በዞኑ በኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል

  • PDF

ሁመራ ህዳር 12/2005 (ዋኢማ) - በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚሰማሩ ባለሃብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

በዞኑ በሰልክላካ ከተማ አንድ ባለሃብት አማካኝነት ከ11ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባ ዘመናዊ ሆቴል ትናንት ተመርቆ አገልግሎት ጀምሯል ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚካኤል አብርሃ ዘመናዊ ሆቴሉን መርቀዉ ሲከፍቱ እንደተናገሩት በዞኑ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማሩ ባለሃብቶች ቁጥር ከ140 በላይ ደርሷል ።

እነዚሁ ባለሀብቶች በአሁኑ ጊዜ ከ1ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ አብዛኛዎቹ ወደ ስራ በመሰማራት ከ7ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አስታዉቀዋል ።

ወደ ማምረት ተግባር ከገቡት ልማታዊ ባለሃብቶች መካከል አንዱ አቶ ገብረእግዚ ፀሐዬ መሆናቸውን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ባለሃብቱ በእለቱ የተመረቀዉን ጨምሮ በዞኑ 50 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ በሁለት ከተሞች ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ገንብተዉ ለአገልግሎት ማብቃታቸዉን ገልጠዋል ።

የሆቴሉ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረእግዚ ፀሐዬ በበኩላቸው በእለቱ የተመረቀዉ ዘመናዊ ሆቴል ከ60 በላይ ሰዎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስታዉቀዋል ።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ሆቴሉ የሰሜን ተራሮችን ብሄራዊ ፓርክን ለመጎብኘት ለሚመጡ ቱሪስቶች አገልግሎት በመስጠት የሚኖረዉ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የክልሉ የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ኤጄንሲ ኃላፊ አቶ ከበደ አማረ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል ።