የብአዴንን 32ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ ከድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

  • PDF

የተከበራችሁ የአማራ ክልል ህዝቦች፤ የብአዴን አባላትና የትግሉ ደጋፊዎች በሙሉ እንኳን ድርጅታችን ብአዴን ለተመሠረተበት 32ኛው ዓመት የልደት በዓል አደረሳችሁ፤ እያለ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰማውን ደስታ ይገልጻል።

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በትግልና በድል ጎዳና እየተረማመደ እንሆ ዛሬ 32ኛ ዓመቱን በማክበር ላይ ይገኛል።  የያኔው ኢህዴን የአሁኑ ብአዴን ሲመሠረት እጅግ አስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ ነበር። ወቅቱ ፀረ-ዴሞክራሲና አምባገነኑ የደርግ መንግስት ጊዜያዊ የበላይነት ያገኘበትና በአንጻሩ ለዴሞክራሲና ለእኩልነት የሚታገሉ ህዝባዊ ድርጅቶች በከፍተኛ ደረጃ የተዳከሙበት ወቅት ነበር።  በመሆኑም “ደርግን ታግሎ መጣል ተራራን በገመድ መጎተት ነው” በሚል መንፈስ አያሌ ታጋዮችና ድርጅቶች በተስፋ መቁረጥ በተበታተኑበት ወቅት “ህዝባዊ ዓላማና ጽናት እስካለ ድረስ የደርግ የበላይነት ጊዜያዊ ነው። ታግሎ ማቸነፍ ይቻላል” የሚል ጽናትና አንበረከክም ባይነት አስተሳሰብ የነበራቸው ቆራጥ ታጋዮች ኢህዴንን መስርተው በትግልና በድል ጎዳና ዘልቀዋል።

የያኔው ኢህዴን የአሁኑ ብአዴን በተመሠረተበት አካባቢ የአማራ ክልል ህዝብን እያደራጀ ከትግል አጋሩ ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር በመተባበር አምባገኑን የደርግ ስርዓት ተፋልሟል።  የትግሉ ሂደት እየተጠናከረ በሄደበት ወቅት ኢህአዴግን በመመስረትና በማጠናከር የበኩሉን አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል።  በኢህዴን/ብአዴን የትግልና እድገት ሂደት የህወሓት ድጋፍ በተለይ ደግሞ የታላቁ መሪያችን የጓድ መለስ ዜናዊ ድርሻ ከፍተኛ ነበር። 

ብአዴን ከ1983 ዓ/ም በኋላም ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት እንዲጸድቅ፣ ባለፉት 21 ዓመታትም የልማትና ዴሞክራሲዊ ስርዓት እንዲጠናከርና የህዝቦች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትም እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ትግል አካሂዷል፤ የተሳካ ውጤትም አስመዝግቧል። 


ድርጅታችን ብአዴን የተመሠረተበትን ህዳር 11፣ 32ኛውን የልደት በዓል የምናከብረው ድርጅታችን ያለፈባቸውን የትግልና የድል ዓመታት በማሰብና የታላቁ መሪያችንን ራዕይ ለማሳካት በያዝነው ዓመት የላቀ የልማትና መልካም አስተዳደር ድሎችን ለማስመዝገብ ሰፊ ተግባራትን በማከናወን ይሆናል። የድርጅታችንን የልደት በዓል ስናከብር ብአዴን አንግቦት የተነሳውን ዓላማና ግብ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የመጣንበት ርቀትና በዚህ ሂደት የነበሩ ጥንካሬዎችንና እጥረቶችን በብቃት በመገምገም፣ ስኬታማ ተሞክሮዎችን በማስፋፋት፣ የጎደሉትን በመሙላት፣ የተሳቱትን በማረምና በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በመነሳሳትና በመዘጋጀት ነው። 

የድርጅታችን 32ኛው ዓመት እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በርካታ ስኬታማ ተግባራት የተከናወኑበት ነበር። በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን ሁለተኛው ዓመት ከመጀመሪያው ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ልምድ በመቅሰም በላቀ መነሳሳት ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ታቅዶ ርብርብ የተካሄደበት ዓመት ነበር። በመሆኑም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን መሠረት በማድረግ የክልሉን ህዝቦች ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት ተከናውነዋል። 

በአገር ደረጃ ለ9ኛ ጊዜ ለተመዘገበው 11.4 በመቶ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የክልላችን ድርሻ አዎንታዊ ሚና ነበረው። በዓመቱ የሰብል ልማት የዋና ዋና ሰብሎችን ወስዶ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባወጣው መረጃ መሠረት የሰብል ምርት ከ71 ወደ 77 ሚሊዮን ኩንታል ማሳደግ ተችሏል።  ባለፉት ዓመታት የተገኙትን የተፈጥሮ ሀብት ልማት ልምድ በመቅሰምና ሰፊ የህዝብ ተሳትፎን በማረጋገጥ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በሚልቅ መሬት ላይ የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ተግባራት ተከናውነዋል።  በመስኖ ልማትም 558 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 62 ሚሊዮን ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ተገኝቷል። በ2004/2005 የሰብል ልማት ላይ ጤፍን በመስመር መዝራትን ጨምሮ የተሻሻሉ ቴክኖሎጅዎችና አሠራሮች ተግባራዊ እንዲሆኑና የህዝቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ሰፊ ርብርብ ተደርጓል።  በመሆኑም በዓመቱ ከፍተኛ የግብርና ምርት እድገት ይጠበቃል። 

በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡት የግብርና ልማት ስኬቶች ድርጅታችን ብአዴንና  የክልላችን መንግስት እስከ አርሶ አደሩ ቀበሌዎችና መንደሮች ገብተው የህብረተሰቡን አስተሳሰብ ለማሳደግ ባካሄዱት ያልተቋረጠ ጥረትና በሰጡት ብቁ አመራር ነው። ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብአቶችንና ቴክኖሎጅዎችን በወቅቱ በማቅረብ፣ የአርሶ አደሩንና የባለሙያውን የማቀድና የመፈጸም ክህሎት ለማሳደግ ባደረጉት ያልተቋረጠ ርብርብ ነው። ህብረተሰቡና ባለሙያው ለስራ የተመቸ አደረጃጀት ውስጥ ገብቶ በመሠማራቱና አሠራሩን ጠብቆ ተግባራዊ በማድረጉ ነው።

በዓመቱ በኢንዱስትሪ ልማት መስክም አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል። ለክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት አቅም የሚሆኑ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በግንባታ ላይ ናቸው።  አንዳንዶቹም ማምረት ጀምረዋል። የግል ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንዱስትሪ ልማት መስኮች እንዲሠማሩ የመሠረተ-ልማት፣ የቦታና መሰል ድጋፎች ተደርገው አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።  ከአጭርና ከረጅም ጊዜ አኳያ የስራ እድል በመፍጠር፣ የገቢ አቅምን በማሳደግ፣ የግብርና-መር ኢኮኖሚ ልማትን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር መሠረት እንደሚሆኑ የታመነባቸውን የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለመገንባትና ለማጠናከር የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። 

አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትን ለማጠናከር በተቀመጡት የድጋፍ ማዕቀፎች መሠረት ከ42 ሺህ በላይ አንቀሳቃሾች ከእድገት ደረጃቸው ጋር የተገናዘበ ድጋፍ ተሰጥቷቸው በኢኮኖሚው ውስጥ ተወዳድረው እንዲዘልቁ ጥረት ተደርጓል። 24ሺህ አዳዲስ አንቀሳቃሾችን በማደራጀት ወደ ስራ ማስገባትም ተችሏል። በግልና በመንግስት ፕሮጀክቶች ከ358 ሺህ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተፈጥሯል።

በመሠረተ ልማት መስክ በዓመቱ እንዲከናወኑ በእቅድ ተይዘው የነበሩ የመንገድ ስራ ፕሮጀክቶች በተለይም ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኙ መንገዶች ግንባታ አጥጋቢ በሚባል ደረጃ ተከናውኗል። የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በገጠርና በከተማ ለማስፋፋት በተደረገው ጥረትም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ግቦችን የሚያሳካ አፈጻጸም ተመዝግቧል። 

በማህበራዊ ልማት ዘርፍም በአጠቃላይ ትምህርት ተሳትፎ ከ4.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ላይ ይገኛሉ። ጥራትን በማሻሻል ረገድም አጥጋቢ ውጤት ተገኝቷል። በተለይ ከበጀት ዓመቱ አጋማሽ በኋላ በተደረገው ርብርብ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማረጋገጥ፣ በትምህርት ተቋማት እድሳትና ግንባታ ተግባራት ለቀጣይ ስራ ትምህርት የተገኘበት ውጤታማ ተግባር ተከናውኗል። 

መከላከልን መሠረት ባደረገው የጤና ፖሊሲያችንና ስትራቴጂያችን መሠረት የመሠረተ ጤና እንክብካቤ እቅድ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ሆኗል። ህብረተሰቡ የተሳተፈበት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ከዓመት ዓመት የላቀ ልምድ እየተገኘበት አፈጻጸሙም እየተሻሻለ መጥቷል።  የእናቶችና ህጻነትን ሞት ለመቀነስ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን ካለፈው ዓመት አንጻር ሲወዳደር እድገቱ አበረታች ነው።

በሁሉም የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት መስኮች የተመዘገቡ ውጤቶች የህብረተሰቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ቢሆንም በገጠርና በከተማ በአካባቢዎች፣ እንዲሁም በህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ፍትሃዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ብዙ መስራትን ይጠይቃል።  በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ችግሮችን ለማስወገድ የተጀመረውን ልማት አጠናክሮ መቀጠልና ተጓዳኝ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ በዓመቱ ትኩረት የሚሰጥባቸው ይሆናሉ። 

የተከበራችሁ የአማራ ክልል ህዝቦችና የድርጅታችን ደጋፊዎች!

በተሃድሶ መስመራችን በግልጽ እንደተቀመጠው በአገራችንም ሆነ በክልላችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ሳይነጣጠሉ በተመጋጋቢነት ተግባራዊ የሚሆኑና ለህዝባችን ተጠቃሚነት ትኩረት የሰጠንባቸው አጀንዳዎች ናቸው። የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የህዝብ ቅሬታዎችን ከመፍታት በላይ ሂደው ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኑሮ መሻሻልና ከፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ጋር የተያያዘ መሠረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ድርጅታችን ይገነዘባል።  በመሆኑም ድርጅታችን የገጠርና የከተማ ልማት ላይ ከሚያደርገው ርብርብ በተጨማሪ ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር ግንባታም እኩል ክብደት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።  እናም በገጠር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና እያደገ የመጣ የልማታዊነት አስተሳሰብ የተፈጠረ ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ እየተዳከመ ይገኛል። 

በከተሞቻችን ከገጠሩ በተለየ ሁኔታ ኪራይ ሰብሳቢነት በመስፋፋቱ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ባካሄድነው ጠንካራ ፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ንቅናቄ አጥጋቢ ውጤት ተገኝቷል። አሁንም ቢሆን የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ በድርጅታችንና መንግስታችን የበላይነት እየተካሄደ ይገኛል። የልማታዊነት አስተሳሰብንና ተግባርን ለመገንባት በተደረገው ተከታታይ ጥረት በህዝብና በመንግስት ሀብት የመበልጸግ አመለካከትና ተግባራዊ ስምሪት የነበራቸው ኃይሎች ከመሸጉበት ተነስተው ወደኋላ እንዲያፈገፍጉና መረጃ የተገኘባቸውም በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል። የኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት የሆኑት የከተማ መሬት አስተዳደር አዋጅና ሌሎች አሠራሮችም ተፈትሸው የህገ-ወጥ በሮች እንዲዘጉ ጥረት ተደርጎ አጥጋቢ ውጤት ተገኝቷል። ይሁን እንጅ የኪራይ ሰብሳቢነት ማህበራዊ መሠረት ወደ ልማታዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ባልተቀየረበት ፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ በአንድ ወቅት እንቅስቃሴ ብቻ የሚቆም ሊሆን እንደማይችል ብአዴን ያምናል። በቀጣይነት ከልማትና ከመልካም አስተዳደር ጉዟችን ጋር ተሳስሮ የሚቀጥል መሆኑን ተገንዝበን ድርጅታችን፣ መንግስታችንና የክልሉ ህዝብ በጋራ ሊረባረቡበት የሚገባ አጀንዳ ሆኖ ይቀጥላል። 

በዓመቱ የተጠቀሱት አንጸባራቂ የልማትና መልካም አስተዳደር ስኬቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፤ የታላቁ መሪያችንና የተሃድሶ ጉዞው መሃንዲስ የጓድ መለስ ዜናዊ ያለጊዜው መስዋዕት መሆን ለድርጅታችን አመራር፣ ለአባላት እንዲሁም ለክልሉ ህዝብ መሪር ሐዘንና ቁጭት የፈጠረ ሆኗል።  ጓድ መለስ ለህዝቦች ነጻነትና እኩልነት በጽናት የታገለ ታላቅ መሪ ነው።  በአገራችን ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማት እንዲረጋገጥ በታላቅ ህዝባዊ ወገንተኝነት፣ ታታሪነትና ጽናት አመራር የሰጠና ኢትዮጵያን ከማያቋርጥ የድህነትና የኋላቀርነት የቁልቁለት ጉዞ አውጥቶ ወደ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የእድገት ምህዋር ያስገባ ምርጥ የህዝብ ልጅ ነው። 

የድርጅታችንን 32ኛ ዓመት የልደት በዓል የምናከብረው የክልላችንና የአገራችን ህዝቦች በታላቁ መሪያችን መስዋዕት መሆን በፈጠሩት ቁጭትና የመሪያችንን ራዕይ አጠናክረን እንቀጥላለን በሚል ከፍተኛ ህዝባዊ መነሳሳትና ህዝባዊ ማዕበል በተፈጠረበት ወቅት ላይ ሆነን ነው። ህዝባዊ ማዕበሉን በብቃት መርቶ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማስፈጸም ድርጅታችን የላቀ ዝግጅት አድርጓል። እቅዳችንን ለማሳካት ድርጅታችን፣ መንግስታችንና ጠቅላላ ህብረተሰቡ በተደራጀ አግባብ ተንቀሳቅሰው የላቀ ውጤት እንደሚያስመዘግቡም ይጠበቃል። በያዝነው ዓመት የሚካሄደው የወረዳና የቀበሌ ምክር ቤቶች ምርጫ ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የህዝቦችን አመኔታ በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲፈጸም ጥረት ይደረጋል።

ታላቁ መሪያችን በመስዋዕትነት ቢለየንም ትግሉ የማራቶን ሩጫ ሳይሆን የዱላ ቅብብሎሽ በመሆኑ በጓዳችን ሃሳብ አመንጭነት የተዘጋጁ የተሃድሶ መስመሮቻችንን ተከትለን፣ ከአንድ ትውልድ በላይ የሚዘልቁና የአገራችንን የሠላም፣ የዴሞክራሲና የልማት እድሎች የሚወስኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጅዎች ባለቤት በመሆናችን “በአንበረከክም” ጽናት የመለስንና የድርጅታችንን ራዕይ ከግብ ለማድረስ  እንረባረባለን። 

በመጨረሻም የድርጅታችን አባላት፣ የክልላችን ህዝቦች፣ ልማታዊ ባለሀብቶች፣ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ የልማትና መልካም አስተዳደር ግቦችን ለማሳካት ላደረጋችሁት ርብርብና በኋላም በታላቁ መሪያችን መስዋዕት መሆን በነበራችሁ መሪር ሐዘን፣ ቁጭትና ራዕዩን እናሳካለን የሚል መነሳሳት፤ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አድናቆቱን እየገለጸ ይህ ህዝባዊ መነሳሳት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን ያቀርባል። 

    ዘመቻ መለስ ለእድገትና ለአረንጓዴ ልማት ግባችን ይሳካል!!
    ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሠማዕታት!!