ሃገራዊ እቅዱን ለማሳካት የመፈጸም አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2005 (ዋኢማ) - ሃገራዊ እቅዱን ለማሳካት ልማታዊ አስተሳሰብን በማምጣት የመፈጸም አቅምን አሳድጎ በውጤታማነት መንቀሳቀስ እንደሚገባ የኢፊዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብአዴን ሊቀመንበር ተናገሩ።

የብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) 32ኛ አመት የምስረታ በአል ትናንት ተከብሮ ዋለ።

ሊቀ መንበሩ አቶ ደመቀ መኮንን ድርጅቱ ባለፉት 20 አመታት ፥ በአማራ ክልል ውስጥ ለተመዘገበው ሁለንተናዊ ዕድገት የመሪነት ሚናውን በመወጣት ድርሻ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ብአዴን የአማራ ክልል ህዝብ በህገ መንግስቱ መሰረት በክልላዊና በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የራሱን ሚና እንዲወጣ አስችሎታልም ነው ያሉት።

በክልሉ በግብርናው ዘርፍ በተለይም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ፥ አጠቃላይ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለተመዘገበው ተከታታይ እድገት ድርጅቱ ሚናውን እንደተወጣም ነው የጠቀሱት።

አቶ ደመቅ አያይዘውም የተሻለ ዕድገት እየተመዘገበ ቢሆንም ፥ ይህን ለማስቀጠል መልካም አስተዳደርን በማስፈን የሚታዩ ችግሮችን ማስወገድ ይገባልም ብለዋል።

እንደ ፋና ዘገባ የሚመዘገበው ለውጥ ሁሉን አቀፍና የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቀዱን ማዕከል ያደረገ መሆን እንደሚገባው ጠቁመው ፥ የህዝቡን ባለቤትነት ይዞ መንቀሳቀስ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።