በውሃ የላብራቶሪ ፍተሻ ላይ ያሉትን አሰራሮች አንድ ወጥና ደረጃውን የጠበቀ ማድረግ ጠቀሜታ አለው

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11ሐ 2005 (ዋኢማ) - በውሃ የላብራቶሪ ፍተሻ ላይ ያሉትን አሰራሮች አንድ ወጥና ደረጃውን የጠበቀ ማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋሻው ተስፋዬ የላብራቶሪ ፍተሻ ንፅፅር ግምገማ ዓውደ ጥናት ላይ እንደተናገሩት በላብራቶሪ ፍተሻ ላይ አንድ ዓይነት ውጤት ማምጣት ዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፣ እውቅናና ተቀባይነት ለማግኘት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

የደቡብ አፍሪካና አካባቢ ሃገራት የውሃ ላቦራቶር ፍተሻ ንጽጽር ግምገማ ዓውደ ጥናት ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ መካሄዱ ለሀገሪቷ ልዩ ጥቅም እንደሚያስገኝ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ አገሮች ያሉትን ላብራቶሪዎች የፍተሻ ውጤታቸውን ትክክለኛነት በመገምገም የብቃት ደረጃቸውን በማሳወቅ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተቀባይነታቸውን ለማሳደግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ጥራት ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ ውድድር እንዲኖር ከውሃ ጥራት ጋር በተያያዘ የተሻለ ሳይንሳዊ መረጃ ለማግኘትና ለእውቀት ሽግግር አውደ ጥናቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የላብራቶሪ ፍተሻ ንፅፅር ግምገማ በአፍሪካ ለዘጠነኛ ጊዜ መካሄዱን የጠቆሙት አቶ ጋሻው ኢትዮጵያ በሶስቱ ላይ ተሳታፊ ሆናለች ብለዋል፡፡ ዓለም ዓቀፍ እና ዘመናዊ ተቀባይነት ባለው አደረጃጀት በመስራት በአምራቾችና በአገልግሎት ሰጪዎቸ መካከል ጥራት ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ ውድድር እንዲኖር ዓውደ ጥናቱ መሰረት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ የኢትዮጵያ የተስማሚ ምዘና ድርጅት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ለአራት ቀናት ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ ከተለያዩ አገራትና ከኢትዮጵያ በውሃ ፍተሻ ሥራ ላይ የተሰማሩ ከ30 በላይ የሚሆኑ ባለሙያዎች ተሳታፊ ናቸው፡፡ ተሳታፊዎቹ በቆይታቸው የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ላቦራቶሪዎችን ይጎበኛሉ፡፡