ምርጫ 2005ን በላቀ ተሳትፎ ለማሳካት የኢትዮጵያ ህዝብ ሊዘጋጅ ይገባል!

  • PDF

ዮርዳኖስ

በቅርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን አካሂዶ ነበር። ምክር ቤቱ ከተቋቋመ ጀምሮ እስካሁን ባለው ሂደት እየተገናኘ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራል። ይህ በአገራችን ታሪክ በአዲስ ምዕራፍ ውስጥ የተወጠነ ሌላ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑ ለማንም እሙን ነው።

የአገራችን ፖለቲካ ከጥላቻ ፖለቲካነት ወደ ህይወት ያዘለ የፖለቲካ ፍትጊያ ለመቀየር መሠረት የሚጥል ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ቀደም ሲል በአገራችን በሰፊው የነበረውና አሁንም በተወሰኑ ወገኖች እየተንፀባረቀ ያለው የፖለቲካ ትግል ጭፍን ትግል ነው።

የሚቀርበው ተቃውሞም ለተቃውሞ ተብሎ የሚደራጅ  መሆኑን ሕዝቡ እየተማረው እያወቀው መጥቷል። የተሰራ አልተሰራም፣ በዓይን የሚታይ የሚጨበጥና ያለ ነገር የለም በሚል ጭፍን ክርክር ይካሄድ እንደነበር ይታወቃል።

የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ተከትሎ ከመስራትና ለሕዝብ የፖለቲካ አማራጭን አቅርቦ በሃሳብ ልቆና ይበጀናል የሚል ስሜት በሕዝብ ዘንድ አሳድሮ ለመመረጥ ከመሞከር ይልቅ ብጥስጣሽ መሠረት የሌላቸውን የጥላቻ ሐረጎችን እየገጣጠሙ ሸውዶ ለማለፍ ወይም ሕገ መንግሥቱ በማይፈቅደው መንገድ ወደ ሕዝብ ኃላፊነት ለመምጣት የሚደረገው ጥረት ቀደም ሲል ጎልቶ ይታይ ነበር፡፡

በአንድ በኩል በሕገ መንግሥቱ ጥላ ሥር ሆነው በአገራቸው ፖለቲካ፣ ምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ጉዳይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈጥረዋል። እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው የፖለቲካ ድርጅት ጋር በአገራቸው ጉዳይ መሆን በሚገባው ነገር የሚወያዩበት መድረክ መፍጠር ችለዋል።

የምርጫ ሂደቶች ምን መመምሰል እንዳለባቸውና አባላቶቻቸው ምን ዓይነት ሥነ ምግባር ሊያሟሉ እንደሚገባቸው የጋራ መግባቢያ ሰነድነ ፈርመዋል። ይህንን ሰነድ ለአባላቶቻቸው በማስተማርም በአገሪቱ ነጻ፣ ዴሞራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እንዲቻል የተቻላቸውን ያህል ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ችግሮች ቢያጋጥሟቸው እንኳን በውይይት ለመፍታት የሚያስችላቸውን አሠራር በጋራ መዘርጋት ችለዋል።

በዚህ መልክ የአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እየተጠናከረ እንዲሄድና ሕዝብ ከሚቀርቡለት በርካታ አማራጮች ይጠቅመኛል ያለውን  ለይቶ መምረጥ እንዲችል አመቺ ሁኔታ መፍጠር የተቻለበት ሁኔታ ታይቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን የስምምነት ኮድም ሆነ ተባብሮና ተጋግዞ መስራት የማይፈልግ ጭፍን የፖለቲካ ጥላቻ የሚያራምድ ጎራ በተወሰኑ የዲያስፖራ አባላት ተንጠልጥሉ አገሪቱ ምንጊዜም ሠላም እንዳታገኝ ከሚሹ ወገኖች ጎራ ተሰልፎ ጽንፈኛ እንቅስቃሴ የሚያደርግ የፖለቲካ ድርጅት መኖሩ እሙን ነው።

ይህ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጥላ ከለላ መመስረት ቢችልም አጠቃላይ ድርጊቱ ግን ሕገ መንግሥቱን የመናድ ተግባር ነው። በአገሪቱ ጭፍን የፖለቲካ ዘመቻ ማካሄድ ነው። በአገሪቱ የሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎችን መቃወም ነው። ከሽብርተኞችና ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመተባበር በአገሪቱ ሠላም እንዳይኖር የሁከትና የብጥብጥ አጀንዳ መፍጠር ነው።

በዚህ መልክ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዳይካሄድ የማሰናከል ሥራን ያከናውናል። ሕዝብን የማወናበድና ትክክለኛ ያልሆነ መንገድ እንዲከተል የማድረግ ስልቶችን ነድፎ ይንቀሳቀሳል። በዚህ ጽሁፍ ትኩረት ለመስጠት የተፈለገው ግን ለሁለተኛው ቡድን አይደለም። በአገሪቱ በሠላማዊ መንገድ የጋራ መድረክ ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ ባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የሰሞኑ ውይይትና ከመራጩ ከኅብረተሰቡ ምን እንደሚጠበቅ ለመጠቆም ያህል ነው።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በ2005 ዓ.ም በሚካሄደው የከተማና የአካባቢ ምርጫ ሠላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያግዛሉ ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በአገሪቱ የተረጋገጠው የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል ገዥው ፓርቲ ያልተቆጠበ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። የዘንድሮው ምርጫ እንዳለፉት ምርጫዎች  ደረጃውን የጠበቀ ነጻ፣ ፍትሃዊና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ የተቻላቸውን ያህል እንደሚንቀሳቀሱና ለእንቅስቃሲያቸውም ሕገ መንግሥቱንና በጋራ ያወጡትን የምርጫ ሥነ ምግባር መርህ እንደሚከተሉ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የአዲስ አበባ ከተማና የአካባቢ ምርጫን በሚመለከት ሊከተላቸው የሚገቡ አቅጣጫዎችንና አሠራሮችን በመለየት ተወያይቶባቸዋል። በዚህ ውይይት ሊያጋጥሙ ይችላሉ የተባሉ ችግሮችን  እንዴት መፍታት እንደሚቻልና በሌሎች ተያያዥ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ   አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀደም ሲል ባወጡት የሥነ ምግባር ደንብና በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት ተፈጻሚ እንዲሆን ስምምነት ላይ ደርሷል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጨባጭ የሆነ የሚታይና የሚዳሰስ፣ አገሪቱን ይጠቅማል የሚሉትን አጀንዳቸውን ይዘው በመቅረብ፤ ሕዝቡ ደግሞ ይኼ ፓርቲ እኛን ያስተዳድራል በሚል በሚሰጠው ድምጽ ላይ ተመስርቶ የወረዳ ምክር ቤቶች እንዲመሰረቱ አመቺ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።

ምርጫው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር መርህን መሠረት አድርጎ እንዲፈፀም በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምክንያት ውይይቶችን በማድረግ በጋር  ለመሥራት ተስማምቷል።

የጋራ ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የጋራ ምክር ቤቶችን በማቋቋምና በማጠናከር ለምርጫው ሠላማዊነትና ፍትሃዊነት በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል። ምርጫው የሴቶችንና የወጣቶችን ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሆን ሁሉም የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ጠንክረው እንዲሰሩ ተደርሷል።

በዚህ ምርጫ አስፈላጊ የሆኑት ሌሎች ነገሮች የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን አጀንዳ እንዴት ለሕዝብ ማድረስ እንዳለባቸውና ይህንን ለማከናወን የሚያስፈልጋቸው ገንዘብ በምን መልክ መሸፈን እንደሚኖርባቸው የሚሉ ዐበይት ጉዳዮች ላይ መወያየትና መስማማት ነበር። በዚህ መልክ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ  ምክር ቤት በሚዲያና ፋይናንስ ነክ ጉዳዮች ላይ ባደረገው ውይይት መግባባት ላይ ከመድረሱም በተጨማሪ ቀጣይ የአፈጻጸም አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

እንደሚታወቀው ለአንዲት አገር የሕዝቡ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነት መረጋገጥ ወሣኙ ነገር የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጠናከር ነው።  የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በተዘረጋበት አገር ማንኛውም አካል ወደ ሕዝብ ኃላፊነት የሚመጣው በሕዝብና በሕዝብ ምርጫ ብቻ ይሆናል። ይህ ተረጋገጠ ማለት ደግሞ ሕዝብ ይጠቅመኛል ያለውን የሚመርጥበት አይበጀኝም ያለውን የሚያወርድበት ሥርዓት ሰረፀ ማለት ነው። እነዚህ ነገሮች ሲረጋገጡ የሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነት ተረጋገጠ ማለት ይቻላል።

የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በአገራችን ላለፉት 21 ዓመታት ተግባራዊ መሆን ችሏል። ሕዝቡም የሥልጣን ባለቤትነቱን በሚገባ ሲተገብረው ቆይቷል። በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት የተጀመረው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አሁን ላይ ቆመን ስንገነዘበው የማይናወጥ መሠረት መጣሉን መረዳት ይቻላል።

የሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነት ተረጋገጠ የሚባለው በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኖረው የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለሕዝብ እያስተዋወቁ ሕዝብ ይጠቅመኛል፤ ይበጀኛል ያለውን መምረጥ ሲችል ነው። ሕዝቡ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አግኝቶ አንዱን ከአንዱ በማነጻጸር መምረጥም ሆነ መጣል የሚችልበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው።

የተለያየ አጀንዳ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት በመደራጀት አጀንዳቸውን ለሕዝብ በማቅረብ መመረጥ የሚችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው። በዚህ መልክ ዜጎች እንደየፍላጎታቸው የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን በመመስረት በአገራቸው የፖለቲካ ሥርዓት በነጻነት ተሳታፊ መሆን ከቻሉ የሕዝቡ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነት መረጋገጡ እውን ሆነ ማለት ነው። 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነቱን ተነጥቆ ኖሯል። ባለፉት ሥርዓታት የነበረው ሁኔታ ሲቃኝ መንግሥታት በጠመንጃ አፈ ሙዝ   የሕዝብን  የፖለቲካ ሥልጣን አፍኖ የሥልጣን እድሜውን ሲያራዝም ኖሯል። ፈላጭ  ቆራጭ መሪዎችን  ማስተናገድ ለኢትዮጵያውያን የተሰጠ ፀጋ ይመስል በርካታ ዓመታት በዚህ መልክ ተቆጥረዋል። 

በኢትዮጵያ ታሪክ ለዘመናት ነግሶ የነበረውን የአፈና ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሥር መሠረቱ በ1983 ዓ.ም ከተናደ በኋላ የተፈጠረው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መሠረቱ እየተጠናከረ መጥቷል። በአፍሪካ አህጉር ተወዳዳሪ ያልነበረውን ግዙፍ ሠራዊት በመገንባት አምባገነንነትንና ጭቆናን በአገሪቱ አስፍኖ የነበረው ሥርዓት ተገርስሶ በኢትዮጵያ የተጻፈው ደማቅ ታሪክ እየተጠናከረ መጥቶ ከማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል።  
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሠላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ባልነበረባት ኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መገንባት አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ይታወቃል። ቀደም ሲል የነበረው ተሞክሮም የራሱን ጫና ማሳደሩ አይቀሬ ይሆናል።
እንደሚታወቀው ሁሉ አገሪቱ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የበላይነት የነገሰባት አገር ነበረች። በወቅቱ የነበረው ፓርቲ ከሚከተለው የፖለቲካ አመለካከት የተለየ ሀሳብ ማመንጨትም ሆነ ማራመድ በሕግ የተከለከለ ነበር። የተለየ ሀሳብ ማመንጨት ፈጽሞ አይታሰብም ብቻ ሳይሆን በሕግ የሚያስቀጣና የሚያስኮንን ነበር፡፡  
የዜጎች የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነት የታፈነበት ዘመን ስለነበር  ምርጫ ይባል የነበረው የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በብዛት ይቀርባሉ፤ ከእነሱ መካከል ምርጫ ይካሄዳል። በአገሪቱ የአሃዳዊ ሥርዓት አስተሳሰብ የነገሰበትና ዜጎች የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነታቸው የተነጠቀበት ሁኔታ ነበር።
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አገር ነች። በአገሪቱ 75 የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ሕጋዊ እውቅና አግኝተው በፌዴሬሽን ምክር ቤት መቀመጫ ወንበርም አላቸው።
ቀደም ሲል የነበረውና ዜጎች  ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ለመጠቀም የማይችሉበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋቸውንና ባህላቸውን የማሳደግና የማዳበር ሥራ አጠናክረው እየተገበሩት ይገኛሉ፡፡ 
ባለፉት አሥርት ዓመታት በተደረገው ጥረት በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እውን ሆኗል፡፡ የተለያየ የፖለቲካ እምነት ያላቸው በርካታ ፓርቲዎች ተፈጥረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ 
በአገሪቱ ይህንን ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውና ተሳትፎ ማድረጋቸው የሚያሳየው ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ነው። አንደኛው ዜጎች በፈለጉበት የፖለቲካ ድርጅት አባል የመሆን መብታቸው መረጋገጡ ሲሆን ሌላው ደግሞ በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ ምህዳር እየሰፋ መምጣቱን ነው።
በመጀመሪያው የተቀመጠው ነጥብ ዜጎች በተፈጠረው ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር ተጠቅመው እንደየፍላጎታቸው በሚያምኑበት የፖለቲካ አጀንዳ ሥር በመደራጀት በአገራቸው የፖለቲካ፣ ምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ድርሻቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸው ሁኔታ መፈጠሩን ያሳያል።
በሁለተኛ ደረጃ የተጠቀሰው ደግሞ በአገሪቱ ወደ ሥልጣን መምጣት የሚቻለው  በሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ ብቻ መሆኑ የተረጋገጠበትን ሁኔታ ማየት የሚቻልበት አቅጣጫ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። በዚህ መልክ በአገሪቱ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብት የሚያረጋግጥ ሥርዓት መፈጠሩንና ሥርዓቱ እየተጠናከረ መምጣቱን ነው የሚያሳየው፡፡ ባለፉት 21 ዓመታት የታየውና የተረጋገጠውም ተሞክሮ ይኸው ነው፡፡ በዚህ መልክ በአገራችን አራት አገራዊ፣ ሦስት የአካባቢና በርካታ የሟሟያ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ 
የመጀመሪያው ታሪካዊ ምርጫ የተካሄደው በ1987 ዓም ነበር። በዚያን አገራዊ  ምርጫ 57 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል። ምርጫው የመጀመሪያው መድብለ ፓርቲ የተሳተፉበት ምርጫ መሆኑ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ነበር።  ምርጫው ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነጻና በአገሪቱ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ነበር፡፡ 
ፍጹም ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ የነበረው የ1987ቱ ምርጫ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የዓለም ኅብረተሰብንም ጭምር ያስገረመና በአገሪቱ የሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነትን ያረጋገጠ ነበር፡፡
በአገሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ በ1992 ዓ.ም ምርጫ ተካሄደ። በዚህ ምርጫ 49 የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል፡፡ ምርጫው እንደ ቀዳሚው ሁሉ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ነበር፡፡ ሕዝቡ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠለትን የፖለቲካ ሥልጣን በመጠቀም ይጠቅመኛል ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ በአገሪቱ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ መርጧል፡፡
1997 ዓ.ም ሌላው ታሪካዊ አገራዊ ምርጫ የተካሄደበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ዓመት በአገሪቱ ተመስርቶ ሥር እየሰደደ የነበረውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ለመናድ የተነሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ምርጫ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ሕገ መንግሥቱን ሕገ ወጥ በሆነ መልክ በመናድ ሥልጣን ለመቆናጠጥ ከፍተኛ ጥረት የተደረገበት ወቅት ነበር። በዚህ አገራዊ ምርጫ አንድ ብሄር፣ ብሄረሰብና ሕዝብ በሌላው ላይ እንዲነሳሳ፤ አገሪቱ ውስጥ የነበረው ሠላም እንዲደፈርስ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሠላምና ልማት ወጥተው መቋጫ በሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንዲዘፈቁ ለማድረግ ያልተሞከረ ነገር አልነበረም። በሦስተኛው አገራዊ ምርጫ 36 የፖለቲካ ድርጅቶች ተሳትፈዋል። 
በ2002 ዓ.ም የተካሄደው አራተኛው አገራዊ ምርጫ ከሦስተኛው አገራዊ ምርጫ የሚለየው በሦስተኛው አገራዊ ምርጫ ከ130 በላይ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አባላት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘታቸው ነው።  በአራተኛው አገራዊ ምርጫ  የተሳተፉት  የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር 63 ቢሆንም ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት የተመረጠው  አንድ አባል ብቻ ነበር፡፡
በአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ከተዘረጋበት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ የአንድ ፖለቲካ  ፓርቲ  ፈላጭ ቆራጭነት አክትሟል። ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የተለያየ አጀንዳ ያነገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች ተመስርተዋል፡፡ ሆኖም  በአሃዳዊ   አስተሳሰብ  የሰከሩ  ስብስቦች  በተከፈተላቸው ሜዳ መጋለብና በአገራቸው የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የቻሉትን ያህል  አስተዋጽኦ ማድረግ ሲጠበቅባቸው    የመድበለ  ፓርቲ  ሥርዓቱን  ለመፈታተን   ያላደረጉት  ጥረት  አልነበረም፡፡ ይሁንና እያደር  እየከሰሙ  የመጡበት  ሁኔታ  ተፈጥሮ  በአገራችን አስተማማኝ   የመድበለ   ፓርቲና   የፌዴራል ሥርዓት   ተዘርግቷል፡፡ በዚህ ዓመትም አራተኛውን የአካባቢ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት  እየተደረገ  ነው፡፡  ምርጫውን ግልጽ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችም ተመቻችተዋል።
ከአሁን በፊት የተካሄዱ ብሄራዊና የአካባቢ ምርጫዎችን በጥልቀት በመገምገም የምርጫዎቹን ጠንካራና ደካማ አፈጻጸሞች የመለየት ሥራ ተከናውኗል። ይህንን መሠረት በማድረግ ጠንካራ አፈጻጸሞችን የበለጠ የማጠናከርና ክፍተት የታየባቸውን ደግሞ በቀጣይ ምርጫ ለማስወገድ የሚያስችል አቅጣጫ ለማስያዝ የተለያዩ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ነው። 
ካለፉት በርካታ ምርጫዎች መሻሻል ያለባቸው ሦስት ዐበይት ነገሮች ተለይተዋል። በመጀመሪያ ደረጃ የመራጮች የሥነ ዜጋ ትምህርት ማኑዋል አለመኖሩና ዜጎች የምርጫ መብታቸውንና ግዴታቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ የማድረጉ ሁኔታ በተጠናከረ መልክ አለመሰራቱ ነበር። ይህንን በ2005 ዓ.ም በሚደረገው የአካባቢ ምርጫ ለማሻሻል የምርጫ የዜጎች ሥነ ዜጋ ማንዋል ተቀርጾ ሥልጠና እየተሰጠበት ይገኛል።   ቦርዱ ከገጽ ለገጽ ሥልጠና በተጨማሪ የብዙኃን መገናኛ አውታሮችን መጠቀም በማስፈለጉ በ13 የተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀ የዜጎች የሥነ ምግባር አስተምህሮ በስምንት የመገናኛ ብዙኃን እያስተላለፈ ይገኛል።
አንዳንድ ክልሎችም ቋንቋውን በማስፋት ለሕዝባቸው ተደራሽ ለመሆን አስተምህሮውን እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡ የአማራ ክልል በአራት ቋንቋዎች፣ የደቡብ ሕዝቦች ክልል ደግሞ በ23 ቋንቋዎች አስተምህሮ እየሰጠ ነው። መራጮች የምርጫ ደንቦችንና ሕጎችን ማወቅ የሚያስችልና የምርጫ ሥነ ዜጋ ክህሎታቸውን ይበልጥ ለማጎልበት የጎላ ሚና ይኖረዋል።
ያለፉት ምርጫዎች ከነበሩባቸው ክፍተቶች መሻሻል የሚገባው ሌላው ነጥብ  ደግሞ የባለ ድርሻ አካላትን አቅም መገንባት ነው። ከዚህ አንጻር የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገሪቱን ሕገ መንግሥት አክብረው ከመንቀሳቀስ አንጻር  የተለያየ ሥልጠና የመስጠት አቅጣጫ ተይዟል። 
የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ ሥልጠና የሚያገኙበትና በመካከላቸው ያለውን ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ መግባባት እንዲኖርና በሠላማዊ መንገድ ሕዝቡ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነቱን እንዲጠቀም ለማስቻል የምክክር መድረኮች ይዘጋጃሉ። በዚህ መልክ በ2004 ዓ.ም ስድስት የተለያዩ መድረኮች ተዘጋጅተዋል፡፡ ገንቢ ውይይቶችም ተካሂደዋል፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ የተለያዩ መድረኮች እንደሚዘጋጁ ይጠበቃል። 
በዚህ ዓመት ለየት ያለ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለው ሌላው ጉዳይ የሴት ተመራጮችን ቁጥር ማሳደግ የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር ነው።  እንደሚታወቀው ሁሉ በ1987 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመረጡ ሴቶች ቁጥር 13 ብቻ ነበር። ይህ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ አድጎ በአሁኑ ወቅት ከ547 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል 152ቱ ሴቶች ናቸው።  እያደገ የመጣውን የሴቶች ተሳትፎ  የበለጠ ለማሳደግ  አቅጣጫ ተይዞ  እየተሰራ ነው፡፡ በዚህ ዓመት በሚካሄደው የአካባቢና የአዲስ አበባ ምርጫ ሴቶችን የበለጠ ተሳታፊ ለማድረግ እንደ ሴቶችና ወጣት ማህበራት የመሳሰሉ አደረጃጀቶች ጋር በመተባበር  ሥልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
በምርጫ ክልል ወይም በወረዳ ደረጃ ከሚመደቡት ሦስት የምርጫ አስፈጻሚዎች መካከል አንድ ሴት እንድትሆንና በቀበሌ ደረጃ ከሚመደቡ አምስት የምርጫ አስፈጻሚዎች ደግሞ ሁለቱ ሴቶች እንዲሆኑ ተደርጓል። በዚህ መልክ የአስመራጭ ምልመላ ተጠናቅቋል፡፡ ከህዳር 22 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ የማስፈጸም የሥልጠና ፕሮግራም ይኖራል። 
ለ2005 ዓ.ም የአካባቢ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሴቶች ተሳትፎ ላይ ልዩ ትኩረት ለመስጠት ይችሉ ዘንድ የተለያዩ የምክክር መድረኮችን የማዘጋጀቱ ሂደት ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡ 
ከላይ ከተገለጹት የቀደምት ምርጫዎች  ክፍተቶች በተጨማሪ በዘንድሮው የአካባቢ ምርጫ የተሻሻለው ነገር የመራጮች መዝገብና ካርድ የሚዘጋጅበት ቋንቋ ነው። በቀደሙት ምርጫዎች የአማርኛ ቋንቋ ብቻ ሥራ ላይ መዋሉ ይታወሳል፡፡ በዘንድሮው ምርጫ ግን ኅብረተሰቡ በሚገባው ቋንቋ አንብቦ መጠቀም እንዲችል የምርጫ ሰነዶቹን በአምስት ቋንቋዎች እንዲዘጋጁ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰነዶችን የማዘጋጀትና አትሞ የማውጣት አቅሙን በማሳደግ በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በአፋርኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ሰነዶቹ ተዘጋጅተዋል።
ከሰነዶች ዝግጅት ጎን ለጎንም በምርጫ ወቅት ቅሬታዎች ሊነሱ ነባራዊ በመሆኑ ቅሬታዎችን በምን መልክ መፈታት እንዳለባቸው የሚያመላክት ቅደመ ሥልጠናዎችና ዝግጅቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ለፍትህ አካላት የሥልጠና ፕሮግራሞች ተይዘው 80 ከመቶ የሚሆኑት ሰልጥነዋል፡፡ 
ቦርዱ ካለፉት ምርጫዎች አፈጻጸም ዳሰሳ ባገኘው ተሞክሮ መሠረት በተሻለ መዋቅርና አደረጃጀት ራሱን በማጠናከር እየሰራ ነው፡፡ ለዘንድሮው ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቷል፡፡ የእጩዎችና የመራጮች ምዝገባም ከታህሳስ 22 እስከ ጥር 21 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል፡፡ ሚያዝያ 6 ቀን 2005 ዓ.ም በመላ አገሪቱ ድምጽ ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ 
በአካባቢ ምርጫው የወረዳ፣ የቀበሌ፣ የማዘጋጃ ቤት፣ የከተማ አስተዳደርና የዞን ምክር ቤቶች አባላት እንደሚመረጡ ይታወቃል፡፡ ምርጫውን በስኬት ለማጠናቀቅ መላው ኅብረተሰብ  የበኩሉን ተሳትፎ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ 
ምርጫው እንደቀደሙት ምርጫዎች ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩም ይገባል። በአገሪቱ እውን መሆን የጀመረውን የሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን  ባለቤትነት ይበልጥ በማጎልበት፣  ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የሚያስችል ቀጣይነት ያለው ልማት በማረጋገጥ አገሪቱን ወደ ላቀ የእድገት ምህዋር ለማሸጋገር የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አንድነታቸውን አጠናክረው ሊሰሩ ይገባል።     
ባለፉት ምርጫዎች ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነቱን በተገቢው መንገድ ያረጋገጠበት ሁኔታ ታይቷል። በመጀመሪያው አገራዊ ምርጫ ለመምረጥ የተመዘገበው ሕዝብ ብዛት 21 ሚሊዮን 337 ሺህ 379 ሲሆን የመረጠው ደግሞ
19 ሚሊዮን 986 ሺህ 179 ነበር። በዚህ ምርጫ 43 የፖለቲካ ፓርቲዎች መቀመጫ ማግኘታቸው የሚታወስ ነው።
በሁለተኛው ምርጫ ደግሞ 21 ሚሊዮን 834 ሺህ 86 መራጮች ተመዝግበው 19 ሚሊዮን 607 ሺሕ 861  የመረጡ ሲሆን 42  የፖለቲካ ድርጅቶችም መቀመጫ ማግኘት ችለዋል። በ1997 እና በ2002  ደግሞ 27 ሚሊዮን 372 ሺሕ 888  እና 31 ሚሊዮን 926 ሺሕ 520 መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን 22 ሚሊዮን 610 ሺሕ 690 እና 29 ሚሊዮን 832 ሺሕ 190 መምረጣቸው የሚታወቅ ነው።
ከዚህ አሃዛዊ መረጃ ማየት እንደሚቻለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነቱን በበሚገባ እየተጠቀመ መምጣቱን ነው። ከአንድ ምርጫ ወደ ቀጣይ ምርጫ በሚገባበት ወቅትም የመራጭ ቁጥር እያደገ መምጣቱን መገንዘብ ይቻላል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ኅብረተሰቡ አጠቃላይ በአገሪቱ የተፈጠረውን ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም ይበጀኛል ያለውን ለመምረጥ ተሳትፎውን እያሳደገ መምጣቱን መገንዘብ ይቻላል።
በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በ1987 ዓ.ም ምርጫ ሲካሄድ የነበረው መራጭ ቁጥርና በ2002 ዓ.ም ከነበረው ጋር ቢነጻጸር የ10 ሚሊዮን  224 ሺሕ 329 መራጮች ልዩነት እንዳለው ማየት ይቻላል።
ይህ የአገራችን ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣኑን በአግባብ እየተጠቀመበት እንዳለ የሚያሳይ ነው። ከነበረው የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ፈላጭ ቆራጭነትና በአፈ ሙዝ ኃይል የታገዘ አገዛዝ ተላቆ ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተረጋግጦለትና በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እውን ሆኖ ዜጎች አንድም በሚያምኑበት የፖለቲካ ድርጅት የመሳተፍ መብታቸው ተከብሮላቸዋል፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ የሚመራቸውን የፖለቲካ ድርጅት ሥልጣን የመስጠትና በትክክል አይሰራልንም ያሉትን የማስወገድ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነታቸውን ያረጋገጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በዚህ መልክም እስካሁን የነበሩት ምርጫዎች በውጤታማነታቸው ተጠናቀዋል። በዘንድሮው የበጀት ዓመት ለሚካሄደው የአዲስ አበባ ምክር ቤትና የወረዳ ምክር ቤቶች እንዲሁም የአካባቢ ምርጫ ላይ ሕዝቡ እንደተለመደው ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አጀንዳዎች በሚገባ በመመርመር በነቂስ ወጥቶ ሊመዘገብና ድምጹን ሊሰጥ ይገባል።
የአንድ ዜጋ ድምጽ ትልቅ ዋጋ አለው። በመሆኑም ሁሉም እድሜው 18 እና ከዚያ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ምርጫውን ለመምረጥ ከወዲሁ ዝግጅት ሊያደርግ ይገባል። ይህ የሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነት እየተጠናከረ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ሥር የሰደደበት ሁኔታ ቢኖርም አንዳንድ አፍራሽ ወገኖች ሕዝቡ የመምረጥ መብቱን እንዳይጠቀምበት በሰንካላ ምክንያቶች ሊያወናብዱት ላይ ታች ሲሉ ይስተዋላሉ።
ይህ ግን ለአገራችንም ሆነ ለሕዝባችን የሚጠቅም ባለመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አጀንዳዎች በሚገባ በመመርመር ይጠቅመኛል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መጠበቅና እለቱ ሲደርስም በከፍተኛ ተሳትፎ ምርጫውን ማከናወን ይጠበቅበታል።