራት የሚያግዙ መሆኑን አመልክተዋል፡፡