ፅህፈት ቤቱ በአገሪቱ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ብሄራዊ የአዕምሯዊ ንብረት አካዳሚ ለማቋቋም ዝግጅቱን አጠናቋል

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2005 (ዋኢማ) - የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት በአገሪቱ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ብሄራዊ የአዕምሯዊ ንብረት አካዳሚ ለማቋቋም ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ፅህፈት ቤቱ ከኢትዮጵያና ከግብጽ ለተውጣጡ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሞያዎች ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚቆይ የአሰልጣኞች ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡ የፅህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አዴሎ በስልጠናው መክፈቻ ወቅት እንደተናገሩት ድርጅቱ ካሁን ቀደም በኢንተርኔት ግንኙነት ብቻ ይሰጥ የነበረውን ስልጠና በአገር ውስጥ ለመስጠት ሰፊ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡

የአእምሯዊ ንብረት ተቋሙ በንግድ ምልክት፣ በቅጂ መብት፣ በኢንዱስትሪ ንድፍ፣ በፓተንትና በግልጋሎት ሞዴል ዙሪያ ሰፋፊ ስልጠናዎችን የሚሰጥ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ስልጠናው ፅህፈት ቤቱ የአዕምሯዊ ንብረት አካዳሚን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማቋቋም የያዘው እቅድ አካል መሆኑንና በቀጣይም የሚሰጡትን ስልጠናዎች ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣሙ በማድረግ በአማርኛ ቋንቋ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ የአካዳሚው ኢትዮጵያ ውስጥ መቋቋም በአገሪቱ ያሉ ሁሉም ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች ስልጠናውን በቀላሉ እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡ ፅህፈት ቤቱ ከዓለም አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚሁ ስልጠና ላይ 18 ኢትዮጵያዊያንና ሶስት ግብጻዊያን ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡