በዞኑ ከ6 መቶ ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ቀረበ

  • PDF

ነገሌ ህዳር 12/2005 (ዋኢማ) - በጉጂ ዞን ባለፉት ሶስት ወራት በተለያዩ የህብረት ስራ ማህበራት የተዘጋጀ ከ600 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን የዞኑ ማህበራት ማደራጃ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የህብረት ስራ ማህበራት አደራጅ አቶ ከበደ ሀይሉ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ወርቁ ለብሔራዊ ባንኩ የቀረበው በ14 የማእድን ፍለጋና ግብይት የህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ነው፡፡ ህብረት ስራ ማህበራቱ በዚህ ዓመት ያቀረቡት ወርቅ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መጨረሻ ለብሄራዊ ባንክ ካቀረበው ወርቅ ጋር ሲነጻጸር ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ለማህበራቱ ለማእድን ፍለጋና ግብይት ሥራ ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክና ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ የኒየን ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ የማህበራቱን የማእድን ፍለጋና ግብይት ለማጎልበት በወርቅ አመዛዘን፣ በማእድን ፍለጋ፣ በወጭና ገቢ አያያዝ ከዞንና ከኦሮሚያ ክልል በተውጣጡ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ በዞኑ ባለፉት ዓመታት በህገወጥ መንገድ ሲካሄድ የነበረው የማእድን ዝውውር ፍለጋና ግብይት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ መቅረቱንም አስረድተዋል፡፡ ማህበራቱ በተያዘው የበጀት ዓመትም ብዛትና ጥራት ያለው የወርቅ ማእድን ለብሄራዊ ባንክ ለማቅረብ እቅድ አውጥተው እየሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ህብረት ስራ ማህበራቱ ለ210 ቋሚና ከ2 ሺ በላይ ሰዎች ጊዜያዊ የስራ እድል ማስገኘታቸው ታውቋል፡፡