ብአዴን ህዝባዊ አላማና ጽናትን አንግቦ ባካሄደው መራራ ትግል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ማረጋገጥ ችሏል - ማእከላዊ ኮሚቴዉ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11ሐ 2005 (ዋኢማ) -  የብሔር አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ባለፉት 21 ዓመታት የክልሉን ህዝብ ከከፋ ድህነት በማላቀቅ የልማትና መልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ለማድረግ በሰጠዉ የአመራር ብቃት ተጨባጭ ዕድገት ማስመዝገቡን ማዕከላዊ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ አስታወቀ ።

ማዕከላዊ ኮሚቴው የድርጅቱን 32ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ብአዴን ህዝባዊ አላማና ጽናትን አንግቦ ባካሄደው መራራ ትግል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ማረጋገጥ ችሏል። የቀድሞዉ ኢህዴን የአሁኑ ብአዴን የአማራ ክልል ሕዝብን እያደራጀ ከትግል አጋር ድርጅቶች ጋር ፀረ-ዴሞክራሲና አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመደምሰስ በቆራጥ ታጋይ ጀግኖች እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ በድል ጎዳና ዘልቋል ።

ብአዴን የተመሰረተበትን ህዳር 11 የልደት በዓል የምናከብረው ድርጅቱ ያለፈባቸውን የትግልና የድል አመታት በማሰብና የታላቁ መሪያችንን ራዕይ ለማሳካት በያዝነው ዓመት የላቀ የልማትና የመልካም አስተዳደር ድሎችን ለማስመዝገብ ሰፊ ተግባራትን በማከናወን ይሆናል ሲል መግለጫዉ አመልክቷል ።

እንዲሁም ድርጅቱ አንግቦት የተነሳለትን ዓላማ ተግባራዊ በማድረግ ያለፉትን እጥረቶች በብቃት በመገምገምና ስኬታማ ተሞክሮዎችን በማስፋፋት በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም በቁርጠኝነት ሊረባረብ እንደሚገባ መግለጫው አስታዉቋል ።

የድርጅቱ 32ኛ ዓመት ሲከበርም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን መሰረት በማድረግ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን በማከናወን እንደሚሆንም መግለጫው አመልክቷል።

ብአዴን የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችንና ግብአቶችን አርሶ አደሩ በስፋት እንዲጠቀም በማደረግ የግብርና ምርትን በእጥፍ ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ነድፎ ተግባራዊ ያደረገው የግብርና ፖሊሲና ስትራቴጂ ግቡን እየመታ ነው ብሏል ።

እንዲሁም መከላከልን መሰረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ በማደረግ የእናቶችንና ህፃናት ሞትን በመቀነስ፣ የትምህርትን ተደራሽነት በማስፋፋትና ሌሎች ለእድገት መሰረት የሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በመዘርጋት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ማዕከላዊ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ አስረድቷል። መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና በተለይም በከተሞች በስፋት የሚስተዋለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ከምንጩ ለማድረቅ ድርጅቱ ከመላው አባላቱ ጋር ያደረገው ጠንካራ የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ንቅናቄ ትግልም አጥጋቢ ውጤት የታየበት በመሆኑ ይህንኑ አጠናክሮ እነደሚቀጥል የማእከላዊ ኮሚቴዉ መግለጫ ያመለክታል ።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ድርጅቱ 32ኛ አመት የምስረታ በዓሉን የሚያብረውም የክልሉና የሃገራችን ህዝቦች በታላቁ መሪያችን ድንገተኛ ህልፈት የተፈጠረውን ቁጭትና መነሳሳት በብቃት በመምራት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማስፈፀም በድጋሚ ቃል በመግባት እንደሚሆን አስታዉቋል ። በኢኮኖሚና በማህበራዊ የልማት መስኮች የተመዘገቡ ውጤቶች የህብረተሰቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ቢሆኑም በቀጣይ በገጠርና በከተሞች የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ከዳር ለማድረስ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ድርጅቱ በመግለጫው አረጋግጧል ።