በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ወደ ውጪ ከተላኩ ምርቶች ወደ 7 መቶ ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ተገኘ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2005 (ዋኢማ) - በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ወደ ውጪ ከተላኩ የተለያዩ ምርቶች ወደ 7 መቶ ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ገቢ መገኘቱን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አብዱራህማን ሰይድ ዛሬ ለዋልታ እንደገለፁት ገቢው 6 መቶ 99 ሚሊዮን 78  የአሜሪካ ዶላር ገቢ የተገኘው ወደ ተለያዩ ሀገራት ከተላኩ የግብርናና የእንዲስትሪ ምርቶች  ነው።

ቡና ፤ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የቁም እንስሳት፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፤ የቅባት እህሎች፤ ጥራጥሬ፤ ቅመማ ቅመም ፤ የቁም እንስሳት ፤አበባ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ወደ ውጭ ከተላኩት ምርቶች ዋና ዋናዎች መሆናቸውን ሃላፊው ተናግረዋል።

እንድ አቶ አብዱራህማን ገለጻ በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት የተገኘው ገቢ በዕቅድ ከተያዘው ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ጋር ሲነጻጸር በ66 በመቶ ዝቅ ያለ ነው።

የቡና ዋጋ መዋዠቅ፣ የገዥዎች በገቡት ኮንትራት መሰረት ውል አለመፈጸምና በወደብ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው መጨናነቅ ለገቢው መቀነስ እንደ ዋና ምክንያቶች ከሚጠቀሱት መካከል እንደሆኑ ሃላፊው ተናግረዋል።

ባለፈው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ወደ ውጪ ከተላኩ የተለያዩ ምርቶች የተገኝው ገቢ 7 መቶ 52 ሚሊየን 9 መቶ 88 ሺ ዶላር መሆኑን አቶ አብዱራህማን አስታውሰዋል።